ልክ ለልከኝነት(2…)

ቤተክርስቲያን

ልክ የመጠን ዳርቻ እንደመሆኑ ነገሮች ከልክ እንዳያልፉብን ብንጠነቀቅ ልክ ነን። የኛ የሆኑ ነገሮቻችንና የሌሎችም ነገሮች ጨምሮ ከልካቸው መስመር እንዳያልፉ እንደሚያሳስብ ቀጥሎም ማየት እንችላለን፤ በእርግጥ እነርሱን ማወቅ ለሚዛናዊ ህይወት ይጠቅማል፦
• የቅጣት ልክ
2ቆሮ.2:5-7 “ነገር ግን ማንም አሳዝኖ ቢሆን፥ እንዳልከብድባችሁ፥ በክፍል ሁላችሁን እንጂ እኔን ያሳዘነ አይደለም። እንደዚህ ላለ ሰው ይህ ከእናንተ የምትበዙት የቀጣችሁት ቅጣት ይበቃዋልና እንደዚህ ያለው ከልክ በሚበዛ ኀዘን እንዳይዋጥ፥ይልቅ ተመልሳችሁ ይቅር ማለትና ማጽናናት ይገባችኋል።”
ሁሉ ነገር ልክ አለው፣ ይህም ለጤናችንም ጭምር የሚበጅ ነው (ለምሳሌ ያለልክ መመገብ አደጋ ነው)፤ ልክ ሲያልፍ በልክ የተሰራው ማንነታችን እንዳይናጋ ያስፈራል፤ ልከኝነት በተለይ በአማኝ ዘንድ አግባብነት ያለው ነገር ነው፣ እንዲሁም ተጠባቂ ነው። ሁለት ሰዎች እኩል ሰአት አይጸልዩም፣ እኩል ሰአት አይጾሙም፣ እኩል ሰአት አያነቡም ወዘተ። በደስታችን ልክ ማድረግ ከተገባ በሃዘናችንም እንዲሁ ነው፣ ስንመላለስ ግንኙነታችን ልክ ያለው ከሆነ ባሳዘነን ላይም ልከኛ ቅጣት ይገባዋል። ክርስትና ከመንፈሳዊ ህይወት ባለፈ ማህበራዊውንም፣ ቤተሰባዊውንም ህይወት ልከኛ ያደርጋል። በተለይ በቤተክርስቲያን ውስጥ ላለ ግንኙነት ልከኛነት እጅግ መሰረታዊ ነገር ነው። ልከኛነት ስርአት አይደለም፣ ጤነኛ ልምምድ ነው። ለምሳሌ በሃጢያት የወደቀ ሰው እስከመቼ ድረስ ይገሰጻል? እስከ መቼስ ከቅዱሳን ይነጠላል? ያለ ገደብ? ያለ ልክ? ቃሉ ሃጢያት ውስጥ የወደቀ ወንድም በንሰሃ ተነስቶ በአምላኩ ምህረት ከቆመ እኛም እናበረታው ዘንድ አብረነው እንድንቆም ያዛል። ንሰሃ በሚፈጥርበት ሃዘን ያለ ልክ እንዳይደቅ እግዚአብሄር ተመልሶ ስለሚያዝንለት በምህረት ያቀርበዋል፣ በመንፈሱም ያድሰዋል፤ በአዲስ መንፈስ እንዳይመላለስ ግን እኛ የድሮ ስፍራችን ቆመን የርሱን ሃዘን እንዳናበዛ ልክ የለሽ ሃዘን እንዳንጨምርበት ጠንቃቃ እንድንሆን ቃሉ ያስተምረናል።
ህዝ.4:11-16 “ውኃውንም በልክ የኢን መስፈሪያ ከስድስት እጅ አንድን እጅ ትጠጣለህ፥ በየጊዜው ትጠጣዋለህ። እንደ ገብስ እንጐቻም አድርገህ ትበላዋለህ፥ ከሰውም በሚወጣ ፋንድያ በፊታቸው ትጋግረዋለሁ። እግዚአብሔርም፦ እንዲሁ የእስራኤል ልጆች እነርሱን በምበትንባቸው በአሕዛብ መካከል ርኩስ እንጀራቸውን ይበላሉ አለ። እኔም፦ ጌታ እግዚአብሔር ሆይ፥ ወዮ! እነሆ፥ ሰውነቴ አልረከሰችም፤ ከታናሽነቴ ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ ጥንብና አውሬ የሰበረውን ከቶ አልበላሁም፥ ርኩስም ሥጋ በአፌ ውስጥ አልገባም አልሁ። እርሱም፦ እነሆ፥ በሰው ፋንድያ ፋንታ ኩበት ሰጥቼሃለሁ በእርሱም እንጀራህን ትጋግራለህ አለኝ። ደግሞም እንዲህ አለኝ፦ የሰው ልጅ ሆይ፥ የኢየሩሳሌምን እንጀራ በትር እሰብራለሁ፥ እየፈሩም እንጀራን በሚዛን ይበላሉ፥ እየደነገጡም ውኃን በልክ ይጠጣሉ፤”
እግዚአብሄር በቃ ሲል ሁሉ ነገር ያበቃል፤ አልበቃ የሚለው ግን የእኛ ፈቃድ ብቻ ነው፤ ይህም ከሰው ልጆች ታሪክ የምንወስደው ትምህርት ነው። አይበቃንም እንበል እንጂ፣ አናቆምም ብለንም እንሩጥ እንጂ ያንን በራሱ ሰአት የሚያደርግ የበላይ ገዢ አለ። በተለይ በእግዚአብሄር ፈቃድ ውስጥ እያለ የራሱን ፈቃድ የሚያስቀድመው እርሱ በእግዚአብሄር እንዲቆም የሚገደደው በብርቱ ክንድ መሆኑን ስናይ አስፈሪ ነው። መቼም ወዳጄ የተባለው ዘር እስራኤል እንደ አባቱ አብረሃም ፍጹም የተሰጠ ባለመሆኑ ያላየው መከራ አልነበረም።
ለምን ያ ሁሉ አስፈሪ ቅጣት ወረደበት? ህዝቡ ምን አደረገ? አምላኩስ ምን አደረገ? ይሄን ለይቶ ማወቅ ይገባል። እግዚአብሄር የእርኩስነታቸውን ከፍታ ለማሳየት በራሳቸው እዳሪ ጋግረህ አቀርብላቸው አለው፤ ሁኔታው ያሸማቀቀው ነቢዩ እግዚአብሄርን በመማጸን ሲለምነው እናያለን፡ እግዚአብሄር ግን ልካቸው እርሱ ነው አለው፣ እንደዚያ ባለ አጸያፊ ህይወት በእርሱ ዘንድ እየኖሩ እንደነበረ በዚያ ሲያመለክታቸው ያንን አዘዘ። እግዚአብሄር ነቢዩን ጠርቶ የኢየሩሳሌምን መመኪያ ያጠገባቸውን ትምክታቸውንም እሰብራለሁ ያኔ በሁሉ ነገር እጥረት ውስጥ ገብተው ከመታበይ ወደ መሸማቀቅ ላይ ይደርሳሉ፣ ከጥጋብ ወደ ሰቀቀን ይወርዳሉ፣ ጠግበው እግዚአብሄር ላይ በደል ሰርተዋልና ሲጠጡ በልኬት፣ ሲበሉም እንደ ውሰጣቸው ምኞት ሳይሆን ተለክቶና ተሳቀው ይበላሉ አለ።
• ልክ የሌለው ልቅ
በልክ ለመኖር አንዱ መንገድ የሚሆነው ልክ የለሾችና አጥፊዎችን ማወቅ ነው፤ ጠላቱን ያወቀ ከጠላቱ ጋር አይወዳጅም፣ ጠላቱ ሊያጠፋው ሊጎዳው ወይም ሊያሰናክለው አይደል ያደባው? ስለዚህ በልክና በገደብ እንድንኖር ስንመከር ጭቆና እንደሆነ አድርጎ የሚመሰክርልን ልቅ የሆነው የእኛነታችን ክፍል ራሱ ነው፤ እርሱ ደግሞ በስተመጨረሻ ለልክ የለሾች አሳልፎ ይሰጠናል፣ ለአመጻቸውም አሳልፎ ይሰጠናል፣ ለፈቃዳቸውም ጭምር አሳልፎ የሚሰትጥ ነው የሚሆነው፤ ከዚያ ምን እናተርፍ ይሆን? እነ ልክ-የለሽን ቀጥሎ እንመልከት፣ 1ኛ. በኢሳ.5:14 ላይ ያለው ቃል የሚያመለክተው ነገር አለ፦
“ሲኦልም ሆድዋን አስፍታለች፥ አፍዋንም ያለ ልክ ከፍታለች፤ ከበርቴዎቻቸውና አዛውንቶቻቸው ባለጠጎቻቸውም ደስተኞቻቸውም ወደ እርስዋ ይወርዳሉ።”
አቤት! የአፍዋ አከፋፈት? ስፋቱ ምን ያህል ነው፤ ያን በመንፈስ ያየው ንጉስ ሰሎሞን እንኳን ተገርሞ ያለ ልክ ይለዋል። ያለ ልክ የተከፈተ በር ጠርጎ እንዳያስገባ ምን ያግደዋል? መንገደኛው በእውነት አስቦበት ካልተጠነቀቀ ያለልክ በተከፈተው አፍ ውስጥ ላይገባ ምን ዋስትና እንዳለው እስቲ ያስብ። በምድር ላይ ያሉ ምንም ማድረግ የማይሳናቸው ከበርቴዎች ነበሩ፣ የተከፈተውን አፍ ግን ሊዘጉም ሆነ ሊያመልጡ ግን አልቻሉም፤ ደግሞም በምክራቸው የተመሰገኑ በጥበባቸው ብዙዎችን የሚያድኑ አዛውንቶችም ነበሩ፣ ግን በምክራቸው ብዛት ሊያመልጡዋት አልቻሉም፤ ባለጠጎም እንዲሁ፣ በብልጥግናቸው ብዛት በገንዘብ ሰፍረው ሰራዊት መግዛትና አፍዋን መጠበቅ እንዴት ይቻላቸው? ያለልክ የተከፈተው አፍዋ ማንም አያመልጠውምና።
2ኛ. ሃስ.26:12፦
“…እኔም ራሴ የናዝሬቱን የኢየሱስን ስም የሚቃወም እጅግ ነገር አደርግ ዘንድ እንዲገባኝ ይመስለኝ ነበር። ይህንም ደግሞ በኢየሩሳሌም አደረግሁት፤ ከካህናት አለቆችም ሥልጣን ተቀብዬ እኔ ከቅዱሳን ብዙዎችን በወኅኒ አሳሰርኋቸው፥ ሲገድሉአቸውም አብሬ ተቸሁ። በምኵራብም ሁሉ ብዙ ጊዜ እየቀጣሁ ይሰድቡት ዘንድ ግድ አልኋቸው፤ ያለ ልክ ስቈጣባቸውም እስከ ውጭ አገር ከተማዎች ድረስ እንኳ አሳድድ ነበር።”
አንድ ልክ የለሽ አካሄድ ደግሞ በዚህ ጥቅስ ውስጥ እናያለን፤ ቁጣና እልክ፣ ቅናትና በቀል ወሰን አላቸው፣ ቢያንስ ማድረግ የሚፈልጉትን እስኪያደርጉ ያልያም መበቀል የፈለጉትን እስኪበቀሉ በዚያ መንፈስ መንቀሳቀስ ይኖራል። ግን እንቅስቃሴው ያለልክ ከሆነ መቆሚያው የት እንደሆነ ሲያስቡት ያስፈራል፤ ያውም ቅዱሳንን በማሳደድ ላይ የወደቀ ልክ የለሽነት እንዴት ያለ ክፉ ነገር ነው? የቀድሞው ሳኦል አዲሱ ሰው ጳውሎስ ህይወቱ ይገርማል፤ ከእጅግ ክፉ ሰውነት ወደ እጅግ ሩህሩነት የተለወጠበት መንገድ ስናይ የእግዚአብሄርን የምህረት ጉልበት እናስተውልበታለን።
3ኛ. ሮሜ.7:13፦
“እንግዲህ በጎ የሆነው ነገር ለእኔ ሞት ሆነብኝን? አይደለም፥ ነገር ግን ኃጢአት ሆነ፤ ኃጢአትም በትእዛዝ ምክንያት ያለ ልክ ኃጢአተኛ ይሆን ዘንድ፥ ኃጢአትም እንዲሆን ይገለጥ ዘንድ በጎ በሆነው ነገር ለእኔ ሞትን ይሠራ ነበር።”
ከላይ ያለው ቃል የኃጢአትን ልክ የለሽነት የሚያሳይ ነው፤ ኃጢአት ሲበክልም ሆነ ሲተላለፍ ልክ የለውም፤ ወይም ማቆምያ የለውም። ቃሉን ተላላፊ ያግኝ እንጂ፣ ትእዛዝን የሚጥስ ይገኝ እንጂ ሃይ ባይ የሚገድበው ወይም በቃህ የሚለው ሰብአዊ ሃይል፣ ብልሃትም ሆነ አሰራር የለም። ትእዛዝ/ህግ በምንም መንገድ ኃጢአት አይወልድም፣ ግን እያንዳንዱን የኃጢአት ስራ እያጋለጠ፣ የሚሹለከለክን አመጸኛ እንዳስቸገረ በግልጽ ይታያል። የእያንዳንዱ የኃጢአት ምንነት በህጉ ምክኒያት ግልጥ ሆኖአል። እስራኤል መፍራት የነበረባቸው ስራቸውን እንጂ ህጉን መሆን አልነበረበትም። የእግዚአብሄርን ትእዛዝ ጠባይ ይሄው ሃዋርያ በዚያው ስፍራ ሲያብራራው እናያለን፦
ሮሜ. 7:14-18 “ሕግ መንፈሳዊ እንደ ሆነ እናውቃለንና፤ እኔ ግን ከኃጢአት በታች ልሆን የተሸጥሁ የሥጋ ነኝ። የማደርገውን አላውቅምና፤ የምጠላውን ያን አደርጋለሁና ዳሩ ግን የምወደውን እርሱን አላደርገውም። የማልወደውን ግን የማደርግ ከሆንሁ ሕግ መልካም እንደ ሆነ እመሰክራለሁ። እንደዚህ ከሆነ ያን የማደርገው አሁን እኔ አይደለሁም፥ በእኔ የሚያድር ኃጢአት ነው እንጂ። በእኔ ማለት በሥጋዬ በጎ ነገር እንዳይኖር አውቃለሁና፤ ፈቃድ አለኝና፥ መልካሙን ግን ማድረግ የለኝም።”
“ከኃጢአት በታች ልሆን የተሸጥሁ የሥጋ ነኝ” ብዬ በባርነት እንዳለሁ ካወቅኩ እንዲሁም ልክ በሌለው የኃጢአት ሃይል እንደተገዛሁ ከመሰከርኩ ባርያ እንደሆንኩ የማላምነው ለምንድነው? ባርነቱን ያለመፈለግና ለሃጢያት መገዛትን መጸየፍ አንድ ነገር ቢሆንም እውነቱ ግን ህይወታችንን ያንበረከከ ሃይል ያለ ልክ እንደፈለገው ሊሰለጥንብን ጉልበት እንዳለው ማስተዋል ተገቢ ነው።
4ኛ. 2ቆሮ. 1:8፦
“በእስያ ስለ ደረሰብን መከራችን፥ ወንድሞች ሆይ፥ ታውቁ ዘንድ እንወዳለንና፤ ስለ ሕይወታችን እንኳ ተስፋ እስክንቆርጥ ድረስ ከዓቅማችን በላይ ያለ ልክ ከብዶብን ነበር”
እግዚአብሄር አቅማችንን የሚያውቅ አምላክ ነው፤ በህይወታችን ለሚመጣው ፈተና እንኩዋን ገደብ አበጅቶለት መጠኑን አልፎ እንዳይሰብረን ያስቆመዋል።
አገልጋዮቹ ሃዋርያት ግን ኢየሱስ የሚጠጣውን የመስዋእት ጽዋ ለመጠጣት እንኩዋን በራሳቸው የማሉ ስለነበሩ በነርሱ ላይ የሆነው እጅግ ከባድ ነበር፤ በሰው ሃይል መቁዋቁውም አይቻልም ነበር፤ መከራው ድርብርብ፣ ጥልቅ፣ ረጅም ነበርና ገደብ የለሽ ይመስል ነበር።
5ኛ. ገላ.1:14-15-
“በአይሁድ ሥርዓት በፊት እንዴት እንደ ኖርሁ ሰምታችኋልና፤ የእግዚአብሔርን ቤተ ክርስቲያን ያለ ልክ አሳድድና አጠፋ ነበር፥ ለአባቶችም ወግ ከመጠን ይልቅ እየቀናሁ በወገኔ ዘንድ በዘመኔ ካሉት ብዙዎችን በአይሁድ ሥርዓት እበልጥ ነበር። ነገር ግን በእናቴ ማኅፀን ሳለሁ የለየኝ በጸጋውም የጠራኝ እግዚአብሔር በአሕዛብ መካከል ስለ እርሱ ወንጌልን እሰብክ ዘንድ ልጁን በእኔ ሁኔታ ሊገልጥ በወደደ ጊዜ፥ ወዲያው ከሥጋና ከደም ጋር አልተማከርሁም፥ ከእኔም በፊት ሐዋርያት ወደ ነበሩት ወደ ኢየሩሳሌም አልወጣሁም፥ ነገር ግን ወደ ዓረብ አገር ሄድሁ እንደ ገናም ወደ ደማስቆ ተመለስሁ። ከዚህ ወዲያ ከሦስት ዓመት በኋላ ኬፋን ልጠይቅ ወደ ኢየሩሳሌም ወጥቼ ከእርሱ ጋር አሥራ አምስት ቀን ሰነበትሁ፤ ነገር ግን ከጌታ ወንድም ከያዕቆብ በቀር ከሐዋርያት ሌላ አላየሁም። ስለምፅፍላችሁም ነገር፥ እነሆ፥ በእግዚአብሔር ፊት ሐሰት አልናገርም። ከዚያ ወዲያ ወደ ሶርያና ወደ ኪልቅያ አገር መጣሁ። በክርስቶስም ያሉት የይሁዳ ማኅበሮች ፊቴን አያውቁም ነበር፤ ነገር ግን፦ ቀድሞ እኛን ያሳድድ የነበረ፥ እርሱ በፊት ያጠፋው የነበረውን ሃይማኖት አሁን ይሰብካል ተብሎ ሲነገር ይሰሙ ነበር፤ ስለ እኔም እግዚአብሔርን ያከብሩ ነበር።”
ከመጠን ያለፈ ሰው ከሚሰራውም ያለፈ ክፋት ውስጥ ሳለን መሃሪው አምላክ ጠራን፣ ወደ እርሱም አቅርቦ በምህረት ስፍራው አስቀመጠን። ሃዋርያው አገልጋይ ከመሆኑ በፊት ያለ ልክ አገልጋዮችን ተቸ፣ አሳደደ፣ አስገደለ፤ እርሱ ክርስቲያን ከመሆኑና ሰው ወዳድ ከመሆኑ በፊት ክርስቲያኖችን የሚጠላ ነበረ። ልክ በሌለው ጥፋት ውስጥ የነበሩትን ልክ በሌለው ምህረት ይቅር ብሎ ልክ የሌለውን ጸጋውን የሚሰጥ አምላክ ይባረክ።
2ቆሮ.10:12-13 “ራሳቸውን ከሚያመሰግኑ ከአንዳንዶች ጋር ራሳችንን ልንቆጥር ወይም ራሳችንን ልናስተያይ አንደፍርምና፤ ነገር ግን እነርሱ ራሳቸውን ከራሳቸው ጋር ሲያመዛዝኑ፥ ራሳቸውንም ከራሳቸው ጋር ሲያስተያዩ፥ አያስተውሉም። እኛ ግን እግዚአብሔር እንደ ወሰነልን እስከ እናንተ እንኳ እንደሚደርስ እንደ ክፍላችን ልክ እንጂ ያለ ልክ አንመካም።”
የክርስትና ውበቱ አዲስ ፍጥረት ማድረጉ፤ ሰው ግን በተፈጥሮው ሁሉን በራሱ መጠቅለል ይወዳል። በቤተክርስቲያን ስራ በጌታ ጸጋ የሚሆንና የሆነውን ይህን መረዳት እርስ በርስ ከመለካካት ያድናል። በቤቱ የሆነው በራሳችን የሆነ ነገር ካልሆነ በራሳችን ባልሆነ ነገር የኔ የኔ የሚያሰኝ ነገር ስጋዊ ነው ማለት ነው። ይህን አካሄድ ማስወገድ እንዲገባ ሃዋርያው ያሳስባል። ጸጋ ልክ የለውም እኛ ግን በልክ የተፈጠርን ነንና ተለጥጠን እንዳንፈነዳ ልካችንን ማወቅ አለብን፤ የጸሎት ጸጋ አለህ? ባንተ እየሰራ ያለው ጸጋ ከልክህ በላይ አይሄድም፣ በእርግጥ አነተ ራስህ ከስሪትህ በላይ አትሄድምና ባንተ ውስጥ ያለው የጸጋ መንፈስ እስከሄድክበት ድረስ በሃይል ያስኬድሃል።
2ቆሮ.10:14 “ወደ እናንተ እንደማንደርስ አድርገን ከመጠን አናልፍምና፥ የክርስቶስን ወንጌል በመስበክ እስከ እናንተ እንኳ ደርሰናልና፤ በሌሎች ድካም ያለ ልክ አንመካም፥ ነገር ግን እምነታችሁ ሲያድግ ከእናንተ ወዲያ ባለው አገር እስክንሰብክ ሥራችንን እየጨመርን፥ በክፍላችን በእናንተ ዘንድ እንድንከብር ተስፋ እናደርጋለን፤ በሌላው ክፍል ስለ ተዘጋጀው ነገር አንመካም። የሚመካ ግን በጌታ ይመካ፤ እግዚአብሔር የሚያመሰግነው እንጂ ራሱን የሚያመሰግን እርሱ ተፈትኖ የሚወጣ አይደለምና።”
ሰው እግዚአብሄርን የሚያገለግለው እግዚአብሄር በወሰነለት መንገድ፣ ሁኔታና ጊዜ ነው። ያገለግል ዘንድም በጸጋው ይደግፈዋል። አገልግሎትን በተመለከተ የሚያገለግሉት በአንድ መንገድና ጸጋ እንዲሆን መጠበቅ የለብንም። እያንዳንዱ እኩል መንፈሳዊ ልኬት የለውም፣ ጸጋውን የሚያንቀሳቅስበት ሰው መንፈሳዊ ቁመና አንድ አይደለምና። ማድረግ ያለበት እንደተሰጠውና እንደቻለው መዘርጋት ነው። እንደሌላው ሳይሆን እንደራሱ፣ ሌላው እንዳለው ሳይሆን ራሱ እንደተቀበለው ነው። የሰው መለኪያ ምንም መልካም አያደርግም። አንዳንድ ሰዎች ግን የተሰጣቸውን ሳይሆን ለሌሎች የተሰጠውን ያያሉ፣ ያን ለመምሰልም ይጣጣራሉ። ሰባኪዎች እሱን ለመምሰል ሞዴል የሚሆናቸውን ሌላ ሰባኪ ከተከተሉ ይሳሳታሉ። መስሎ ማገልገል ሳይሆን ሆኖ እንደተቀበሉት ማገልገል ነው ምስጋና ያለው። ጳውሎስን አንዳንድ ሰዎች መጥተው በሰው መለኪያ ሊመዝኑት ሲሞክሩ ይገስጻቸዋል። ስብከቱን አይተው፣ ደብድቤውን አንብበውና ቁመናውን ተመልክተው አንድ መለኪያ ላይ አስቀመጡት፣ ያም ሰዋዊ መለኪያ ስለነበረ ጥቅም አልነበረውም። ስለዚህ በናንተ መለኪያ ውስጥ አልገባም በዚያ አልመካምም አላቸው። የሚመካ ግን ጸጋን በሚሰጥ ጌታ ይመካ፣ የሚመካ ቢኖር ግን ሳይነቅፍ ከደካሞች ጋር በሚሰራው አምላክ ይመካ።
• ያለ ልክ የተፈቀደ መንገድ አለ
ለእግዚአብሄር በሆነ ነገር ልክ አልተተመነልንም፣ አልተወሰነም፣ አይቆጠብም፤ ምክኒያቱም ወሰን ለሌለው አምላክ የሚሆን ነውና።
አምልኮአችን ገደብ የማይኖረው ብዙ ምክኒያት አለው፣ በዋናነት ግን የእግዚአብሄር ማንነትና የእኛ ማንነት ሁኔታ ነው። አምላካችን እግዚአብሄር የአማልክት አምላክና የጌቶች ጌታ ነው፤ ሰማይና ሰማያት ይይዙት ዘንድ አይችሉም፣ ሰማይና ምድርን የሞላ አምላክ ነው፣ ሁሉን የሚያይ ሁሉን የሚያውቅም ነው። ስለዚህ ይህ ታላቅ አምላክ እንደምን ሊመለክ ይገባዋል? ሰዎች ግን ታናሾች ነን፤ ደካሞች ነን፤ ሟች ነን፤ ውስን ነን፤ ሁሉን አናውቅም፤ በሁሉ ስፍራ አንገኝም፤ ራሳችንን ማዳን አንችልም። እግዚአብሄር የሚያድነን ስለሆነ ግን ሊመሰገን ይገባዋል፤ አጋንንታዊ ሃይላት ጠላቶቻችንና በስጋ ጉልበት ልንታገላቸው የማንችል ሲሆን እርሱ ግን ከነርሱ ታዳጊያችንና ደህንነታችን ነውና ስለዚህ እናመልከዋለን፤ እርሱ ህይወት ሰጪያችን ነው፣ ስለዚህም እናመልከዋለን፤ ምስጋናውም ብዙ ነው ወሰን የሌለው ነው። መላእክት ያለማቁዋረጥ ያመልኩታል፣ ይገዙለታል፣ ያለምንም ምርጫ ለአምላካቸው ብቻ ተገዢ ናቸው፤ የሰው ልጅም ታዛዥ ሲሆንና መንፈሳዊ መረዳት ውስጥ ሲገባ ፈጣሪውን በሙሉ ሃይሉ ያመልከዋል።
እዝ.7:21-23 “እኔም ንጉሡ አርጤክስስ በወንዝ ማዶ ላሉት በጅሮንዶች ሁሉ ይህን ትእዛዝ ሰጥቻለሁ። የሰማይ አምላክ ሕግ ጸሐፊ ካህኑ ዕዝራ ከእናንተ የሚፈልገውን ሁሉ አዘጋጁለት፤ እስከ መቶ መክሊት ብርም ቢሆን፥ እስከ መቶ የቆሬስ መስፈሪያ ስንዴ፥ እስከ መቶም የባዶስ መስፈሪያ የወይን ጠጅ፥ እስከ መቶም የባዶስ መስፈሪያ ዘይት ቢሆን፥ ጨውም ያለ ልክ ቢሆን ስጡ። በንጉሡና በልጆቹ መንግሥት ላይ ቍጣ እንዳይሆን፥ የሰማይ አምላክ ያዘዘው ሁሉ ለሰማይ አምላክ ቤት በሙሉ ይደረግ።”
እግዚአብሄር ለራሱ ክብር የሚሆን ሰው ከየትም ማስነሳት የሚችል አምላክ ነው፤ እግዚአብሄር በኢየሩሳሌም ዳግም ይመለክ ዘንድ የአህዛብ ንጉስን ልብ ሲያንቀሳቅስ ንጉሱ ባለው ነገር ላይ ያለ ልክ ስጦታ እንዲቀርብ ሲያዝ ይታያል። ለእግዚአብሄር ባለን ነገር ያለልክ ማቅረብ በረከቱን ምህረቱን እንዲያበዛ ያደርጋል። በአዲስ ኪዳን ያሉ አማኞችም በስጋ ለተገለጠው ለእስራኤል አምላክ በእውቀትና በእምነት የሚሆን ከፍ ያለ አምልኮ ምስጋና አገልግሎት ይሰጡት ዘንድ ይገባል።
ኤፌ.4:14 “ሁላችን የእግዚአብሔርን ልጅ በማመንና በማወቅ ወደሚገኝ አንድነት፥ ሙሉ ሰውም ወደ መሆን፥ የክርስቶስም ሙላቱ ወደሚሆን ወደ ሙላቱ ልክ እስክንደርስ ድረስ፥ ቅዱሳን አገልግሎትን ለመሥራትና ለክርስቶስ አካል ሕንጻ ፍጹማን ይሆኑ ዘንድ።”
የእግዚአብሄር አምልኮ ተቀጣጥሎ ወደ አርያም እስኪደርስ ድረስ አምልኮ አያቋርጥም፣ የእግዚአብሄር ክብር ወርዶ የክብሩን ቤት እስኪሞላ፣ መንፈሱ ወርዶም ህዝቡ እስኪለወጥ አይቋረጥም። የእኛ ልብም እሱን መፈለግ አያቋረጥ፣ ያኔ የርሱ ምህረት በብዙ ቸርነት ይገለጣል።