ችግር በብዙ መልክ ይገለጣል፤ ቢሆንም እጥረት፣ ማጣት፣ አለመሳካት፣ እንቅፋት፣ እክል፣ ድካም፣ አደጋ፣ ህመም የመሳሰሉት በአብዛኛው በስጋችን ላይ የሚሆኑ ችግሮቻችን ናቸው። ችግር ግን በስጋ ላይ ብቻ አይቆምም፣ ይልቁንም በመንፈሳዊ የህይወት አቋም ውስጥ ከፍ ባለ ሁኔታ ይገለጣል እንጂ። መንፈሳዊ ችግር በስጋ ላይ ሊንጸባረቅ የማይችል ከሆነ በለመድነው መንገድ ‘’ይህ በመንፈሳዊ ህይወታችን ውስጥ የሆነብን ነው’’ ብለን አስረግጠንና አምነን እንደ ችግር ለመቀበል ለየት ያለ እይታ ይጠይቃል። ስለዚህ ልዩ የእይታ አድማስ የምንቀበለው፣ ከሚታየው ነገር አሻግረን ማየት የምንችለውና በመንፈሳዊ አለም ያለን ጉስቁልና መለየት የምንችለው ከስጋ አእምሮ በወጣ መንገድ በተለይ የልቦናችን ዓይን በእግዚአብሄር መንፈስ ሊበራ ሲችል ብቻ ነው፤ በመንፈስ የሆነ ብርሃንም ከጌታ ስንቀበልና ችግራችን ሲገለጥ ነው፤ በዚህ ማስተዋል ልንጎበኝ የምንፈልግ ደግሞ ከአምላካችን ጋር መጣበቅና አስቀድሞ በርሱ መጎብኘት ያስፈልጋል። መንፈሳዊውን ብርሃን የሚሻው ንጉስ በትህትና ሲለምን እንዲህ ይላል፦
‘’የሚያስጨንቁኝም እኔ ብናወጥ ደስ እንዳይላቸው፥ ለሞትም እንዳልተኛ ዓይኖቼን አብራ።’’ (መዝ.13:4)
ንጉሱ ከመንፈስም ከስጋም በኩል ብርቱ ችግር ውስጥ ነበር፣ በቸገረኝ ነገር እንዳልጠፋ እንዲሁም ጥፋቴን የሚሹ አስጨናቂዎቼ ደስ እንዳይላቸው ዓይኖቼ ተከፍተው የችግሮቼን ምንጭ ልለይና ልጠንቀቅ ይላል።
ችግር አካላዊ ሲሆን የጉዳቱ ምልክት በአካላችን ላይ በሚፈጥረው ጠባሳ ይታወሳል፣ አብሮንም ይኖራል፤ በመንፈስ የሚደርሰው ጉዳት ግን የላቀ ነው፤ አድርቆን፣ መንፈሳዊነትን አሳጥቶንና ከእግዚአብሄር አርቆ ሲያስቀረን በአካላችን ላይ አንዳች ምልክት ሳያሳርፍ ነው።
እግዚአብሄር ለልጆቹ በተለይ እርሱን ለሚያመልኩና ለሚያገለግሉ ግን እርሱ ራሱ ቀርቦ ያገለግላቸዋል፤ ጠላቶቻቸውን አፍ ይዘጋል፣ የትምክህት ክንዳቸውን ያሙዋሙዋል፣ አሳባቸውን ይበትናል። ተቸግሮአል፣ የሚረዳው ጎኑ የለም፣ አገኘሁት፣ እውጠዋለሁም ሲል ደካማውን ሊጎዳ የሚመጣ ጠላት ከእግዚአብሄር ዘንድ ብርቱ ተግሳጽ ይሆንበታል፤ እግዚአብሄር እውነተኛና መታመኛ አምላክ ነውና፦
ኢሳ.25:4-5 ‘’የጨካኞችም ቍጣ እስትንፋስ ቅጥርን እንደሚመታ ዐውሎ ነፋስ በሆነ ጊዜ፥ ለድሀው መጠጊያ፥ ለችግረኛው በጭንቁ ጊዜ መጠጊያ፥ ከውሽንፍር መሸሸጊያ ከሙቀትም ጥላ ሆነሃል። እንደ ሙቀት በደረቅ ስፍራ የኀጥአንን ጩኸት ዝም ታሰኛለህ፤ ሙቀትም በደመና ጥላ እንዲበርድ እንዲሁ የጨካኞች ዝማሬ ይዋረዳል።’’
በእርሱ የታመናችሁ ተጠጉት፣ አብልጣችሁ እርሱንና መንገዱን ፈልጉ፤ ፈቃዱን አውቀው ለቀረቡት መፍትሄ ሆኖአቸዋል፣ መልስ ሆኖአቸዋአል፣ መጠጊያ፣ መታመኛ፣ መዳኛ፣ ጉልበትም ጭምር ሆኖአቸዋል።
የእግዚአብሄር ፈጣን መልስ ምስኪኖችን ከውድቀት አትርፎ ያቆማል፤ እርሱ ለብርታት ይሆናል፣ በመጠጊያነቱ እረፍት ይሰጣል፣ ጥላ ሆኖ ከመከራ ሃሩር ይጋርዳል፣ እግዚአብሔር ለፍላጎታችን ሁሉ መልስ አለውና እንዴት እንደሚታደገንና እንደሚያኖረን ያውቃል።
ነገር ግን በእግዚአብሄር ህዝብ ላይ ችግር፣ መከራና ፈተና ይመጣ የነበረው ከአምላካቸው በራቁ ጊዜ እንደነበረ ከእስራኤል ታሪክ እንማራለን፤ እነርሱ ተስፋቸው እግዚአብሄር ብቻ እንደሆነ ሲዘነጉና አምላካቸውን ቸል ሲሉ ህይወታቸው በችግር ይያዝ ነበር፤ እነርሱ የነገራቸውን ቸል ሲሉና ከአህዛብ ጋር ሲደባለቁ በሚገጥማቸው የህይወት እንቅፋት ዘመናቸው ቸል ይላቸው ነበር፤ እነርሱ ህያውና ብቸኛ አምላክ የሆነውን የአብረሃም፣ የይስሃቅና የያእቆብን አምላክ ሲተዉ ይተዋቸው ስለነበር በክፉ መናፍስት ይጠቁ ነበር፣ እርሱም ለገዛ ምኞታቸው አሳልፎ ይሰጣቸው ነበር። ህዝቡ ግን ፊቱን ሲመልስና በስራው ተጸጽቶ በንሰሃ ሲመለስ የእግዚአብሄር ምህረት ፈጥኖ ያገኛቸዋል፦
ኢሳ.9:1-3 ‘’ነገር ግን ተጨንቃ ለነበረች ጨለማ አይሆንም። በመጀመሪያው ዘመን የዛብሎንንና የንፍታሌምን ምድር አቃለለ፤ በኋለኛው ዘመን ግን በዮርዳኖስ ማዶ በባሕር መንገድ ያለውን የአሕዛብን ገሊላ ያከብራል። በጨለማ የሄደ ሕዝብ ብርሃን አየ፤ በሞት ጥላ አገርም ለኖሩ ብርሃን ወጣላቸው። ሕዝብን አብዝተሃል፥ ደስታንም ጨምረህላቸዋል፤ በመከር ደስ እንደሚላቸው፥ ሰዎችም ምርኮን ሲካፈሉ ደስ እንደሚላቸው በፊትህ ደስ ይላቸዋል።’’
የነፍስ ጉስቁልናና ተስፋ የማጣት ችግር በህይወታችን ከከረመና ስር ከሰደደ ደግሞ እስከ ትውልድ በሚደርስ የስጋ ጉስቁልና መመታት ጭምር ይከተላል፤ ይህም ባለማስተዋል የሚኖሩ የእግዚአብሄር ልጆች በመንፈሳዊ ብቻ ሳይሆን በስጋዊ ኑሮአቸው የእግዚአብሄር አብሮነት አማራጭ የሌለው ውሳኔ መሆኑን ሲያሳይ ነው።
ኢሳ.10:1፡2-4 ‘’መበለቶችም ቅሚያቸው እንዲሆኑ፥ ድሀ አደጎችንም ብዝበዛቸው እንዲያደርጉ፥ የድሀውን ፍርድ ያጣምሙ ዘንድ፥ የችግረኛውንም ሕዝቤን ፍርድ ያጐድሉ ዘንድ የግፍን ትእዛዛት ለሚያዝዙ፥ ክፉንም ጽሕፈት ለሚጽፉ ወዮላቸው!
በተጎበኛችሁበት ቀን፥ መከራም ከሩቅ በሚመጣበት ዘመን ምን ታደርጉ ይሆን? ለረድኤትስ ወደ ማን ትሸሻላችሁ? ክብራችሁንስ ወዴት ትተዉታላችሁ? ከእስረኞች በታች ይጐነበሳሉ፥ ከተገደሉትም በታች ይወድቃሉ። በዚህም ሁሉ እንኳ ቍጣው አልተመለሰችም፥ ነገር ግን እጁ ገና ተዘርግታ ትኖራለች።’’
በእግዚአብሄር የተጠሩ ወገኖች ከአምላካቸው ውጪ ሳሉ በአእምሮአቸው ውሳኔ ሳሉና በራሳቸው የበቁ ሲመስላቸው፣ የልባቸውን አሳብም በዚያ ሲፈጽሙ እየተሳበ የሚመጣን ጥፋት ማየት እንደሚሳናቸውና ሊከላከሉት እንደማይችሉ ቃሉ ያሳየናል። የይሁዳ መንግሥት በጥንካሬ የቆመና በብልጥግና የተሞላ በሚመስል ጊዜ ታላቅ ጥፋት እየቀረበው በመሄድ ላይ ነበር፤ ያኔ ሃያላኑ ሙሰኞች ሆነው ችግረናን የሚበድሉ ነበሩ፤ ሴቶቹም እግዚአብሄርን የማይፈሩና ግድየለሾች ነበሩ፤ በዚህ ሁሉ ልምምድ ውስጥ ሳሉ ግን የፍርድ ቀን የመቃረቡ አዋጅ ከእግዚአብሄር ይወጣ ጀመር።
እስራኤላውያን ያምጹ እንጂ ተቃውሞውን ያቀረበው ነቢዩ ኢሳይያስ ወደፊት ሊሆን ያለው አስጨንቆት የእግዚአብሄርን ቃል ሲያሳስባቸው እናያለን፤ የማሳሰቢያው ዋና ማእከላዊ መልእክትም፦ እግዚአብሔር ይሁዳን ሊጥል ነው የሚል ማስጠንቀቂያ የነበረው ነው። ሆኖም ይህ ማስጠንቀቂያ በጊዜው ለመኩዋንንቶቹ ሆነ ለህዝቡ እንደ ክህደት የተቆጠረ ንግግር ነበር እንጂ ዋጋ ያለው መልእክት አልሆነም።
የእግዚአብሄር ነቢይ የሆነው እርሚያስ ከህዝቡ ክፋት የተነሳ ህይወቱ የጎሰቆለ ነቢይ ነበር፤ የወገኖቹ እልከኝነት በአንድ ወገን ነቢዩ ከአምላኩ የሰማው የፍርድ ቃል በሌላ በኩል ሆነው እጅግ ያስጨንቁት ነበር፤ የህዝቡ እልከኝነት፣ የነገስታቱ ከእግዚአብሄር ፈቃድ የወጣ አካሄድ ከዚያም የከፋው የሃይማኖት መሪዎቻቸው ሃሰተኝነት ሲያስጨንቀው በሌላ በኩል የአምላኩ ተናገር፣ ህዝቤን አስጠንቅቅ የሚለው ግፊት እያሳሰበው ነቢዩ ህይወቱ በፈተና የተሞላ ሆነበት። እርሱም የሰማውን የአመጸኞችን ማስፈራርያ ሲናገር የብዙ ሰዎችን ስድብ ሰምቻለሁ፥ ማስፈራራትም ከብቦኛል፤ መውደቄን የሚጠብቁ የሰላሜ ሰዎች አሉ፤ ምናልባት ይታለል እንደ ሆነ፥ እናሸንፈውም እንደ ሆነ፥ እርሱንም እንበቀል እንደ ሆነ፥ ክሰሱት እኛም እንከስሰዋለን ይላሉ ሲል በጭንቀት ይናገራል።
በኤር.20:11-13 ላይ ደግሞ የአምላኩን ማጽናናት አንስቶ ሲናገር፦
‘’እግዚአብሔር ግን እንደ ኃያልና እንደ ጨካኝ ከእኔ ጋር ነው፤ ስለዚህ አሳዳጆቼ ይሰናከላሉ አያሸንፉም፤ አይከናወንላቸውምና በጽኑ እፍረት ያፍራሉ፥ ለዘላለምም በማይረሳ ጕስቍልና ይጐሰቍላሉ። አቤቱ፥ ጻድቅን የምትመረምር ኵላሊትንና ልብን የምትመለከት የሠራዊት ጌታ ሆይ፥ ክርክሬን ገልጬልሃለሁና በቀልህን በላያቸው ለይ። ለእግዚአብሔር ዘምሩ እግዚአብሔርንም አመስግኑ፤ የችግረኛውን ነፍስ ከክፉ አድራጊዎች እጅ አድኖአልና።’’
አንዳንዴ ችግር መፍትሄ እንዲገኝለት ወደ ራስ ማየት መልካም ነው፣ ችግሮቻችን የተፈጠሩት በራሳችን ስህተት ሆነው ይሆናልና። ራስን በፍጹምነት ደረጃ ማቆም ወይም መፈረጅ ሰው በሰውነቱ ደካማ መሆኑን ከመዘንጋት ወይም ካለማወቅ የመጣ ነው፤ ስጋ ለባሽ ደካማ ነውና ለሃጢያት፣ ላለማስተዋል፣ ለመተላለፍ የተጋለጠ ነው፤ ይህ አይነካካኝም ለሚል ቢያንስ ቢያንስ ለስንፍና የተጋለጠ መሆኑን ሊቀበል ተገቢ ነው። ታላቁ ሃዋርያ ግን ያለበት ከፍታ ሳይሸፍነው የሰውን ስሪት ጠቅለል አድርጎ በሚያሳይ መልኩ በራሱ አድርጎ ሊያሳየን ሞክሮአል፦
ሮሜ.7:14-20 ‘’ሕግ መንፈሳዊ እንደ ሆነ እናውቃለንና፤ እኔ ግን ከኃጢአት በታች ልሆን የተሸጥሁ የሥጋ ነኝ። የማደርገውን አላውቅምና፤ የምጠላውን ያን አደርጋለሁና ዳሩ ግን የምወደውን እርሱን አላደርገውም። የማልወደውን ግን የማደርግ ከሆንሁ ሕግ መልካም እንደ ሆነ እመሰክራለሁ። እንደዚህ ከሆነ ያን የማደርገው አሁን እኔ አይደለሁም፥ በእኔ የሚያድር ኃጢአት ነው እንጂ። በእኔ ማለት በሥጋዬ በጎ ነገር እንዳይኖር አውቃለሁና፤ ፈቃድ አለኝና፥ መልካሙን ግን ማድረግ የለኝም። የማልወደውን ክፉን ነገር አደርጋለሁና ዳሩ ግን የምወደውን በጎውን ነገር አላደርገውም።የማልወደውን የማደርግ ከሆንሁ ግን ያን የማደርገው አሁን እኔ አይደለሁም፥ በእኔ የሚኖር ኃጢአት ነው እንጂ።’’
ራሳችንን እንዲህ ስናይ ምህረቱን ፍለጋ ወደ እግዚአብሄር ቃል እናዘነብላለን፣ መሻታችንን አስተካክለን ወደ ፈቃዱ እናመራለን፣ ሃይሉን እንጠማለን፣ መዳንን የሙጥኝ እንላለን።
የችግሮቻችን ምንጭ ከመንፈሳዊ ነገር ሲነሳ መፍትሄው መንፈሳዊ ሊያውም አምላካዊ ብቻ ካልሆነ አደገኛ ነው፤ ብዙዎች የሚስቱት መንፈሳዊ እንቆቅልሾችን በስጋ አእምሮ ሊፈቱ ሲሞክሩ ስለሆነ ይህን አውቆ መፍትሄው ያለው ከእግዚአብሄር ዘንድ መሆኑን ቁርጥ እድርጎ ማመን ያስፈልጋል። በእኔ ማለት በሥጋዬ በጎ ነገር እንዳይኖር አውቃለሁና፤ ፈቃድ አለኝና፥ መልካሙን ግን ማድረግ የለኝም። የማልወደውን ክፉን ነገር አደርጋለሁና ዳሩ ግን የምወደውን በጎውን ነገር አላደርገውም።የማልወደውን የማደርግ ከሆንሁ ግን ያን የማደርገው አሁን እኔ አይደለሁም፥ በእኔ የሚኖር ኃጢአት ነው እንጂ። እንዲህ ከሆነ በአብዛኛው የችግሬ ምንጭ ያለው እኔው ውስጥ ነውና ራሴን ልፈትሽ፤ ለዚህ ምንም ሰበብ ሳያስፈልገኝ፣ ወደ ማንም ከማመልከት በፊትም ወደ ራሴ ተመልክቼ ልፈወስ፤ እንዲህ ቅን ስሆን ትክክለኛ ንሰሃ ልገባ እችላለሁ፣ የእግዚአብሄርን ፍጹም ምህረትም እንዲሁ እቀበላለሁ።
ሮሜ.7:24-25 ‘’እኔ ምንኛ ጎስቋላ ሰው ነኝ! ለዚህ ሞት ከተሰጠ ሰውነት ማን ያድነኛል? በኢየሱስ ክርስቶስ በጌታችን ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን። እንግዲያስ እኔ በአእምሮዬ ለእግዚአብሔር ሕግ፥ በሥጋዬ ግን ለኃጢአት ሕግ እገዛለሁ።’’
በስጋ አእምሮ ስገዛ ኃጢአት ስለሚገዛኝ በመንፈስ እየተገዛሁ አርነት እንድወጣና ነጻነት ያለው ህይወት እንድኖር በእግዚአብሄር ታምኜ ልኖር ያስፈልጋል።
ራስን ለእግዚአብሄር ጥበቃ መስጠት
ውስብስብ ከሆነው መንፈሳዊ ችግር ለመውጣት ብቸኛው መንገድ በእግዚአብሄር ምሪት መኖር ከሆነ እግዚአብሄር ለሚሰጠን ምሪት ከርሱ ማስተዋል ልንቀበል የግድ ያስፈልጋል።
ስለማስተዋል ስናነሳ የጌታ ደቀመዛሙርትን ምሳሌ አድርገን ማየት አለብን፤ ለምሳሌ ሃዋርያት ልዩ የማስተዋልና የመገለጥ ሃይል እስኪቀበሉ ድረስ በኢየሩሳሌም ተከማችተው በአንድ ልብ በጸሎት ጌታን እንዲጠባበቅቁ ተደርገው ነበር፤ ጌታም እንደ ተስፋው ቃል ሲገለጥና መንፈሱን ሲያፈስ ሃይልን ተቀበሉ፣ ፍጹም ለውጥ ተቀበሉ፣ አንድ አዲስ ማንነትን የተላበሱ የወንጌል ሰራዊት ሆነው ሊቆሙ ቻሉ። ከዚያ ወዲያ ያን የተለወጠ የደቀመዛሙርት ህይወት ሊያቆም የቻለ ሃይል ከቶ አልነበረም። በዚያ የማስተዋል ሃይል መንፈሳዊውን አለም አስሰዋል፣ በርብረዋል፣ መዋጋት የነበረባቸውን ሃይላት ተዋግተዋል፣ ችግረኛንም ነጻ አውጥተዋል። ከችግራቸው ይልቅ ለችግረኞች የደረሱት በተቀበሉት የበለጠ ሃይል ምክኒያት ነው፦
ሐዋ.3:1-8 ‘’ጴጥሮስና ዮሐንስም በጸሎት ጊዜ በዘጠኝ ሰዓት ወደ መቅደስ ይወጡ ነበር። ወደ መቅደስም ከሚገቡት ምጽዋት ይለምን ዘንድ፥ ሰዎች ተሸክመው መልካም በሚሉአት በመቅደስ ደጅ በየቀኑ ያስቀምጡት የነበሩ ከእናቱ ማኅፀን ጀምሮ አንካሳ የሆነ አንድ ሰው ነበረ። እርሱም ጴጥሮስና ዮሐንስ ወደ መቅደስ ሊገቡ እንዳላቸው ባየ ጊዜ፥ ምጽዋትን ለመናቸው። ጴጥሮስም ከዮሐንስ ጋር ትኵር ብሎ ወደ እርሱ ተመልክቶ፦ ወደ እኛ ተመልከት አለው። እርሱም አንድ ነገር ከእነርሱ እንዲቀበል ሲጠብቅ ወደ እነርሱ ተመለከተ። ጴጥሮስ ግን፡- ብርና ወርቅ የለኝም፤ ይህን ያለኝን ግን እሰጥሃለሁ፤ በናዝሬቱ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ተነሣና ተመላለስ አለው። በቀኝ እጁም ይዞ አስነሣው፤ በዚያን ጊዜም እግሩና ቍርጭምጭምቱ ጸና፥ወደ ላይ ዘሎም ቆመ፥ ይመላለስም ጀመር፤ እየተመላለሰም እየዘለለም እግዚአብሔርንም እያመሰገነ ከእነርሱ ጋር ወደ መቅደስ ገባ።’’
ሃዋርያት በተቀበሉት ጸጋ ተደግፈው ለተጨነቁ ደርሰዋል፣ በጌታ ኢየሱስ ስም ታምራት ሰርተዋል፤ እንዲሁም ከእግዚአብሄር ምህረት የተቀበሉ ሁሉ ለችግረኞች ይደርሱ ዘንድ ሲማጸኑ ነበር። እነዚህ አይናቸው የበራ ደቀመዛሙርት ሲመሰክሩ ለደካማ ራሩላቸው አሉ፣ ችግረኛውን አትለፉ አሉ፣ አትፍረዱም አሉ። ደካማ ሆነው ያውቃሉና፣ ተቸግረው ያውቃሉና፣ በስንፍና ሆነው ከፍርድ እንዴት እንዳመለጡም ያውቃሉና። እርግጥ ነው፣ አጥብቆ ለሚጸልይና ፊቱን ለሚፈልግ የእግዚአብሄር መልስ ይመጣል፣ ስለዚህ፦
‘’ለደካማ ኃይልን ይሰጣል፥ ጕልበት ለሌለውም ብርታትን ይጨምራል። ብላቴኖች ይደክማሉ ይታክቱማል፥ ጐበዛዝቱም ፈጽሞ ይወድቃሉ’’ (ኢሳ.40:29-30)