ለማን ብዬ ልስማ?[2…]

ቤተክርስቲያን

ለማን ብዬ ልስማ – ለማን ብዬ ልሰማ ነው፣ ለራሴ ስል ካልሆነ፡፡የሚያጠፋኝ ብዙ ብዙ ነገር በአለም ውስጥ ስላለ እራሴን ለማዳን ስል ለራሴ ብዬ ቃሉን ልሰማ ተገቢ ነው፤ አለፍ ሲል ደግሞ ሌሎችን አድን ዘንድም ስለሚባለው ነገር ተጠንቅቄ ልሰማ ተገቢ ነው፣ ጠንቅቆ ያለመስማት ሰሚውንም አድማጩንም እኩል የሚያጠፋበት ጊዜ ስላለ ማለት ነው፡፡ በአለም ውስጥ  የሚሰሙት እጅግ የበዙ፣ የተወሳሰቡና ሊያጠፉ የሚችሉ ድምጾች የእግዚአብሄር ጥበብ በተገለጠባቸው ቃሎች መታረቅ ያለባቸው ናቸው፡፡ የአለም ድምጾች አለምን አሳምነውም ሆነ ገዝተው መምራት ይችላሉ፤ ድምጾቹ አእምሮንና አሳብን ስለሚቆጣጠሩ ተጽእኖአቸው ከፍተኛ ነው፤ እንዲሁም የሚናገሩት በአለም ፍላጎት ልክ ነው፡፡ አንድ አማኝ በአለም እስከኖረ ድረስ እለት በእለት አለም የምትለውን እየሰማ ነው የሚኖረው፡፡ ከእርሱዋ ስርአት ከፍ ብሎ ሊኖር ካስፈለገ ግን የግድ በአለም ድምጽና ስርአት ሳይያዝ መኖር መቻል አለበት፤ እራሱን ለአለም አሳብና ምኞት ሳያስገዛ ከፍ ብሎ መቀመጥ አለበት፡፡ ወደ ራሳችን ነገሩን ስንመልስ በዚህ አንጻር ለህይወታችን ምሪት ሆኖ እንዲጠቅመን  ዙሪያችን ከሚሽከረከረው ድምጽ ይልቅ ለእግዚአብሄር ቃል ቅድሚያ መስጠት ከጥፋት የሚያስመልጥ ጥበብ ስለመሆኑ ቀጥሎ ያለውን የዳዊት ታሪክ እንመልከት፡-
1ሳሙ.23:1-6 ”ለዳዊትም፡- እነሆ፥ ፍልስጥኤማውያን ቅዒላን ይወጋሉ፥ አውድማውንም ይዘርፋሉ የሚል ወሬ ደረሰው።ዳዊትም፡- ልሂድን? እነዚህንስ ፍልስጥኤማውያን ልምታን? ብሎ እግዚአብሔርን ጠየቀ፤ እግዚአብሔርም ዳዊትን፡- ሂድ፥ ፍልስጥኤማውያንን ምታ ቅዒላንም አድን አለው። የዳዊትም ሰዎች፡- እነሆ፥ በዚህ በይሁዳ መቀመጥ እንፈራለን፥ ይልቁንስ በፍልስጥኤማውያን ጭፍሮች ላይ ወደ ቅዒላ ብንሄድ እንዴት ነው? አሉት።ዳዊትም ደግሞ እግዚአብሔርን ጠየቀ፤ እግዚአብሔርም መልሶ፡- ፍልስጥኤማውያንን በእጅህ አሳልፌ እሰጣለሁና ተነሥተህ ወደ ቅዒላ ውረድ አለው።ዳዊትና ሰዎቹም ወደ ቅዒላ ሄዱ፥ ከፍልስጥኤማውያንም ጋር ተዋጉ፤ እንስሶቻቸውንም ማረኩ፥ በታላቅም አገዳደል ገደሉአቸው። ዳዊትም በቅዒላ የሚኖሩትን አዳነ።”
ዳዊት በዚያ ሰአት ሶስት ድምጾችን በአንድነት ሰማ፤ ድምጾቹ የሚያደነጋግሩ ቢመስሉም ተረጋግቶ እንዲወስን የርሱን አስተዋይነት የሚጠይቁ ነበሩ፡፡ ስለዚህ ዳዊት ሰማ፡- ስለፍልስጤማውያን ድል ማድረግ የሚያስደነግጥ ወሬ ሰማ፤ እግዚአብሄርን ሲጠይቅም ከእግዚአብሄር የሚያደፋፍር ቃል ሰማ፤ የርሱ የሆኑ ሰዎች ደግሞ የሚያስፈራራ ነገር ሲናገሩት ያንንም ሰማ፡፡ ከሰማቸው ድምጾች በሁዋላ ዳዊት አስተውሎ መውሰድ ስለነበረበት ድምጽ ወሰነ፤ እጅግ አስተዋዩ ሰው  ዳዊት በእግዚአብሄር ቃል የታመነ ሰው ነበረና የሚበጀውን ድምጽ ተከትሎ በመውጣት ከጥፋት አመለጠ፡፡
በሌላ በኩል እራሴን ለማዳን ስል ለራሴ ብዬ ልስማ ማለት ቃሉ ወደ እኔ የመጣው ለከንቱ እንዳልሆነ ላስተውልና በአትኩሮት ላዳምጠው ማለት ነው፡፡ የእግዚአብሄር ቃል የሚመጣው ውስጣችን ድረስ ዘልቆ በመግባት መሰራት ያለበትን ስራ ሊሰራ እስከሆነ ድረስ በአይመለከተኝም መንፈስ ገሸሽ ልናደርገው የሚያስችል ብቃት የለንም፡፡ ጉድለታችን፣ ጥፋታችንና ውስንነታችን ከተቀመጠበት ልባችን ድረስ ዘልቆ እንዲሰራ ለቃሉ መፍቀድ አስፈላጊ ነው፡፡ የልቡን ጉዋዳ የዘጋ ጉድለቱንና ጥፋቱን ደብቆና አምቆ የያዘ ሰው ነው፡፡ ለታዛዥ ሰው ግን የእግዚአብሄር ቃል የሚሰራና የሚለውጥ ሀይል ነው፡፡
​​​​​​​​ሐዋ.10:44-46 ”ጴጥሮስ ይህን ነገር ገና ሲናገር ቃሉን በሰሙት ሁሉ ላይ መንፈስ ቅዱስ ወረደ። ከጴጥሮስም ጋር የመጡት ሁሉ ከተገረዙት ወገን የሆኑ ምዕመናን በአሕዛብ ላይ ደግሞ የመንፈስ ቅዱስ ስጦታ ስለ ፈሰሰ ተገረሙ፤በልሳኖች ሲናገሩ እግዚአብሔርንም ሲያከብሩ ሰምተዋቸዋልና።”
እግዚአብሄር ለከንቱ አይናገርም፡፡ ስለዚህ እግዚአብሄርን በዚህ እውቀት የሚያውቁ ሁሉ የእግዚአብሄርን ድምጽ በትግስት ይጠባበቃሉ፡፡

  • መዝ.50:1-2 ”የአማልክት አምላክ እግዚአብሔር ተናገረ፥ ከፀሓይም መውጫ ጀምሮ እስከ መግቢያዋ ድረስ ምድርን ጠራት። ከክብሩ ውበት ከጽዮን እግዚአብሔር ግልጥ ሆኖ ይመጣል።”
  • ​​​​​​​​መዝ.60:6 ”እግዚአብሔር በቅድስናው ተናገረ፤ ደስ ይለኛል።”
  • ​​​​​​​​መዝ.77:5-10 ”የዱሮውን ዘመን አሰብሁ፤ የዘላለሙን ዓመታት አሰብሁ፤ አጠናጠንሁም በሌሊት ከልቤ ጋር ተጫወትሁ፥ ነፍሴንም አነቃቃኋት። እግዚአብሔር ለዘላለም ይጥላልን? እንግዲህስ ቸርነቱን አይጨምርምን? ለዘላለምስ ምሕረቱ ለልጅ ልጅ ተቈረጠችን? የተናገረውስ ቃል አልቆአልን? እግዚአብሔርስ ሞገሱን ረሳን? በቍጣውስ ምሕረቱን ዘጋውን?ይህ ድካሜ ነው አልሁ፥ የልዑል ቀኝ እንደ ተለወጠ።”

የእግዚአብር ቃል ህይወት በመሆኑ ይናፈቃል፣ መልስ በመሆኑ ይጠበቃል፣ የሚሰራ በመሆኑ ይታመኑታል፡- ያ ስለሆነ የመጣላቸውን አበርትቶአል፣ ከሞት አስነስቶአል፣ አድሶአል፣ መንፈስ ቅዱስ እንዲወርድባቸው አድርጎአል፣ አጽንቶአል፡፡ ድምጹን የሚወዱ የቃሉ ሀይል እንደሚለውጣቸው ያውቃሉና ይናፍቁታል፣ ስለዚህ ዝም አትበል ተናገረኝ ይላሉ፣ እግዚአብሄርን፡፡
ዘዳ.30:9፤10 ”የአምላክህንም የእግዚአብሔርን ቃል ብትሰማ፥ በዚህም ሕግ መጽሐፍ የተጻፉትን ትእዛዙንና ሥርዓቱን ብትጠብቅ፥ በፍጹምም ልብህ በፍጹምም ነፍስህ ወደ አምላክህ ወደ እግዚአብሔር ብትመለስ፥ እግዚአብሔር በአባቶችህ ደስ እንዳለው በመልካሙ ነገር ሁሉ እንደ ገና በአንተ ደስ ይለዋልና አምላክህ እግዚአብሔር በእጅህ ሥራ ሁሉ በሆድህም ፍሬ በከብትህም ፍሬ በእርሻህም ፍሬ እጅግ ይባርክሃል።”
ያደጉ አማኞች ስለሚያስተውሉ የቃሉን ድምጽ በጾም በጸሎት ይፈልጋሉ፣ ይጠባበቃሉ፤ አመጸኞች በተቃራኒው አልሰማም ሲሉ ያንገራግራሉ፡፡ እነዚህ ሁለት ነገሮች በአጠቃላይ የአማኞችን ባህሪ ያንጸባርቃሉ፤ የሚሰሙም የማይሰሙም በቤቱ ስላሉ፡፡ ሁልጊዜ የልብ አመጽ የእግዚአብሄርን ቃል ከመጠማት ያስቆማል፡፡ ያለ-ቃሉ የምንኖረው ህይወትም መንገድ ይስታል፡፡ ሳሙኤል፣ ዳዊትና ዳንኤልን የመሳሰሉ የእግዚአብሄር ሰዎች ግን ቃሉን የሚጠባበቁ፣ በቃሉ የሚወጡና የሚገቡ ነበሩ፡፡ በዘመናችንም እንደዚህ ያሉ ትሁታን ልብ ያላቸው ያስፈልጋሉ፡፡
በብሉይ ኪዳን ዘመን የነበረ የትንቢት ቃል እግዚአብሄር ለሰው ልጆች የገባውን ተስፋ የሚናገር ነበር፡፡ በዘመናችን የተሰበክልን የምስራች ቃልም የትንቢቱን ፍጻሜና የተስፋውን እውን መሆን የሚያስረዳ ነው፤ መፍራት ያለብን ግን ቸልተኝነት እንዳያሸንፈንና የሰማነውን እንዳንጥል ነው፡፡ በጥንት ዘመን እስራኤላውያን ከእግዚአብሄር የሰሙትን ድምጽ ሊከተሉና ሊታዘዙ ያለመቻላቸውን ቃሉ እንዲህ ያመለክተናል፡-
​​​​​​​​ዕብ.4:1-12 ”እንግዲህ ወደ ዕረፍቱ ለመግባት ተስፋ ገና ቀርቶልን ከሆነ፥ ምናልባት ከእናንተ ማንም የማይበቃ መስሎ እንዳይታይ እንፍራ። ለእነዚያ ደግሞ እንደ ተነገረ ለእኛ የምስራች ተሰብኮልናልና፤ ዳሩ ግን የሰሙት ቃል ከሰሚዎቹ ጋር በእምነት ስላልተዋሐደ አልጠቀማቸውም።’’ ይላል፡፡
ዛሬ ስንሰማ ለራሳችን ብለን እንስማ፣ በእምነት ተዋህዶ ህይወታችንን  እንዲሰራ በማስተዋልም እንስማ፡፡ ቃሉ እየተመረጠ የሚጣል ምራጭ ፍሬ የለውም፣ የሚበጠር ሳይሆን የነጠረና የጠራ ነው፤ ወደ እኛ የሚላከውም እንዲሰራን ነው፡፡
የህያው እግዚአብሄር ቃል ፈቃዱን ወደ እኛ ይዞ በመጣ ጊዜ ቃሉ እንደአመጣጡ እንዲለውጠን ሆኖ በውስጣችን ካልገባ አይጠቅመንም፣ ለዚያም አሰማማችን ወሳኝ ነው፡፡ አሰማማቸውን ያላስተካከሉትን እግዚአብሄር ሲገስጻቸው እንደተናገረው፡-
”… ሥራው ዓለም ከተፈጠረ ጀምሮ ምንም እንኳ ቢፈጸም፡- እንዲህ ወደ ዕረፍቴ አይገቡም ብዬ በቁጣዬ ማልሁ እንዳለ፥ እኛስ ያመንን ወደ ዕረፍቱ እንገባለን። ስለ ሰባተኛው ቀን በአንድ ስፍራ፡- እግዚአብሔርም በሰባተኛው ቀን ከሥራው ሁሉ ዐረፈ ብሎአልና፤ በዚህ ስፍራም ደግሞ፡- ወደ ዕረፍቴ አይገቡም። እንግዲህ አንዳንዶች በዚያ እንዲገቡ ስለ ቀሩ፥ ቀድሞም የምስራች የተሰበከላቸው ባለመታዘዝ ጠንቅ ስላልገቡ፡- ዛሬ ድምፁን ብትሰሙት ልባችሁን እልከኛ አታድርጉ በፊት እንደ ተባለ፥ ይህን ከሚያህል ዘመን በኋላ በዳዊት ሲናገር፡- ዛሬ ብሎ አንድ ቀን እንደ ገና ይቀጥራል።’’ ይላል፡፡
ሆኖም እግዚአብሄር ከግብጽ ባርነት ያዳናቸውና ክንዱን የሚያውቁ የእግዚአብሄርን ድምጽ ከመጠባበቅና ቃሉን ከመናፈቅ አፈግፍገው ስለነበር ከመንገድ ቀርተዋል፡፡ እግዚአብሄር ባሳዩት እልከኝነት ስላልተደሰተ ቁጣውን በምድረበዳ አወረደባቸው፡፡
በሌላ በኩል የእግዚአብሄርን ባህሪ ያስተዋሉ ትሁታን የሚለዩባቸውን መንገዶች እናያለን፣ ከዚህም ውስጥ ዋነኛው ለቃሉ የሚሰጡት ስፍራ ነው፡፡ እነዚህ ድምጹን የሚወዱ አማኞች  የቃሉ ሀይል እንደሚለውጣቸው ያውቃሉና ይናፍቁታል፣ እግዚአብሄርን በየእለቱ ዝም አትበል ተናገረኝ ይላሉ፡፡
’’…የእግዚአብሔር ቃል ሕያው ነውና፥ የሚሠራም፥ ሁለትም አፍ ካለው ሰይፍ ሁሉ ይልቅ የተሳለ ነው፥ ነፍስንና መንፈስንም ጅማትንና ቅልጥምንም እስኪለይ ድረስ ይወጋል፥ የልብንም ስሜትና አሳብ ይመረምራል..” (ዕብ.4:12)
ህያው ቃሉ ለነፍሳችን ህይወትን ስለሚሰጥ ልንቀበለው የግድ ነው፤ መንፈሳችን ውስጥ በመግባት መለኮታዊ ስራ ስለሚሰራም ቸል ልንለው አንችልም፡፡ረቂቅ ቃሉ ሀይል ስላለው በሰው ሀይል መሆን የማይችለውን በውስጣችን ያከናውናልና በቃሉ ለመሰራት ብለን መስማት ይገባናል፡፡
ቃሉን የተቀበሉ የተለወጡበትና ያደጉበት አማኞች ጥቅሙን ስለሚያስተውሉ የቃሉን ድምጽ በጾም በጸሎት አዘውትረው ይፈልጋሉ፣ ቃሉም በከንቱ ወደነርሱ አይመጣም፣ እንደአመጣጡ በከንቱ አይመለስም፣ የታረሰ የልብ እርሻ አግኝቶ እንደሆነ  የህይወት ዘር በዚያ ያኖራል እንጂ፡-
​​​​​​​​ኢሳ.55:10-12 ”ዝናብና በረዶ ከሰማይ እንደሚወርድ፥ ምድርን እንደሚያረካት፥ ታበቅልና ታፈራም ዘንድ እንደሚያደርጋት፥ ዘርንም ለሚዘራ እንጀራንም ለሚበላ እንደሚሰጥ እንጂ ወደ ሰማይ እንደማይመለስ፥ ከአፌ የሚወጣ ቃሌ እንዲሁ ይሆናል፤ የምሻውን ያደርጋል የላክሁትንም ይፈጽማል እንጂ ወደ እኔ በከንቱ አይመለስም።”
ከእግዚአብሄር አፍ የሚወጣ ቃል የእግዚእሄርን ፈቃድ ወደ ሰው ይዞ ሲመጣ በዘመናት መሃል  ያሰበው ስራው በምድር ይገለጣል፡፡  ቃሉ እርሱ የሚሻውን ከመፈጸም ሌላ በከንቱ ወደ እርሱ እንደማይመለስ እግዚአብሄር ተናግሮአልና፡፡
​​​​​​​​በያዕ.1:22 ሲናገር  ”ቃሉን የምታደርጉ ሁኑ እንጂ ራሳችሁን እያሳታችሁ የምትሰሙ ብቻ አትሁኑ።” በማለት  የሰማነውን ቃል  በመተግበር መታዘዛችንን እንድናሳይ ያሳስበናል፡-
​​​​​​​​መዝ.103:20 ”ቃሉን የምትፈጽሙ፥ ብርቱዎችና ኃያላን፥ የቃሉንም ድምፅ የምትሰሙ መላእክቱ ሁሉ፥ እግዚአብሔርን ባርኩ።”
ራስን መስማት
ሰው ራሱን በመመርመር ደረጃ ውስጡን ሊያዳምጥ ይገባዋል፡፡ ፍላጎቱን፣ እቅዱን፣ እምነቱንና ስሜቱን ያውቅ ዘንድ የውስጡን ጩሀት  መስማት አለበት፡፡ በህይወታችን ውስጥ ለሚከሰቱ ነገሮች አጸፋዊ የሆኑ በጎ ነገሮች ማፍለቅ የሚቻለው ሚዛናዊነት ያለው ውሳኔ ሲኖረን በመሆኑ ውስጣችንን ሁሌም እየፈተሸን መዘጋጀት የግድ ይላል፡፡ ከውስጥ የሚሰማንን በውጪ ካለው እውነታ ጋር እንዴት አብረን እናስኪደው? በእኛ ያለውስ በዙሪያችን ካለው ጋር እንዴት ይስተያያል? እነዚህን በትክክል ለመመለስ ውስጥን አትኩሮ መስማት ያስፈልጋል፡፡
ከዚህ በመለስ ግን ከውስጤ የሰማሁት እርሱ ነው ትክክል ከርሱ ሌላ ምን አግዶኝ ማለት አይቻልም፡፡ የኔ የህይወት ዝግጅት የራሴን የውስጤን ድምጽ እየሰማሁ እንዳልታለል ሊጠብቀኝ ይገባል (በስጋ ፍለጎት አነሳሽነት ይሁን የመንፈስ ድምጽ፣ ማንኛውንም ለመረዳት ውስጤ የሚጮሀውን ድምጽ መለየት ይገባነኛል እንጂ ለተሰማኝ ነገር ብቻ አድልቼ እርሱን መከተል የለብኝም)፡፡
ጌታ ተናገረኝ የሚል ንግግር የሚያበዙ በብዙ ሲስቱ ይስተዋላል፡፡ ለምን? ቢባል ድምጹን ስለማይለዩ፡፡ ሁልጊዜ የመንፈስ አቅጣጫችን የምናየውንና የምንሰማውን  ድምጽ ይወስናል፡፡ በእግዚአብሄር አቅጣጫ የቆመ ሰው ከእግዚአብሄር የሚሰማው ድምጽ አለ፡፡ ድምጹ በህሊናው፣ በጆሮው፣ በህልሙ በራእይ.. በብዙ መንገድ ሊመጣ ይችላል፤ ግን ሁሉንም በሀላፊነት፣ በሸክምና በትህትና መስማት አለበት፡፡ ደግሞም የድምጹን መንፈስ በህያው ቃሉ አንጻር መተርጎም አለበት፤ ያለበለዚያ በጣም መሳት እንዳይሆን ያስፈራል፡፡
ኢዮ.33:14-19 ”እግዚአብሔር በአንድ መንገድ በሌላም ይናገራል፤ ሰው ግን አያስተውለውም። በሕልም፥ በሌሊት ራእይ፥ አፍላ እንቅልፍ በሰዎች ላይ ሲወድቅ፥ በአልጋ ላይ ተኝተው ሳሉ፥ በዚያን ጊዜ የሰዎችን ጆሮ ይከፍታል፥ በተግሣጹም ያስደነግጣቸዋል፥ሰውን ከክፉ ሥራው ይመልሰው ዘንድ ከሰውም ትዕቢትን ይሰውር ዘንድ፤ ነፍሱን ከጕድጓድ፥ በሰይፍም እንዳይጠፋ ሕይወቱን ይጠብቃል። ደግሞ በአልጋ ላይ በደዌ ይገሥጸዋል፥ አጥንቱንም ሁሉ ያደነዝዛል።”