ለችግረኛው የቆመ(1…)

እግዚአብሄር በአምላካዊ ቸርነትና በፍጹም ደግነት ለቅዱሳን መጽናናትና ድጋፍ ሆኖ የሚገለጠው ሰዎች በነርሱ ላይ ያን አመለካከትና ምግባር ማሳየት ስለማይችሉ ነው። አለም በከፋ መንፈስ ተይዛ ሳለች ልጆችዋ በጎነትን ሊያፈልቁ ስለማይችሉ ህያው አምላክ ለራሱ የቀደሳቸውን ወገኖች እንዴት ባለ ምህረት እንዲያኖር ያውቃል። የሰው ልጆች ለደግነት መስፈርታቸው የሚወዱትና የሚወዳቸው ሰው መሆኑ፣ የሚጠቅሙትና የሚጠቅማቸው ሆኖ ሲገኝም ነው። በእግዚአብሄር ፊት ደስ የሚያሰኘውን መልካም ነገር በማድረግ ፈንታ ሰዎች ክፋትና አመጽ እንዲሁም አድማ አድርገውበት ሳለና በህይወቱም በተፈጠረ ሁከት ምክኒያት ከፍተኛ መናወጥ ውስጥ ሆኖ ሳለ ንጉስ ዳዊት ከእግዚአብሄር ጋር መነጋገርን መረጠ፤ በተለይ አቅሙ ተሙዋጦ በህመሙ ሰበብ አልጋ በያዘበት ወቅት ጠላቶቹ እጅግ ከፍተውበትና ጨክነውበት ስለነበር የደረሰለትና ያጽናናው የእግዚአብሄር እርዳታና ምህረት ተሰምቶት ነበርና በተሰበረ ልብ ተናገረ፤ ለርሱ ከሰው ልጅ ጭካኔ በተቃራኒ የሚገለጥ የእግዚአብሄር ቸርነትና ጸጋ እንደሚደርስለት አምኖ ነበርና፦
‘’ለችግረኛና ለምስኪን የሚያስብ ምስጉን ነው፤ እግዚአብሔር በክፉ ቀን ያድነዋል። እግዚአብሔር ይጠብቀዋል፥ ሕያውም ያደርገዋል፥ በምድር ላይም ያስመሰግነዋል፥ በጠላቶቹም እጅ አያሳልፈውም። እግዚአብሔር በደዌው አልጋ ሳለ ይረዳዋል፤ መኝታውን ሁሉ በበሽታው ጊዜ ያነጥፍለታል። እኔስ፦ አቤቱ ማረኝ፤ አንተን በድያለሁና ነፍሴን ፈውሳት አልሁ። ጠላቶቼም በላዬ ክፋትን ይናገራሉ። መቼም ይሞታል ስሙስ መቼ ይሻራል? ይላሉ። እኔን ለማየት ቢገባ ከንቱን ይናገራል፤ ልቡ ኃጢአትን ሰበሰበለት፤ ወደ ሜዳ ይወጣል ይናገራልም። በላዬ በመተባበር ጠላቶቼ ሁሉ ይሾካሾኩብኛል፥ በእኔ ላይም ክፋትን ያስባሉ። ክፉ ነገር መጣበት፤ ተኝቶአል ከእንግዲህ ወዲህ አይነሣም ይላሉ።’’ (መዝ.41:1-8)
ጻድቅ ሰው እንደማይቸገር ቃልኪዳን አልተገባም፣ ነገር ግን አምላኩ ችግረኛውን ችግር ከሚያመጣበት የጠላት አሰራርና ከሚያስጨንቀው ከርሱ እንደሚያድነው ማስተማመኛ ሰጥቶታል። የእምነት ሰው የሆነው ንጉስ ዳዊት ወደ ሰው ከመመልከትና እርዳታቸውን ከመሻት ይልቅ ልቡን ወደ እግዚአብሄር አዘነበለ፤ በህመም ተመትቶ በተኛበት አልጋው ላይ ሆኖ ከህመሙ ጋር እየታገለ፣ በሌላ በኩል ልቡን ከሚሰብሩ ጠላቶች አሳብ ጋር እየተሙዋገተ አብልጦ የእግዚአብሄርን ምህረት ሲሻና በእምነት ወደሚያድነው ሲጸልይ ነበር።
በጎ ባልሆነ አመለካከት የተያዙ ወገኖች ሊያባብሱ የሚፍቁት የቁስል ጠባሳ ጠልቆ በሚሰማበት አስጨናቂ ወቅት፣ መልካም ስሜት መፍጠር ወይም በትእግስትና በትህትና ነገሮችን መቀበል አዳጋች ነው፣ ነገር ግን በዚያ አስቸጋሪ ወቅት የእግዚአብሄርን አሳብ ማክበር መታደል ነው፣ ከእግዚአብሄር መልስ አለውና። በተመሳሳይ ንጉሱ የደረሰበትን ነገር፣ በሚጠሉት እጅ የተከናወነበትንም ጭከና በጽሞና ወደ አምላኩ አቀረበ እንጂ በንግስና ስልጣኑ አልታገለውም፣ ወይ ጠላቶቼ ወዮላችሁ ብሎ አልተነሳም።
መዝ.38:15-22 ‘’አቤቱ፥ በአንተ ታምኛለሁና፤ አቤቱ አምላኬ፥ አንተ ትሰማኛለህ። ጠላቶቼ በእኔ ላይ ደስ እንዳይላቸው ብያለሁና፥ እግሮቼም ቢሰናከሉ ራሳቸውን በእኔ ላይ ከፍ ከፍ ያደርጋሉ። እኔስ ወደ ማንከስ ቀርቤአለሁና፥ ቍስሌም ሁልጊዜም በፊቴ ነውና። በደሌን እናገራለሁና፥ ስለ ኃጢአቴም እተክዛለሁ። ጠላቶቼ ሕያዋን ናቸው ይበረቱብኝማል፥ በጠማማነትም የሚጠሉኝ በዙ። ጽድቅን ስለ ተከተልሁ፥ በበጎ ፋንታ ክፉን የሚመልሱልኝ ይጠሉኛል። አቤቱ፥ አንተ አትጣለኝ፤ አምላኬ፥ ከኔ አትራቅ። አቤቱ መድኃኒቴ፥ እኔን ለመርዳት ፍጠን።’’
መቼም በመንፈሳዊ ህይወት በማደግ የምናየው መለኮታዊ አሰራር በመንፈሳዊ ህይወት የልጅነታችን ወቅት ፈጽሞ ሊታወቅ ያዳግታል፤ ምክኒያቱም እግዚአብሄር ያየኛል ሊያድነኝም ፈጥኖ ይመጣል አንልም፤ ከፈተና በሁዋላ መታደስ ይሆናል፣ እንደገናም ማደግና ደስታ ይከተላል ፈጽሞ ልንል አንችልም፤ ትኩረታችን የሚሰማን ህመም ላይ ስለሆነ በርሱ ተይዘን ከማጉረምረምና ከማልቀስ አልፈን የእግዚአብሄርን እጅ በማመን በመገለጡ ደስታ ውስጥ ልንሆንና ልናመሰግን እንዴት እንችላለን?
ነገር ግን በእግዚአብሄር ፊት ሰው ተፈልጎአል
ሉቃ10:25-37 ‘’እነሆም፥ አንድ ሕግ አዋቂ ሊፈትነው ተነሥቶ። መምህር ሆይ፥ የዘላለምን ሕይወት እንድወርስ ምን ላድርግ? ​አለው።እርሱም በሕግ የተጻፈው ምንድር ነው? እንዴትስ ታነባለህ? አለው።እርሱም መልሶ፦ ጌታ አምላክህን በፍጹም ልብህ በፍጹም ነፍስህም በፍጹም ኃይልህም በፍጹም አሳብህም ውደድ፥ ባልንጀራህንም እንደ ራስህ ውደድ አለው።ኢየሱስም፦ እውነት መለስህ፤ ይህን አድርግ በሕይወትም ትኖራለህ አለው።እርሱ ግን ራሱን ሊያጸድቅ ወድዶ ኢየሱስን፦ ባልንጀራዬስ ማን ነው? አለው።’’
አንዳንዴ ራስን በአምላክ ፊት በቅን ልብ ማቅረብና መፈተሽ ብንለምድ እጅግ መልካም መፍትሄ እናገኛለን፤ ከፈለግን ያቀረብነው እኛነታችን ምን እንደሚመስል ወይም የህይወት ደረጃችን የት ላይ እንዳለና ጉድለታችን የቱ እንደሆነ እርሱ ሊያሳየን ይችላል፤ በአምላካዊ ምክርና ተግሳጽ መታነጽ ግን የእኛ ፈንታ ነው፤ ለምሳሌ ያ ህግ አዋቂ ሲናገር ራሱን ሊያጸድቅ ወድዶ የተናገረው ንግግር ቢሆንም ጌታ ኢየሱስ ግን በሚያቀና መንገድ ህይወቱን የሚያሳይ ምሳሌ አቅርቦለት መፍትሄውን አሳይቶታል፦
‘’…ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አለ፦ አንድ ሰው ከኢየሩሳሌም ወደ ኢያሪኮ ወረደ በወንበዴዎችም እጅ ወደቀ፤ እነርሱም ደግሞ ገፈፉት ደበደቡትም በሕይወትና በሞት መካከልም ትተውት ሄዱ።ድንገትም አንድ ካህን በዚያ መንገድ ወረደ አይቶትም ገለል ብሎ አለፈ።እንዲሁም ደግሞ አንድ ሌዋዊ ወደዚያ ስፍራ መጣና አይቶት ገለል ብሎ አለፈ።አንድ ሳምራዊ ግን ሲሄድ ወደ እርሱ መጣ አይቶትም አዘነለት፥ቀርቦም ዘይትና የወይን ጠጅ በቍስሎቹ ላይ አፍስሶ አሰራቸው፥ በራሱ አህያም ላይ አስቀምጦት ወደ እንግዶች ማደርያ ወሰደው ጠበቀውም።በማግሥቱም ሁለት ዲናር አውጥቶ ለባለቤቱ ሰጠና። ጠብቀው፥ ከዚህም በላይ የምትከስረውን ሁሉ እኔ ስመለስ እከፍልሃለሁ አለው።እንግዲህ ከነዚህ ከሦስቱ በወንበዴዎች እጅ ለወደቀው ባልንጀራ የሆነው ማንኛው ይመስልሃል? እርሱም፦ ምሕረት ያደረገለት አለ። ኢየሱስም፦ ሂድ አንተም እንዲሁ አድርግ አለው።’’
ተግባር የገለጠ ህይወት አስፈላጊ ነው

ከፍ ያለና ባዶ የሆነ ንግግር የሚናገር ሳይሆን በተግባር በሚገለጽ ርህራሄና ደግነት የተገለጠ ደግ ሰው በፈጣሪው ዘንድ ሁሌም ይፈለጋል፤ እንዲህ ያለ ሰው ለችግረኛና ለምስኪን የሚያስብ ነው አለ እግዚአብሄር። ለተቸገረው ወንድሙ የሚያስብ፣ የልብ ትርታውን የሚያደምጥና የሚጨነቅለት፣ በርሱ ቦታ ሆኖ ህመሙን የሚታመም፣ ችግሩን የሚረዳ፣ ጭንቀቱን በእውነተኛ ሰሜት ውስጥ ሆኖም የሚካፈል ሰው በእግዚአብሄር ፊት ሞገስ ያለው ነው። ያ ምስኪን ባዶ ሆኖ እጁን የሚሞላለት ደግ ሰው ሲጠባበቅ የሚደርስለት ሩህሩህ ቢኖር በእግዚአብሄር ዘንድ ሞገስ ያገኛል፤ የእለት ጉርሱን የሚሸምትበት ሳይኖረው፣ የሚደርበውን አልባስም ሽቶ በእጦትና በብርድ የሚቆራመደውን አይቶ ያልደነደነ ሩህሩህ እግዚአብሄር ይፈልገዋል።
መክ.5:10-14 ‘’ብርን የሚወድድ ሰው ብርን አይጠግብም፤ ባለጠግነትንም የሚወድድ ትርፉን አይጠግብም፤ ይህም ደግሞ ከንቱ ነው። ሀብት ሲበዛ የሚበሉት ይበዛሉ፤ ሀብቱን በዓይኑ ብቻ ከማየት በቀር ለባለቤቱ ምን ይጠቅመዋል? እጅግ ወይም ጥቂት ቢበላ የሠራተኛ እንቅልፍ ጣፋጭ ነው የባለጠጋ ጥጋብ ግን እንቅልፍን ይከለክለዋል። ከፀሐይ በታች የሚያሳዝን ክፉ ነገር አየሁ፤ ለመከራው በባለቤቱ ዘንድ የተቈጠበች ባለጠግነት ናት። ያችም ባለጠግነት በክፉ ነገር ትጠፋለች፤ ልጅንም ቢወልድ በእጁ ምንም የለውም።’’
እግዚአብሄርን አምናለሁ እያልን በተግባር የማንኖረውን ቃል ብናስተጋባ ቆይቶ የሚከተለው ነገር መልካም አይደለም፤ ደጋግመን ያልነው ነገር እኛን በሰው ፊት መፈተኑ አይቀርም፣ ማሳጣቱም አይቀርም፣ እንዲሁም እፍረት ሳያለብሰን አያቆምም፤ ህሊና ስላለን ያን ብርቱ የሚያቀና የህይወት ክፍል በማሸማቀቅ ራሳችንን ወደ ባርነት ለማስገባት መሯሯጥ ተገቢ አይደለም። ለዚህ ነው በእግዚአብሄር ለመታየት የሚሻ ሰው እርሱ አስቀድሞ ባልንጀራውን ማየት እንዲያስፈልገው ቅድመ-ሁኔታ በእግዚአብሄር የተቀመጠው፤ ወንድም ለወንድሙ እንዲያስብና እንዲራራ በእግዚአብሄር ስለተፈለገ ነው።
ባለጠጋው እግዚአብሄር የሰጠውን በረከት በካዝናው ውስጥ ቆልፎ ወዲያና ወዲህ እንዲል ሳይሆን በምድሪቱ ላይ ያሉትን እንዲያስብበት ነው፤ እግዚአብሄር አበክሮ እነዚህን ባለጠጎች ይቀሰቅሳል፣ ባለጠጎች እናንተ እጃችሁን ዘርጉና አቅም ያጠራቸውን ድረሱ፣ እጅ ያጠራቸውን ደግፉ፤ እኔ ደግሞ ባቃታችሁ፣ ባስቸገራችሁና በእጃችሁ ባለው ገንዘብ መቋቋም የማትችሉት ፈተናም በቀረባችሁ ጊዜ ለእናንተ እኔ ከፊት ሆኜ ልስራ ይላል እግዚአብሄር።
1ጢሞ.6:17-19 ‘’በአሁኑ ዘመን ባለ ጠጎች የሆኑት የትዕቢትን ነገር እንዳያስቡ፥ ደስም እንዲለን ሁሉን አትርፎ በሚሰጠን በሕያው እግዚአብሔር እንጂ በሚያልፍ ባለ ጠግነት ተስፋ እንዳያደርጉ እዘዛቸው። እውነተኛውን ሕይወት ይይዙ ዘንድ፥ ለሚመጣው ዘመን ለራሳቸው መልካም መሠረት የሚሆንላቸውን መዝገብ እየሰበሰቡ፥ መልካምን እንዲያደርጉ በበጎም ሥራ ባለ ጠጎች እንዲሆኑ፥ ሊረዱና ሊያካፍሉም የተዘጋጁ እንዲሆኑ ምከራቸው።’’
ምስጉን ሰው
እግዚአብሄር ያመሰገነው ይህ ሰው ሞገስ ከእርሱ የተቀበለ፣ ምህረትን ከእርሱ ያገኘ ብቻ ነው፤ እርሱ እግዚአብሄር የተመለከተው ሰው፣ ልቡ የቀናም ስለሆነ ተቀባይነት ያለው ነው፤ የምስጋናው መነሻ ከእግዚአብሄር የተቀበለውን በጎነት ለሰዎች ማካፈል መቻሉ ነው፤ ብዙ ጨካኝ፣ ዘራፊ፣ ነጣቂና ራስ ወዳድ ባለጠጎች ባሉበት አለም እግዚአብሄርን የሚያስደስት ልብ ያለው ሰው ማግኘት አስገራሚ ነው፤ በእግዚአብሄር ለመመስገንና ምህረት ለማግኘት እግዚአብሄር ወዳመለከተህ ተመልከት፦ ወደ ችግረኛውና ወደ ምስኪኑ አይንህን አንሳ። አዎ ምስጉን ሰው የእግዚአብሄርን ቸርነት ስለሚያውቅ ቸርነት ያደርጋልና፣ የተቀበልኩትን እኔም እሰጣለሁ፣ እንደተማርኩ እኔም ለተጨነቀው ደርሳለሁ የሚል ልብ አለውም።
ችግረኛና ምስኪን ማሰብ
የተቸገረን ማድረግ ባለመቻሉም የተጨነቀን መድረስ፣ በአሳብ ወደ ህይወቱ ደርሶ መመልከት፣ ቤቱን ጓዳውንም በምህረት ፈትሾ መፍትሄ መስጠት ቢኖር ያ ትልቅ በረከት ነው፦ ማሰብ መቻል ነው፣ አእምሮን ለበጎ ነገር ማዘንበል ትልቅ በራስ መተማመን ነው፤ ጨካኝ ቀማኞች ባሉበት አለም ሆዳቸው የሚባባ ለችግረኛው የሚራሩ ምስጉኖች መገኘታቸው የእግዚአብሄር ምህረት ተገልጦላቸው ነው፤ አንድ ሃብታም ሰው በሩ ላይ የተቀመጠ ችግረኛን ማየት አቃተው፣ ድሃው ውሾች ቁስሉን እስኪልሱት ተቸገረ፣ ባለጠጋው ግን አቅም ያጣ ምስኪን ደጁ ተቀምጦ ማየት ያልቻለው አሳቡ ሌላ በመሆኑ ነው፤ እግዚአብብሄር ግን ያን ሃብታምና ችግረኛ በአንድ ሚዛናዊ አተያይ ተመልክቶ ስለነበር በሆነው ነገር አዘነ።
ትኩረት ባለበት ስፍራ ልብ ማለትና ማስተዋል ሊኖር ግድ ነው፤ ስለዚህ እግዚአብሄር በሚፈልግብን ነገር ላይ አሳብን ማድረግ ከእግዚአብሄር ዘንድ ብዙ መልካም ነገር ይስባል፤ የእግዚአብሄርን ፈቃድ ካላወቅን ግን በርሱ አሳብ ውስጥ ያለውን ዋና ነገር አናስተውልም፣ በዚያ ምክኒያት ማግኘት ያለብንን እናጣለን፣ መቀበል የነበረብንን እናሳልፋለን፣ ይህም የሁልጊዜ የሰው ልጆች ጉድለት ነው፤ እግዚአብሄር ግን በማስተዋል ከባረከን መመልከት የምንችልበትን የእይታ ጉልበት ይሰጠናል።
​​​​​​​​አሳቡ ወደ በጎ ስራ ያዘነበለውን እግዚአብሄር ያስበዋል
መዝ.52:6-7 ‘’ጻድቃን አይተው ይፈራሉ፤ በእርሱም ይሥቃሉ እንዲህም ይላሉ። እግዚአብሔርን ረዳቱ ያላደረገ፥ በባለጠግነቱም ብዛት የታመነ፥ በከንቱ ነገርም የበረታ ያ ሰው እነሆ።’’
ሌባ ባለጸጋን አስቡት፣ ነፍሰ-ገዳይ ሃብታምን አስቡት ወይም ወንበዴ ባለሃብትን በህሊናችሁ ሳሉት፤ እስቲ የዚህ ሰው ሃብት ለህይወቱ ምን የሚረባ ነገር ያደርግለታል? በአመጽ ምክኒያት ከተቀመጠው ፍርድና እርግማን ማን ያስጥለዋልስ? ምን ያህልስ ይደሰትበታል ( ደስታ ከፈጠረለት)? ያንን በደንብ አቅርቦ መመልከት ከእያንዳንዳችን ይፈልጋል።
ነገር ግን ቅንና ንጹህ ልብ ውስጥ የሚፈልቅ ታናሽ በጎነት በቸሩ አምላክ ፊት ይጎላና ብዙ በረከት ይወልዳል፤ እግዚአብሄር የልብ አምላክ ነውና። በጣም ታናሽ ነገር በማድረግ እጅግ ብዙ ምህረት መቀበል ትልቅ ነገር ነው፤ ከእኛ የሚጠየቀው ካለን ነገር እጅግ ያነሰውን ቢሆንም እንኳ በእምነትና በትህትና ብንሰጥ እግዚአብሄር ይቀበለዋል፤ እግዚአብሄር የልባችንን ቅን ዝንባሌ በማየት ለነገራችን ብዙ እጥፍ አትረርፎ ይመልሳል፤ እግዚአብሄርን ረዳቱ ያላደረገ በባለጠግነቱም ብዛት የታመነው ግን ከስሮአል።
ልቡን ላቀና የእግዚአብሄር መልስ ብዙ እጥፍ ነው፤ እግዚአብሄር በክፉ ቀን ያድነዋል፦ በጎ ያሰበውን ሰው የሚያይ ጌታ ይህን ያደርጋል፤ ያ ሰው ለተራበው ምናልባት የሰጠው ታናሽ ዳቦና ጥቂት ውሃ ነው፤ እግዚአብሄር ግን መጠኑን ሳይሆን ልቡን አይቶ ምህረቱን ይሰጠዋል፤ በደግ ቀን የሰራት ጥቂት ነገር በክፉ ቀን በእግዚአብሄር ዘንድ ትታሰብና ደህንነት ታመጣለች፦ ይህን የሚያደርግ አምላክ የታመነና እውነተኛ ነው።