በእግዚአብሄር ፈቃድ አካባቢ ያለውን የፍጥረት ስፍራ ሰው ማስተዋል ቢችል የምድር ፊት ዛሬ ላይ ምን ሊመስል ይችል ነበር? ሌላው ቀርቶ ሰው የታሰበለትን ቢረዳ፣ እግዚአብሄር ሲጣራ ቢሰማ፣ ለራሱ አሳብ ሳይሆን ለሰሪው ድምጽ ጆሮውን ቢያዘነብል የሰው ልጅ እንዴት ባለ ሰላምና ደስታ ይኖር ነበር? አለም መልኩዋም አሳቡዋም ምንም ቢያባብል በመጎተቻዋ ተጠልፈው እጅ ያልሰጡ ያተረፉት ነገር ብዙ ነው፤ በዚህ ሳያበቃ ደግሞ ከርሱዋ እስራት ተንጥቀው ራሳቸውን ወደ እግዚአብሄር ያስጠጉ የምድር መጻተኞች ያላቸውን የፈጣሪያቸውን ታላቅ ስጦታ ቢያዩና ልብ ቢሉ የነርሱ በረከት ለሌላውም እስኪተርፍ የሚታይ ይሆናል።
ኤፌ.1:17-19 “የክብር አባት የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ አምላክ እርሱን በማወቅ የጥበብንና የመገለጥን መንፈስ እንዲሰጣችሁ እለምናለሁ። ይህም የልባችሁ ዓይኖች ሲበሩ የመጥራቱ ተስፋ ምን እንዲሆን በቅዱሳንም ዘንድ ያለው የርስት ክብር ባለ ጠግነት ምን እንዲሆን ለምናምን ከሁሉ የሚበልጥ የኃይሉ ታላቅነት ምን እንዲሆን ታውቁ ዘንድ ነው፤ ክርስቶስንም ከሙታን ሲያስነሣው ከአለቅነትና ከሥልጣንም ከኃይልም ከጌትነትም ሁሉ በላይና በዚህ ዓለም ብቻ ሳይሆን ነገር ግን ሊመጣ ባለው ዓለም ደግሞ ከሚጠራው ስም ሁሉ በላይ በሰማያዊ ስፍራ በቀኙ ሲያስቀምጠው በክርስቶስ ባደረገው ሥራ የብርታቱ ጉልበት ይታያል፤ ሁሉንም ከእግሩ በታች አስገዛለት ከሁሉ በላይም ራስ እንዲሆን ለቤተ ክርስቲያን ሰጠው። እርስዋም አካሉና ሁሉን በሁሉ የሚሞላ የእርሱ ሙላቱ ናት።”
የክርስቶስ ክብር መገኛ ስፍራ ሰማያዊ ስፍራ የሚባል መንፈሳዊ ስፍራ ነው፤ በሰማያዊ ስፍራ ጌታ ኢየሱስ በሚገኝበት በዚያ በረከት አለ፣ ይህ በረከት ቁሳዊ ሳይሆን መንፈሳዊ ሲሆን በመንፈስ ቅዱስም የሚሰጥ ነው፣ መንፈሳችንን የሚመግብ፣ የሚያለመልምና የሚያሳድግም ነው፤ በመንፈሳዊ በረከት እንባረክ ዘንድ በጌታችን በኢየሱስ ሰውነት ተገልጦ በረከቱን የሚሰጠን አንድ አምላክ እግዚአብሄር ነው፤ ይህን በረከት እግዚአብሄር ሊፈጥርና ለእኛ ሊሰጥ ያቀደው ፍጥረትን ወደ መኖር ከማምጣቱ በፊት በመሆኑ እግዚአብሄር እኛን ሊፈጥር ባቀደ ጊዜ በመንፈሳዊ በረከት ሊባርከን እንደተዘጋጀ ያመለክታል፤ መንፈሳዊና ሰማያዊ በረከት የተጠበቅልን የሰው ልጆች ለዚህ በረከት ብቃት የሚሰጠን ቅድስናና ነውር የሌለው ስብእና ነው፣ ይህን ስብእና በራሳችን ችሎታ፣እውቀት ሃይልም ሆነ ደህንነት መጎናጸፍ የማንችል ከመሆኑ ጋር ተያይዞ እግዚአብሄር ብቃት የሆነውን የክርስቶስ ስጋና ደም ሊያዘጋጅ ወደደ፣ እኛ ሁላችንም እግዚአብሄር ባዘጋጀው ስጋና ደም (ክርስቶስ) ለዚህ ተመረጥን (በሰማያዊ ስፍራ መገኘት የምንችልበት ብቃት ላይ ደረስን)። የእግዚአብሄር በጎ ፈቃድ የኛን አመጽ ያለፈ በመሆኑ ሃጢያትና ነውራችንን አልፎ የሚያድንበትን ስራ ሰራ፣ ይህም ስራ በመስቀል ላይ ልጁ እንዲሰቀል በማድረግ በፈሰሰው ደሙና በተቆረሰው ስጋው አድኖ ልጆቹ የምንሆንበትን መንገድ አስቀድሞ አቀደ፤ በአንድያና ውድ በሆነ ልጁ ሞት የሰራው የማዳን ስራም ከእኛ ምንም ነገር ሳይጠይቅ በነጻ በመስጠት በዚህ የጸጋ ስጦታ የምስጋና ክብርን በፍጥረቱ አንደበት የሚፈጥር አደረገው፤ መንፈሳዊ ስጦታ የሆነው ጸጋው ከጌታችን ኢየሱስ ደም መፍሰስና ስጋ መቆረስ ጋር የሚገናኝ እንደመሆኑ በርሱ ስቃይ የተቀበልነው ፍትህ፣ ነጻነት፣ ደስታ፣ መፈታትና የዘላለም ህይወት ሊመሰገን የተገባው ሆኖአል፤ ሰይጣን በሃጢያት አጥምዶና ነፍሳችንን በሞት ፍርድ አሳስሮአት የነበረ ቢሆንም ለነፍሳችን ጌታ ኢየሱስ ነፍሱን በመክፈል እኛን በነጻ አስለቅቆአል፣ ነጻም አውጥቶናል፤ የተሰጠን የመዳን ስጦታ በህይወታችን የሚገለጠው በጸጋው መንፈስ መፍሰስ ሲሆን እውቀቱ በጥበብና በአእምሮ የሚበዛ ሆኖ ህይወታችን እንዲባረክ ያደረገ ነው፣ አስቀድሞ ጥበብና አእምሮ ስላልነበረን ለሰይጣን ክፉ እውቀትና ጥበብ ተላልፈን በመሰጥት እንደጠፋንበት ዘመን ያለ ሳይሆን ከሰይጣን ወጥመድ ወጥተን በጌታ ኢየሱስ ምህረት አጥር ውስጥ በመግባት በደህንነት መኖር የቻልን ሆንን።
እግዚአብሄር አለም ሳይፈጠር ያቀደውን እቅድ ሙላቱን በአለም ፍጻሜ ላይ አድረጎታል፤ ይህን እቅዱን ተግባራዊ የሚያደርገውም እቅዱን ባዘጋጀበት በክርስቶስ ነው። እግዚአብሄር በልጁ ሞት አንድ የማዳን ስራ እንደሰራ ሁሉ ያን ስራውን በጀመረበት በልጁ የሚፈጽመው ነው የሚሆነው፤ እርሱ በልጁ አለማትን ፈጠረ፣ ሰውን በልጁ መልክ ፈጠረ፣ ሰውን ከተሸጠበት ስፍራ ሄዶ በደሙ ገዛ፣ በዚያው ደም ያዳነውን ሰው እየከለለ ሊያኖረውና የመንግስቱ ወራሽ ሊያደርገው ፈቀደ፤ ከዚያም ባለፈ ሀዝቡን ባፈሰሰው ደምና በቆረሰው ስጋው እንዳዳነ ሁሉ የዳኑትን በእርሱ በአንድ መንግስት በዘለአለም ጊዜ ውስጥ ሊጠቀልል ያልዳኑት ደግሞ በእርሱ እጅ አድርጎ ሊፈርድባቸውና በሌላ አንድ የቅጣት ስፍራ በዘላለም ውስጥ ሊያኖር እግዚአብሄር አቅዶአል፤ በዚህ መንገድ እግዚአብሄር ሊያደርግ የፈቀደውን አለም ሳይፈጠርም ያቀደውን በክርስቶስ የመጀመርና በክርስቶስ የመፈጸም ስራ በአዲስ ኪዳን እንዲታወቅ ገልጦታል፤ በክርስቶስ የጀመረው ስራ በዘመን ፍጻሜ ሲጠቃለል በርሱ የተፈጠረው ፍጥረት በርሱ በራሱ የሚጠቀለል ነው የሚሆነው።
ኤፌ1:3-10 “በክርስቶስ በሰማያዊ ስፍራ በመንፈሳዊ በረከት ሁሉ የባረከን የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ አምላክና አባት ይባረክ።ዓለም ሳይፈጠር፥ በፊቱ ቅዱሳንና ነውር የሌለን በፍቅር እንሆን ዘንድ በክርስቶስ መረጠን። በበጎ ፈቃዱ እንደ ወደደ፥ በኢየሱስ ክርስቶስ ሥራ ለእርሱ ልጆች ልንሆን አስቀድሞ ወሰነን።በውድ ልጁም እንዲያው የሰጠን የጸጋው ክብር ይመሰገን ዘንድ ይህን አደረገ። በውድ ልጁም፥ እንደ ጸጋው ባለ ጠግነት መጠን፥ በደሙ የተደረገ ቤዛነታችንን አገኘን እርሱም የበደላችን ስርየት። ጸጋውንም በጥበብና በአእምሮ ሁሉ አበዛልን። በክርስቶስ ለማድረግ እንደ ወደደ እንደ አሳቡ፥ የፈቃዱን ምሥጢር አስታውቆናልና፤ በዘመን ፍጻሜ ይደረግ ዘንድ ያለው አሳቡም በሰማይና በምድር ያለውን ሁሉ በክርስቶስ ለመጠቅለል ነው።”
በቃሉ አትኩሮት የተሰጠውን ባረከን የሚል ቃል እናገኛለን። ቃሉ እግዚአብሄር የባረከን የት እንደሆነ ሲያመለክት በሰማያዊ ስፍራ… እንደሆነ ይታያል። የባረከንም መቼ እንደሆነ ሲያመለክትም ዓለም ሳይፈጠር እንደነበረ ያመለክታል። በማን ባረከን? በክርስቶስ፤ በርሱ ሲባርከንም ገና በጊዜው እኛ በህይወት ሳንኖር አካላችን በምድር ላይ ሳይመላለስም እርሱ ግን አስቀድሞ አይቶ በረከቱን በእኛ ላይ እንዳደረገ ያመለክታል። እግዚአብሄር በምንስ ባረከን? የባረከን በመንፈሳዊ በረከት ነበር፣ በረከቱም በጊዜ የተገደበም እንዳልሆነ በግልጥ ይናገራል፤ እግዚአብሄር በመንፈሳዊ ስፍራ ዓለም ሳይፈጠር በፊት በረከቱን በሚጠራቸው ወገኖች ላይ እንዳስቀመጠ እናያለን። በረከቱን ያስቀመጠባቸው ወገኖችም በእግዚአብሄር የተጠሩ፣ በርሱ ውሳኔ በጸጋው የዳኑ ነበሩ። በዚህ መንገድ እኛ ከመፈጠራችን አስቀድሞ በረከቱን በእኛ በሰው ልጆች ላይ አስቀምጦአል።
እግዚአብሄር ምርጫውን በክርስቶስ አደረገ። የምርጫው አላማ ምን ነበር? የተመረጥን በፊቱ ቅዱሳንና ነውር የሌለን በፍቅር እንሆን ዘንድ በክርስቶስ መረጠን።
ይህም በኢየሱስ ክርስቶስ ሥራ ለእርሱ ልጆች ልንሆን አስቀድሞ ወሰነን ይላል። እነዚህ ሰዎች ልጆች ይሆኑ ዘንድ የተወሰነው በማን ነበር? በክርስቶስ የተደረገ ነበር። በምን ሁኔታ ያን እንዳደረገ ሲናገር በበጎ ፈቃዱ እንደ ወደደ፥ በኢየሱስ ክርስቶስ ሥራ ለእርሱ ልጆች ልንሆን አስቀድሞ ወሰነን እንጂ በእኛ ፍላጎት እንዳይደለ ቃሉ ያስረዳል።
እግዚአብሄር በጸጋው መርጦናል፤ የት ባረከን? በሰማያዊ ስፍራ። መች ለሚለውም አለም ሳይፈጠር ነው ይላል። በማን መረጠን? በክርስቶስ። በረከቱ ምን ይሰጣል? መንፈሳዊ በረከቶችን በሙሉ።
እስከምን ድረስ? በፊቱ ቅዱሳንና ነውር የሌለን በፍቅር እንሆን ዘንድ፤ ዓለም ሳይፈጠር በክርስቶስ ስለመረጠን። በኢየሱስ ክርስቶስ ሥራ ለእርሱ ልጆች ልንሆን አስቀድሞም ወሰነን። ያን ታላቅ እቅድ ሊፈጽምም እግዚአብሄር መጣ።
ዮሐ.1:11-12 “የእርሱ ወደ ሆነው መጣ፥ የገዛ ወገኖቹም አልተቀበሉትም። ለተቀበሉት ሁሉ ግን፥ በስሙ ለሚያምኑት ለእነርሱ የእግዚአብሔር ልጆች ይሆኑ ዘንድ ሥልጣንን ሰጣቸው”
አለም ሳይፈጠር ያቀደውን የማዳን ስራ ሊያከናውን ሲጀምር አስቀድሞ የመጣው ወገኔ ወዳለው ወደ አብረሃም ዘር ነበር፤ እርሱ ሲመጣ ግን እርሱ ህዝቡን እንደተቀበለ ያለ አቀባበል ከህዝቡ ማግኘት አልቻለም ነበር፤ በዚህም ወገኖቹ የተባሉት ተስፋ ሰጥቶአቸው የነበሩ የአይሁድ ህዝብ እንደማያውቁት ሆኑ፤ የወገኖቹ ክህደት እግዚአብሄርን ከስራው ግን አላገደውም፤ ወደ ምድር የወረደው የአብረሃም ወዳጅ ልጆቹ ሳይቀበሉት ቢያፈገፍጉም እግዚአብሄር እነሆኝ ባለበት ጊዜና ስፍራ ላይ እጃቸውንና ልባቸውን ወደ እርሱ የዘረጉትን ተቀብሎአቸዋል፤ እነዚህ የተቀበሉት የጠራቸው የእግዚአብሄር ልጆች የመሆን ብቃትን ከርሱ የተቀበሉበትን ምስጢር ከእርሱ አግኝተዋል፤ ይህ የልጅነት ዋስትና የተገኘው እግዚአብሄር በሰጠው የልጅነት ስልጣን ምክኒያት ነው፤ ስልጣኑ ተገብቶአቸው የነበሩት ሲጥሉት እግዚአብሄር ለፈለጉት አህዛብ መዳንን ሰጥቶአል።
የሰው ልጅ የእግዚአብሄር የዘላለሙ አሳቡ ካልገባው እጅግ ይቸገራል፣ይጠፋበታልም። የቃሉ ብርሃን ደግሞ ያ እንዳይሆን በብዙ ምክርና ብርሃን ያነቃቃል፦
1ጴጥ.1:18-21 “ከአባቶቻችሁ ከወረሳችሁት ከከንቱ ኑሮአችሁ በሚያልፍ ነገር በብር ወይም በወርቅ ሳይሆን፥ ነውርና እድፍ እንደ ሌለው እንደ በግ ደም በክቡር የክርስቶስ ደም እንደ ተዋጃችሁ ታውቃላችሁ። ዓለም ሳይፈጠር እንኳ አስቀድሞ ታወቀ፥ ነገር ግን እምነታችሁና ተስፋችሁ በእግዚአብሔር ይሆን ዘንድ፥ ከሙታን ባስነሣው ክብርንም በሰጠው በእግዚአብሔር በእርሱ ስለምታምኑ ስለ እናንተ በዘመኑ መጨረሻ ተገለጠ።”
ማዳን የማንችልባቸው ደካማ ትምክህቶች እኛ ሰዎች በውስጣችንና በዙርያችን አሉን፣ እነዚያ ትምክህቶች በመንፈሳዊ ህይወት ጉዳይ ላይ የሚያመጡት ተጽእኖ አይኖም፤ በህግ በኩል አይሁዶች የተሸጠ ወገናቸውን መልሰው በመግዛት ነጻ የሚያወጡበት መንገድ ቢኖራቸውም ያን ይፈጽሙ የነበረው ከአባቶቻቸው በወረሱት ብርና ወርቅ ነበር፤ ሆኖም ያ የማንንም ነፍስ ገዝቶ መዋጀት እንደማይችል ሃዋርያው ያሳስባል፤ አይሁድ በብርና በወርቅ የሚያደርጉት ቤዛነት ወገናቸውን ከስጋ ባርነት ነጻ የሚያወጣ ነበረ፤ ይህ የቤዛነት ማለት የነፍስ ቤዛነት ሳይሆን፥ ሰውን ከሰው አገዛዝ ነጻ የሚያወጣ ነበረ፤ ነውርና እድፍ እንደ ሌለው እንደ በግ ደም በክቡር የክርስቶስ ደም የተዋጀነው መዋጀት ግን ከሞት ፍርሃት ነጻ የሚያወጣ ነው፣ ከአጋንንት እስራት ነጻ የሚያወጣ ነው፣ እንዲሁም ከዘላለም ፍርድም የሚያድን ነው።
እግዚአብሄር ዓለም ሳይፈጠር ያቀደውን እቅድ ሲገለጥ ተስፋ ባደረጉት ዘንድ ለምስጋና ይሆን ዘንድ ምስጢሩ በመንፈስ ቅዱስ ታውቆአል፤ ምስጢሩ መገለጡ እምነታችንና ተስፋችን በእግዚአብሄር እንዲሆን አድርጎአል፤ የዘላለም ድነት በኢየሱስ ሞትና ትንሳኤ ስለሆነ የእርሱን ህይወት ወራሾች እንሆን ዘንድ ዳግመኛ ከእርሱ መወለድ አስፈላጊ ነበር፤ ከስጋ አባታችን ከአዳም አንዴ ተወልደናል፣ የርሱ ዘር ግን የሚጠፋ ዘር ነው፤ እግዚአብሄር ግን ከማይጠፋ ዘር ከመንፈስ መወለድን አዘጋጅቶ በሕያውና ለዘላለም በሚኖር በእግዚአብሔር ቃል ከማይጠፋ ዘር ተወለድን፤ ከአዳም የተገኘ ሥጋ ሁሉ ረጋፊ ሆኖ እንደ ሣር የተመሰለ ነው፣ ክብሩም ሁሉ እንደ ረጋፊው ሣር ጊዜያዊ አበባ ነው፤ ሣሩ ይጠወልጋል አበባውም ይረግፋል፤ እንዲሁ አዳማዊ ስጋ ይረግፋል፣ የማይጠፋው የጌታ ቃል ግን ለዘላለም ይኖራል።
“አሁን ግን በሕግና በነቢያት የተመሰከረለት የእግዚአብሔር ጽድቅ ያለ ሕግ ተገልጦአል፥ እርሱም፥ ለሚያምኑ ሁሉ የሆነ፥ በኢየሱስ ክርስቶስ በማመን የሚገኘው የእግዚአብሔር ጽድቅ ነው፤ ልዩነት የለምና፤ ሁሉ ኃጢአትን ሠርተዋልና የእግዚአብሔርም ክብር ጎድሎአቸዋል፤ በኢየሱስ ክርስቶስም በሆነው ቤዛነት በኩል እንዲያው በጸጋው ይጸድቃሉ። እርሱንም እግዚአብሔር በእምነት የሚገኝ በደሙም የሆነ ማስተስሪያ አድርጎ አቆመው፤ ይህም በፊት የተደረገውን ኃጢአት በእግዚአብሔር ችሎታ ስለ መተው ጽድቁን ያሳይ ዘንድ ነው፥ ራሱም ጻድቅ እንዲሆን በኢየሱስም የሚያምነውን እንዲያጸድቅ አሁን በዚህ ዘመን ጽድቁን ያሳይ ዘንድ ነው። ትምክህት እንግዲህ ወዴት ነው? እርሱ ቀርቶአል።”
ጌታ ኢየሱስ ሲወለድ በምድር ላይ አንዳች የጽድቅ ፍሬ የሚታይበት ፍጥረት አልነበረም፤ ቃሉ አይሁድም የግሪክ ሰዎችም ሁሉ ከኃጢአት በታች እንደሆኑ ይናገራል፤ በሮሜ3 ውስጥ እንደተመለከተው መድሃኒት በምድር ሲገለጥ እርሱን የሚቀበል ልብ ጨርሶ አልተዘጋጀም፣ ብቁ ሰው ጽድቅን የናፈቀ አንዳች አልነበረም፣ ቃሉን ያስተዋለም አልነበረም፣ ሃጢያት ምድርን ሸፍኖ ስለነበረ ከግርዶሹ አምልጦ በጭላንጭል እንኩዋን እግዚአብሔርን የሚፈልግ አንድ ሰው አልተገኘም፤ ሰው የተባለ ከቤተመቅደስ እስከ ቤተመንግስት፣ ከገጠር እስከ ከተማ፣ ከሃይማኖት መምህራን እስከ ተራው ህዝብ፣ ከአለቆች እስከ ምንዝር፣ ሁሉ በተሳሳተ መንገድ ላይ ነበር፤ ሰዎች ሁሉ በእግዚአብሄር ፊት በሃጢያታቸው ተይዘው የሚያጣጥሩ ነበሩና ለአንዳችም የጽድቅ ስራ የማይጠቅሙ ሆነው ተገኝተዋል፤ በጎነቱን ሊገልጥ የተገለጠ አምላክ በፍጥረቱ መሃል ቸርነት ያለበትን ሊያገኝ ፈልጎ አንዳችም አላገኘም፤ አስተማሪዎች ከንቱን ይናገራሉ፣ እስራት ያስተምራሉ፣ የሃይማኖት መምህራን ልማድና ተረት እንጂ ህይወት የሚገኝባቸውን የጌታ ቃላት አያሰሙም፤ ጌታ ሲመለከታቸው ጕሮሮአቸው እንደ ተከፈተ መቃብር ሆኖ አግኝቶታል፣ ምክኒያቱም አምላክን ጠርተው ሃሰት ገልጠዋል፣ ሃይማኖትን እየሰበኩ ፈጣሪን ሳይሆን ራሳቸውን የሚያሳዩ ሆነዋል፤ በምላሳቸውም ሸንግለው ብዙ የዋህ ነፍሳትን ወደ ሲኦል ልከዋል፤ ደህንነትን የሚያወሩ ሳይሆኑ እንደ እባብ ተናድፈው በክፉ ቃላቸው መርዝን የሚረጩ ነበሩ፤ በህያው አምላክ ቤተመቅደስ አካባቢ ሆነው ተስፋውን አላሰሙም፤ እነርሱ ግን አታላዮችና ገንዘብ አትራፊዎች ነበሩ፣ መባረክ አላወቁም፣ አፋቸውም እርግማንና መራርነት ሞልቶበታልና፤ በጽድቅ እንዲቆሙ የተፈጠሩ እግሮቻቸው ደምን ለማፍሰስ ፈጠኑ፤ የሙሴ ህግ ተሰጥቶአቸው ሳለ በህጉ የሚኖሩበት አቅም ስላልነበራቸው እግዚአብሄርን የሚያስቆጡ ሆኑ፤ እነርሱ እንደተመኙት ሳይሆን ጥፋትና ጉስቁልና በመንገዳቸው ቆሞ ነበር፤ ሁከተኞች የሰላም ፍሬ ያልነበራቸውና የሰላምንም መንገድ የማያውቁም ነበሩ።
(ኢሳ. 25:6 “የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔርም ለሕዝብ ሁሉ በዚህ ተራራ ላይ ታላቅ የሰባ ግብዣ፥ ያረጀ የወይን ጠጅ፥ ቅልጥም የሞላባቸው የሰቡ ነገሮች፥ የጥሩና ያረጀ የወይን ጠጅ ግብዣ ያደርጋል።”
ዛሬም ነገም በማይረሳ ማስተዋል ሆነን የታሰበልንን ደጋግመን እናስብ፦ የተራራው ታላቅ ግብዣ ለፍጥረት እስከዛሬ አልተዘጋምና፣ ያረጀው ወይን ጠጅም አላለቀም፣ ቅልጥም የሞላባቸው የሰቡ ነገሮች አሁንም ድረስ አሉ፣ ወደ ጥሩና ያረጀ የወይን ጠጅ ግብዣ ከጌታ ዘንድ የተዘረጋች እጅ እየተጣራች ነው፦ ወንጌል ይህን እያወጀ ነው፣ ሁሉንም ወደዚያ እየጠራ ነው።