የህይወታችን መሰርት ጌታ ኢየሱስ ነው፣ ደግሞም የመንፈሳዊ ህይወታችን እድገት ልክም ነው፤ ወደዚያ ልክ ለመድረስ ሁሌም እየተሰራን እስከ ፍጻሜ እንጓዋዛለን። ወደ እርሱ ሙላት እንዘረጋለን እንጂ ሙላቱን የሚፈጽመው እርሱ ራሱ ነው። የጀርባ ታሪካችን የሚያውቅ፣ ልካችንና መድረሻችን የሚያይ አምላክ ትክክለኛው ደረጃ እስክንደርስ በመንፈሱ እየሰራ በጸጋው እየደገፈና እያስተካከለ ያኖረናል። የቃሉ ውሃ-ልክ የእኛን መንፈሳዊ ሚዛን የሚያስተካክልና ወደ ልኩ የሚወስድ ብቸኛው መመሪያችን መሆን አለበት። ማንም ከቃሉ ልቆ መገኘት አይችልም፤ ስለዚህ ራሱን በቃሉ መፈተሽ ለልከኝነቱ ማረጋገጫ ይሆነዋል።
እግዚአብሄር ልክ አብጅቶልናል፤ በመንፈሳዊውም በዚህ አለም ኑሮም ቢሆን። ለመንፈሳዊነታችን የምንሰማው፣ የምንመለከተው፣ ተስበንና ተራምደንም መድረስ ያለብን ልክ ያ ቃሉ የሚያመለክተን የልክ አይነት ነው ማለት ነው። በስጋችን በምድር ላይ የምንኖረው ህይወት መንፈሳዊ ህይወትን በእጅጉ ይጫነዋል። ስለዚህ የአንዱ ወደ ልክ መድረስ ለሌላኛው ልከኝነት ጠቃሚ መንገድ እንደሚከፍት ይታያል ማለት ነው፦
1ጴጥ.4:12-14 “ማንም ሰው የሚናገር ቢሆን፥ እንደ እግዚአብሔር ቃል ይናገር፤ የሚያገለግልም ቢሆን፥ እግዚአብሔር በሚሰጠኝ ኃይል ነው ብሎ ያገልግል፤ ክብርና ሥልጣን እስከ ዘላለም ድረስ ለእርሱ በሚሆነው በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል እግዚአብሔር በነገር ሁሉ ይከብር ዘንድ፤ አሜን። ወዳጆች ሆይ፥ በእናንተ መካከል እንደ እሳት ሊፈትናችሁ ስለሚሆነው መከራ ድንቅ ነገር እንደ መጣባችሁ አትደነቁ፤ ነገር ግን ክብሩ ሲገለጥ ደግሞ ሐሤት እያደረጋችሁ ደስ እንዲላችሁ፥ በክርስቶስ መከራ በምትካፈሉበት ልክ ደስ ይበላችሁ።”
የሰባኪ፣ የአስተማሪም ሆነ የእግዚአብሄርን ቃል ተናጋሪ ልኩ የእግዚአብሄር ቃል ብቻ ነውና ሲናገር ቃሉን ብቻ ለማስተላለፍ መሆን ይገባዋል ማለት ነው፤ እግዚአብሄርን የሚያገለግልም አገልግሎቱ እንደ እግዚአብሄር ቃል ሊሆን የግድ ነው። በርሱ ልክ ውስጥ ለሚጓዝ የሚያገኘው መከራ እንኩዋን በክርስቶስ መከራ ልክ ውስጥ ያለ በመሆኑ ሃዘን ወይም ትካዜ ሳይሆን ደስታ ሊሰማው እንዲገባው ቃሉ ቀድሞ ይናገራል።
ልከኝነታችንን ስንፈላልግ ከቃሉ ብዙ የምንማራቸው መንገዶች አሉ፣ ከነርሱ ጥቂቶቹ የሚከተሉትን ይመስላሉ፦
• የአሰማም ልክ
የአሰማም ልክ ወደ ጆሮ የሚደርሰውን የነገር መጠን ይወስናል፣ ይገድባል፤ ጆሮ ክዳን የለው ግን እንዴት? ስለአሰማም ስንነጋገር አሰማማችን እስከምን ድረስ ይሁን፣ ደግሞ ምንስ እንስማ? መልሱ የአሰማማችንን ልክ የሚፈልግ ነው የሚሆነው፤ ስንሰማ መስማት ያለብን የተፈቀደልን ነገር ሲሆን ተገቢ የሚሆነውም የሰማነው ነገር ውስጣችን ገብቶ እስኪዋሃደን ድረስ ነው። ቃሉን ከሰማን የሰማነው ቃል ህይወት የሚሆነው እስከ ነፍስ ድረስ ዘልቆ በመግባት እንዲሰራ ከፈቀድን ብቻ ነው፤ ቃሉ የማድረግ ችሎታ ቢኖረውም ለመለወጥ ግን የኛን ፈቃድ ይፈለጋል፦
እብ.4:2 “ለእነዚያ ደግሞ እንደ ተነገረ ለእኛ የምስራች ተሰብኮልናልና፤ ዳሩ ግን የሰሙት ቃል ከሰሚዎቹ ጋር በእምነት ስላልተዋሐደ አልጠቀማቸውም።”
እግዚአብሄር ባለማዳላት አስቀድሞ ለአይሁድ ነግሮ የነበረውን ወንጌል ለእኛ ለአህዛብም በእኩል ደረጃ ነግሮናል፤ ግን መነገር ተነግሮ ነበር፣ መስማትንም እኛም ሰምተን ነበር፣ ዳሩ ግን የተሰበከው የምስራች ቃል ወደ ውስጣችን እስከምን ድረስ ገብቶ ስራውን በህይወታችን ሰራ? ጥያቄው መለወጣችንን የመረምራል፤ የተሰበከልን እስከ ውስጥ ማንነታችን ዘልቆ እኛን ካልለወጠና ካልሰራን በቃሉ ጸጋ አልተጥቀምንምና። የሰማነውን ቃል በእምነት አሜን ብለን እንያዝ፤ በእኛ ከኖረ መስራት ይጀምራል።
ምን መስማት እንዳለብን ሲናገር መስማትም በእግዚአብሄር ቃል ነው ይላል፣ የህይወታችን ልክ በእርሱ ብቻ የሚለካና የሚስተካከል ነውና። ቃሉ ተራ ድምጽና ንግግር፣ የሰዎች አሳብ ማስተላለፊያ ዲስኩር ወይም የሰዎችን አሳብ መግለጫ እውቀት አይደለም፤ የእግዚአብሄር አፍ የሚናገረው የእርሱ አላማ መግለጫ የድምጹ ቃላዊ መልክት ነው፣ ቃሉ ሃይል የተሞላ ነው፣ አለማትን የመፍጠር ጉልበቱን አሳይቶአል፣ ከእግዚአብሄር አፍ ወጥቶአልና። ማንም ከቃሉ መንፈስ ንቅንቅ ማለት አይችልም፣ የተገለጠውን የእግዚአብሄር አሳብ መለወጥም አይችልም። ስለዚህ ይህን አውቆና ሁሌም የቃሉ አሳብ ለጥቅም እንደሆነ አምኖ መቀበል ውጤቱን በቃሉ ልክ ያመጣል።
እንዲሁም የአሰማማችን ልክ የት ድረስ ነው የሚለውን ከማወቅ አስቀድሞ አሰማማችንን የሚስወስነውን የህይወታችንን ልክ እንመልከትና ጉድለትን በጸጋው መሙላት ወደሚችለው ጌታ ዞር እንበል፣ ሌላ ይተሻለ አማራጭ የለም፤ ስለ እኛ በማር.4:2-8 ላይ እንዲህ ተጽፎአል፦
“በምሳሌም ብዙ ያስተምራቸው ነበር፥ በትምህርቱም አላቸው። ስሙ፦ እነሆ፥ ዘሪ ሊዘራ ወጣ። ሲዘራም አንዳንዱ በመንገድ ዳር ወደቀና ወፎች መጥተው በሉት። ሌላውም ብዙ መሬት በሌለበት በጭንጫ ላይ ወደቀና ጥልቅ መሬት ስላልነበረው ወዲያው በቀለ፤ ፀሐይም ሲወጣ ጠወለገ፥ ሥርም ስላልነበረው ደረቀ። ሌላውም በእሾህ መካከል ወደቀ፥ እሾህም ወጣና አነቀው፥ ፍሬም አልሰጠም። ሌላውም በመልካም መሬት ላይ ወደቀና ወጥቶ አድጎ ፍሬ ሰጠ፥ አንዱም ሠላሳ አንዱም ስድሳ አንዱም መቶ አፈራ። የሚሰማ ጆሮ ያለው ይስማ አለ።”
ዋናው ነገር ዘሪውን ልብ አልን ወይ? ዘሩን አስተዋልንስ? ዘሩ ያረፈው ማንስ ላይ እንደሆነ የኛስ ህይወት ከየትኛው እንደሚመደብ ደግሞ አወቅን? የአሰማማችን ልክ በመዘግየትና በመፍጠን አማራጮች የታጀበ እንደሆነም ቀጥሎ ያለው ቃል ያስረዳል፦
“ስለዚህ፥ የተወደዳችሁ ወንድሞቼ ሆይ፥ ሰው ሁሉ ለመስማት የፈጠነ ለመናገርም የዘገየ ለቍጣም የዘገየ ይሁን፤ የሰው ቍጣ የእግዚአብሔርን ጽድቅ አይሠራምና። ስለዚህ ርኵሰትን ሁሉ የክፋትንም ትርፍ አስወግዳችሁ፥ ነፍሳችሁን ማዳን የሚችለውን በውስጣችሁም የተተከለውን ቃል በየዋህነት ተቀበሉ። ቃሉን የምታደርጉ ሁኑ እንጂ ራሳችሁን እያሳታችሁ የምትሰሙ ብቻ አትሁኑ።ቃሉን የሚሰማ የማያደርገውም ቢኖር የተፈጥሮ ፊቱን በመስተዋት የሚያይን ሰው ይመስላል፤ራሱን አይቶ ይሄዳልና፥ ወዲያውም እንደ ምን እንደ ሆነ ይረሳል። ነገር ግን ነጻ የሚያወጣውን ፍጹሙን ሕግ ተመልክቶ የሚጸናበት፥ ሥራንም የሚሠራ እንጂ ሰምቶ የሚረሳ ያልሆነው፥ በሥራው የተባረከ ይሆናል። አንደበቱን ሳይገታ ልቡን እያሳተ እግዚአብሔርን የሚያመልክ የሚመስለው ማንም ቢኖር የእርሱ አምልኮ ከንቱ ነው። ንጹሕ የሆነ ነውርም የሌለበት አምልኮ በእግዚአብሔር አብ ዘንድ ይህ ነው፤ ወላጆች የሌላቸውን ልጆች ባልቴቶችንም በመከራቸው መጠየቅ፥ በዓለምም ከሚገኝ እድፍ ሰውነቱን መጠበቅ ነው።” (ያእ.1:22-27)
• የአተያይ ልክ
አሰማምና አተያይ ላይ ማተኮራችን ለመዳናችን መንገድ መክፈታችን ነው፤ በየትኛውም የህይወት ደረጃ እንኑር ይህ የህይወት መርህ የግድ የሚያስፈልገን ነው። በቀን በቀን በሰአት በሰአት ከዚያም በታች ባለ የጊዜ ድቃቂ ወደ ቃሉ ብናተኩር በዚያው ልክ እየተባረክን፣ መዳን ካለብን ነገር እየዳንንና ወደ እርሱ እየቀረብን እንሄዳለን። እግዚአብሄር ለአብረሃም ውርሱን ከማስረከቡ በፊት እይታውን አስፍቶ የሚወርሰውን ልክ እንዲመለከት አዘዘው፤ የውጤታችን ስፋት የራእያችን ልክ በመሆኑ በስፋትና በርዝመት ይመለከት ዘንድ ቀና ማለት እንደሚገባ አሳሰበው፤ አብረሃምም እስከሩቅ ምድር ድረስ ( እስከ እይታው ልክ ድረስ) ትመለከተ፣ እንዳየውም ልክ ዘሩ ያንን ሊወርስ ቻለ፦
ዘፍ.13:14-17 “ሎጥ ከተለየው በኋላም እግዚአብሔር አብራምን አለው፦ ዓይንህን አንሣና አንተ ካለህበት ስፍራ ወደ ሰሜንና ወደ ደቡብ ወደ ምሥራቅና ወደ ምዕራብ እይ፤ የምታያትን ምድር ሁሉ ለአንተና ለዘርህ ለዘላለም እሰጣለሁና። ዘርህንም እንደ ምድር አሸዋ አደርጋለሁ፤ የምድርን አሸዋን ይቈጥር ዘንድ የሚችል ሰው ቢኖር ዘርህ ደግሞ ይቈጠራል። ተነሣ በምድር በርዝመትዋም በስፋትዋም ሂድ እርስዋን ለአንተ እሰጣለሁና።” በማለት አብረሃም የሚያየው የሚወርሰው ልኩ እንደሆነ አመለከተው።
ሆኖም ትኩረታችንን የሚወስዱና እግዚአብሄር ካሳየን ነገር ላይ አይናችንን እንድናነሳ የሚያዘናጉ የአጋንንት ጣልቃ ገብነቶች ስላሉ ጥንቃቄ ማድረግ ይፈልጋል።
• የአኗኗር ልክ
የእግዚአብሄር ህዝብ የህይወት መሰረት ክርስቶስ ነው፤ ህዝቡ ይህን ህይወት ሲኖረው እንደ እግዚአብሄር ፈቃድ መሆን አለበት። ህይወቱ በስጋ ፈቃድ ተጽእኖ ስር እንዳይሆንም በእግዚአብሄር ምሪት ስር ሊሆን ተገቢ ነው። ይህ እንዲህ ከሆነ እኗኗሩስ እንዴት መሆን አለበት?
2ጴጥ. 3:11-12 “ይህ ሁሉ እንዲህ የሚቀልጥ ከሆነ፥ የእግዚአብሔርን ቀን መምጣት እየጠበቃችሁና እያስቸኰላችሁ፥ በቅዱስ ኑሮ እግዚአብሔርንም በመምሰል እንደ ምን ልትሆኑ ይገባችኋል? ስለዚያ ቀን ሰማያት ተቃጥለው ይቀልጣሉ የሰማይም ፍጥረት በትልቅ ትኵሳት ይፈታል”
የእግዚአብሄር ቃል በምንኖርበት ዘመን መኖር ከቻልን መሆን ያለበት በቅዱስ ኑሮ እግዚአብሔርንም በመምሰል እንዲሆን ያመለክታል። ይህም ኑሮ የመንፈስ ኑሮ ነው።
ሮሜ.7:6 “አሁን ግን ለእርሱ ለታሰርንበት ስለ ሞትን፥ ከሕግ ተፈትተናል፥ ስለዚህም በአዲሱ በመንፈስ ኑሮ እንገዛለን እንጂ በአሮጌው በፊደል ኑሮ አይደለም።”
አማኝ በመንፈስ ኑሮ ተገዝተው መኖር የሚችሉት ቃሉ ከክርስቶስ ጋር ተሰቅዬአለሁ የሚለውን ትልቅ የህይወት ለውጥ አሰራር ሲያስተውሉ ነው። በመንፈስ መኖርን የሚያስችል የክርስቶስ በእኛ መኖር እንደሆነ ቃሉ ያስተምረናል፤ በገላ.2:20 ይህን ሲናገር፦ “ከክርስቶስ ጋር ተሰቅዬአለሁ፤ እኔም አሁን ሕያው ሆኜ አልኖርም ክርስቶስ ግን በእኔ ይኖራል፤ አሁንም በሥጋ የምኖርበት ኑሮ በወደደኝና ስለ እኔ ራሱን በሰጠው በእግዚአብሔር ልጅ ላይ ባለ እምነት የምኖረው ነው።” ይላል። በአዲስ ልደት የተገፈፈው አሮጌው ሰው እንዳይመለስ፣ አዲሱ ሰው ግን የበረታ እንዲሆን የጌታችን እውነት በኛ ላይ መግዛት ይኖርበታል፣ እውነቱ አእምሮን መምራት፣ መግዛት ማሰልጠንና መንፈሳዊ ማድረግ ይችላልና።
ኢፌ.4:21-23″በእርግጥ ሰምታችሁታልና፥ እውነትም በኢየሱስ እንዳለ በእርሱ ተምራችኋል፤ ፊተኛ ኑሮአችሁን እያሰባችሁ እንደሚያታልል ምኞት የሚጠፋውን አሮጌውን ሰው አስወግዱ፥ በአእምሮአችሁም መንፈስ ታደሱ”
የመንፈስ ኑር የተገለጠ ባህሪ አለው፣ይህን ባህሪውን ቃሉ ቅድስናና ጽድቅ ነቀፋም የሌለበት ኑሮ ይለዋል። የወንጌል ሰባኪዎች ከጌታም ስልጣኑን የተቀበሉ ሃዋርያቶች ስለዚህ ህይወት ባህሪና በእነርሱ ህይወት መገለጡን በማብራራት የኛም አካሄድ ያን እንዲይዝ ያሳስቡናል፦
1ተሰ.2:10-12″በእናንተ በምታምኑ ዘንድ በእንዴት ያለ ቅድስናና ጽድቅ ነቀፋም በሌለበት ኑሮ እንደ ሄድን፥ እናንተና እግዚአብሔር ምስክሮች ናችሁ፤ ወደ መንግሥቱ ወደ ክብሩም ለጠራችሁ ለእግዚአብሔር እንደሚገባ ትመላለሱ ዘንድ እየመከርንና እያጸናን እየመሰከርንላችሁም፥ አባት ለልጆቹ እንደሚሆን ለእያንዳንዳችሁ እንደ ሆንን ታውቃላችሁና።”
ሃዋርያው ስለመንፈስ ኑሮአቸው ክርስቲያኖቹን እራሳቸውንና የላካቸውን እግዚአብሔር ምስክሮች እስኪያደርግ የደፈረው በሃዋርያቱ ይሰራ የነበረው ጌታ በሙላት በነርሱ ሲሰራ ስለነበረ ነው።
1ጴጥ.1:15-16 “ዳሩ ግን፦ እኔ ቅዱስ ነኝና ቅዱሳን ሁኑ ተብሎ ስለ ተጻፈ የጠራችሁ ቅዱስ እንደ ሆነ እናንተ ደግሞ በኑሮአችሁ ሁሉ ቅዱሳን ሁኑ።ዳሩ ግን፦ እኔ ቅዱስ ነኝና ቅዱሳን ሁኑ ተብሎ ስለ ተጻፈ የጠራችሁ ቅዱስ እንደ ሆነ እናንተ ደግሞ በኑሮአችሁ ሁሉ ቅዱሳን ሁኑ።”
• የአገልግሎት ልክ
የእግዚአብሄር ባሪያዎች የአገልግሎት ሩጫቸውን ያደረጉት ጌታን ከፊታቸው አድርገው ነበር፤ በዚያም ያለመታከት በጽናት ወደፊት የሄዱበትና ፈተናን ታግሰው አገልግሎታቸውን የፈጸሙት የሩጫውን ልክ ከጌታ ስለተቀበሉ ነበር።
2ቆሮ.10:12-16 “ራሳቸውን ከሚያመሰግኑ ከአንዳንዶች ጋር ራሳችንን ልንቆጥር ወይም ራሳችንን ልናስተያይ አንደፍርምና፤ ነገር ግን እነርሱ ራሳቸውን ከራሳቸው ጋር ሲያመዛዝኑ፥ ራሳቸውንም ከራሳቸው ጋር ሲያስተያዩ፥ አያስተውሉም። እኛ ግን እግዚአብሔር እንደ ወሰነልን እስከ እናንተ እንኳ እንደሚደርስ እንደ ክፍላችን ልክ እንጂ ያለ ልክ አንመካም። ወደ እናንተ እንደማንደርስ አድርገን ከመጠን አናልፍምና፥ የክርስቶስን ወንጌል በመስበክ እስከ እናንተ እንኳ ደርሰናልና፤ በሌሎች ድካም ያለ ልክ አንመካም፥ ነገር ግን እምነታችሁ ሲያድግ ከእናንተ ወዲያ ባለው አገር እስክንሰብክ ሥራችንን እየጨመርን፥ በክፍላችን በእናንተ ዘንድ እንድንከብር ተስፋ እናደርጋለን፤ በሌላው ክፍል ስለ ተዘጋጀው ነገር አንመካም። የሚመካ ግን በጌታ ይመካ፤ እግዚአብሔር የሚያመሰግነው እንጂ ራሱን የሚያመሰግን እርሱ ተፈትኖ የሚወጣ አይደለምና።”
እግዚአብሄርን በግልም በህብረትም እናገለግለው ዘንድ በር ከፍቶአል፤ እግዚአብሄርን የሚያመልክና የሚያገለግል ከእግዚአብሄር ብዙ ምህረት ይቀበላልና ጥቅሙ ለራሱ ነው ማለት ነው።
ማቴ.8:14-15 “ኢየሱስም ወደ ጴጥሮስ ቤት ገብቶ አማቱን በንዳድ ታማ ተኝታ አያት፤ እጅዋንም ዳሰሰ፥ ንዳዱም ለቀቃት፤ ተነሥታም አገለገለቻቸው። ”
የጴጥሮስ አማት በህመም ታስራ ራስዋንና ቤተሰብዋን እንዳትጠቅም ሆና ነበር፤ ጌታ ኢየሱስ ግን ከህመምዋ ስለፈወሳት ተነስታ ወደ ሙሉ ብቃትዋ ተመልሳለች። እግዚአብሄር የፈታን በግል እንድናገለግል ብቻ ሳይሆን እንደ ማህበርም ይህን የጽድቅ ስራ እንድናከናውን ጭምር ነው፤ ስናገለግል ጌታን ተመልክተን ከሆነ ከፊታችን የሚደቀነውን ፈተናና መሰናክል እንድናልፍ የሚያስችል ጸጋ እንቀበላለን።
1ቆሮ.16:14-15 “በእናንተ ዘንድ ሁሉ በፍቅር ይሁን። ወንድሞች ሆይ፥ የእስጢፋኖስ ቤተ ሰዎች የአካይያ በኩራት እንደ ሆኑ ቅዱሳንንም ለማገልገል ራሳቸውን እንደ ሰጡ ታውቃላችሁ”
• የአምልኮ ልክ
አምልኮ የእግዚአብሄር የምህረት መንገድ ነው፤ በአምልኮ ውስጥ እግዚአብሄር ከህዝቡ ጋር ይገናኛል፤ ስለዚህ ህዝቡ እርሱን እንዲያመልኩ ያዛቸዋል፦
ፊሊ.2:9-11 “በዚህ ምክንያት ደግሞ እግዚአብሔር ያለ ልክ ከፍ ከፍ አደረገው፥ ከስምም ሁሉ በላይ ያለውን ስም ሰጠው፤ ይህም በሰማይና በምድር ከምድርም በታች ያሉት ሁሉ በኢየሱስ ስም ይንበረከኩ ዘንድ፥መላስም ሁሉ ለእግዚአብሔር አብ ክብር ኢየሱስ ክርስቶስ ጌታ እንደ ሆነ ይመሰክር ዘንድ ነው።”
በእግዚአብሄር ፊት የሚቆም ሰው አምልኮ የሚያቀርበው አምላኩን ባመነው ልክ ነው፤ የሚዘረጋው እጁ ርዝመቱም የሚወስነው እምነቱ በተዘረጋበት ክልል ልክ ነው፣ አምላኩን በመንፈስ የሚዳስሰው ልቡ እንደተሞላው እምነት ልክ ነው። በመንፈስ ለሚደረግ አምልኮ ስንነሳ ግን አንድ ሃያል እጅን ይዘን እንነሳ፣ ከጠላት ጋር ስንፋለም አንድ ያለ ልክ ከፍ ከፍ ያለ ብርቱ ጌታ ከእኛ ጋር እንደሚሆን ተማምነን መሆን አለበት፣ ይህ ጌታ በአጋንንት ላይ ገዢ በመሆኑ ከፍ ያለውን ስሙን ይዞ ይመጣል፣ ስሙ ምድር ላይ አይወሰንም ወደ ጥልቅ መውረድ ይችላል፣ የቱ ጋኔን ያቆመዋል፣ አየርን ጥሶ ያልፋል የአየር አለቃ አያቆመውም፣ ሰማያትንም ያልፋል፣ በዚያ የሚታዘዙት መላእክት ይህን ስም ያለመታከት ይጠራሉ። ስሙ ልክ ስለሌለው በምንም በማንምም አይወሰንም። ይህን ስም እናሰራ ዘንድ ቅድሚያ መንፈሳችን ሊዘጋጅ እምነታችንም በመንፈስ ቅዱስ ሊበረታ የግድ ነው። የእምነት መንፈስ ስሙን ብቻ ያሰራዋልና።
2ዜና.29:26-29 “ሌዋውያንም የዳዊትን የዜማ ዕቃ ይዘው፥ ካህናቱም መለከቱን ይዘው ቆመው ነበር። ሕዝቅያስም የሚቃጠለውን መሥዋዕት በመሠዊያው ላይ ያሳርጉ ዘንድ አዘዘ፤ የሚቃጠለውም መሥዋዕት ማረግ በተጀመረ ጊዜ የእግዚአብሔር መዝሙር ደግሞ ተጀመረ፥ መለከቱም ተነፋ፥ የእስራኤልም ንጉሥ የዳዊት ዜማ ዕቃ ተመታ። ጉባኤውም ሁሉ ሰገዱ፥ መዘምራኑም ዘመሩ፥ መለከተኞችም ነፉ፤ የሚቃጠለው መሥዋዕት እስኪፈጸም ድረስ ይህ ሁሉ ሆነ።ማቅረቡንም በፈጸሙ ጊዜ ንጉሡና ከእርሱ ጋር የነበሩ ሁሉ አጐነበሱ ሰገዱም።”
• የኑሮ ልክ
የክርስቲያን ህይወት ልክ በስጋ ክልከላ ላይ የተመሰረተ ሳይሆን በመንፈስ ምሪት ላይ የተመሰረተ ነው።
ቆላ.2:22-23 “ከዓለማዊ ከመጀመሪያ ትምህርት ርቃችሁ ከክርስቶስ ጋር ከሞታችሁ፥እንደ ሰው ሥርዓትና ትምህርት፦ አትያዝ፥ አትቅመስ፥ አትንካ ለሚሉት ትእዛዛት በዓለም እንደምትኖሩ ስለ ምን ትገዛላችሁ? እነዚህ ሁሉ በመደረግ ሊጠፉ ተወስነዋልና። ይህ እንደ ገዛ ፈቃድህ በማምለክና በትሕትና ሥጋንም በመጨቆን ጥበብ ያለው ይመስላል፥ ነገር ግን ሥጋ ያለ ልክ እንዳይጠግብ ለመከልከል ምንም አይጠቅምም።”
ኑሮአችን በመንፈሳዊ ህይወታችን ላይ የተደገፈ ሊሆን እንደሚገባው የታመነ ነው። በብሉይ ኪዳን የነበሩ ህግጋቶች ባብዛኛው ስጋዊ ነገሮች ላይ በሚያሳድሩት ክልከላ ላይ ያተኩሩ ነበር። ህጉና ትእዛዞቹ የአዲስ ኪዳን ጥላ ስለነበሩ የእለት ተእለት ኑሮን ይመለከታሉ እንጂ መንፈሳዊነት ላይ አላተኮሩም። እስራኤል ግን ያንን እንኩዋ መሸከም ስላልቻሉ በዚያ ብዙ ጊዜ እንደወደቁ በታሪካቸው ውስጥ ተመዝግቦአል። የአዲስ ኪዳን ህይወት ግን እነዚህን በኑሮ ላይ መሰረት ያደረጉ ህግጋት አልፎ በመንፈስ ግንኙነት አማኝን የሚመራ፣ የሚሰራና የሚያበረታ ሆነ። ሃዋርያው አትያዝ፥ አትቅመስ፥ አትንካ የሚባሉት ትእዛዛት የሰው ስርአትና ትምህርት በመሆናቸው እልፍ በሉና ወደ ጌታ ትምህርት ግቡ ይላል። እነዚህ ትእዛዛት ሥጋን በመጨቆን መንፈሳዊ ይምስላሉ እንጂ የሥጋ ስራን በመንፈስ ስር ሊያስገዙ አይችልም። ስለዚህ ኑሮአችን በመንፈሳዊ ነገር ይመራ፣ የህይወታችንም ልክ የቃሉ እውነትና መንፈሱ በእኛ አድሮ የመስራቱ ውጤት (ፍሬ) ይሁን።
1ጴጥ.4:3-4 “ክርስቶስም በሥጋ ስለ እኛ መከራን ስለተቀበለ፥ ከእንግዲህ ወዲህ በሥጋ ልትኖሩ በቀረላችሁ ዘመን እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ እንጂ እንደ ሰው ምኞት እንዳትኖሩ፥ እናንተ ደግሞ ያን አሳብ እንደ ዕቃ ጦር አድርጋችሁ ያዙት፥ በሥጋ መከራን የተቀበለ ኃጢአትን ትቶአልና። የአሕዛብን ፈቃድ ያደረጋችሁበት በመዳራትና በሥጋ ምኞትም በስካርም በዘፈንም ያለ ልክም በመጠጣት ነውርም ባለበት በጣዖት ማምለክ የተመላለሳችሁበት ያለፈው ዘመን ይበቃልና።”
ቀድሞ እንኖርበት የነበረው ኑሮ ምን ያህል ልክ የለሽ እንደነበረ ያሳይና አሁን ከዚያ እንደተላቀቀ ሰው ያለ ኑሮ መኖር እንዲገባን ያመለክታል። ክርስቶስም በሥጋ ስለ እኛ መከራን ሲቀበል የራሱን ክብር ጥሎ ስለነበር እኛም በሥጋ ልንኖር በቀረልን ዘመን ፈቃዳችን ትተን እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ እንጂ እንደ ሰው ምኞት እንዳንኖር ይመክራል፤ ሰው በእለት ተለት ኑሮው ውስጥ የሃጢያት ሥጋውን በማስጨነቅ የሃጢያትን በር ከዘጋ እግዚአብሄር ይቀበለዋልና። የአሕዛብ ፈቃድ የተባለውን መዳራት፣ የሥጋ ምኞት፣ ስካር፣ ዘፈን፣ ያለ ልክ መጠጣትና ነውር ያለበት የጣዖት አምለኮ ሁሉ የነፍስ ወጥመድና መጥፊያ በመሆናቸው ልማዶቹን በስጋ ኑሮ በምንመላለስበት ዘመን ሁሉ ልንጠየፋቸው እንዲገባ ተመክረናል።