ለመመለስ መንቃት

ቤተክርስቲያን

የአምነት ጉዞንና የባህር ጉዞን የሚያመሳስሉ ሰዎች አሉ፤ ምክኒያታቸውን ሲያስረዱ አንድ ሰው የእምነት ጉዞን ሲጉዋዝ  አገኛለሁ ብሎ የሚጠብቀውን መንፈሳዊ ነገር ተስፋ አድርጎ እንጂ በእጁ ጨብጦ የሚጉዋዝ አለመሆኑ፣ በባህር ላይ የሚደረግ ጉዞም የሚታይ ነገር ከፊት ሳይኖር በእምነት ብቻ መዳረሻን አልሞ ወደተገመተ አቅጣጫ የሚቀዝፍበት መሆኑ ነው፤ ባህርተኛው በእምነት ከሆነ ጊዜ በሁዋላ እደርሳለሁ ወዳለው ሩቅ ስፍራ እንደሚደርስ በማሰብ የሚጉዋዝም መሆኑ ነው፡፡ በእምነት ጉዞ ውስጥ መሪ የሆነውን አምላክ ቃል ተከትለን እንጉዋዛለን እንጂ በእጃችን የተጨበጠ ማረጋገጫ ይዘን እርሱን አንከተልም፣ ሳያዩ የሚያምኑ ብጹአን ናቸው ብሎአልም፤ መርከበኛም ቢሆን በአይኑ የሚያያትን አገር አግኝቶ ሳይሆን በእጁ ያለችው ኮምፓስ ወደሚፈልገው ምድር አቅጣጫ እንደምትመራው ታምኖ ሰፊውን ባህር የሚያቆራርጥ ነው የሚሆነው፡፡
ትልቁና ዋነኛው እውነታም ይሄ ነው፡- የባህር ጉዞ ሁሌም በአደጋ የተከበበ ነው፤ ባህር ላይ በሚነፍስ አውሎ ነፋስ መመታትም ይኖራል፣ በባህሩ ሞገድ ሀይል የመርከብ መገልበጥም ሊከሰት ይችላል፣ ካልተጠነቀቁ በባህር ውስጥ ሀያል አሳዎች መዋጥም ሌላ ስጋት ነው፡፡ ሁሎችም ስጋቶች ግን በህይወት የሚመጡ ስጋቶች እንደመሆናቸው ህይወት በባህር ጉዞ ላይ ከፍተኛ ጭንቀት እንዲያገኘው ይሆናል፡፡
መንፈሳዊ ህይወት በጌታ ካለው መጽናናትና ከለላ ውጪ ስጋት ያለበት ነው፡- አለም፣ ስጋና ሰይጣን ከብበውታልና፡፡እነዚህ ሶስት ሀይሎች ዳግም የተወለደውን መንፈስ ያጠቃሉ፣ ያጎሰቁላሉ፣ ያደክማሉ ሲቻላቸው ይማርካሉ፡፡ ስጋትነታቸው እስከ ግድያ እንደሚደርስ እናስተውላለን ወይ? (ከእግዚአብሄር የተለየ መንፈስ ሙት እንደመሆኑ)፡፡ እነዚህን ማእበሎች የሚቁዋቁዋም ውስጣዊ ብርታት ከጌታ የተቀበልነው መንፈስ ብቻ ነው፣ የነርሱ ማእበል ኢላማ ግን ያንን ሀይል ማስጣል ነው፡፡
ከላይ ያየነው ስጋት የሚያደርሰው ጥፋት እንዳለ ሆኖ በሌላ አቅጣጫ የሚታይ መሳት (መስመር መልቀቅ) የሚባል ሌላ አደጋ ሊፈጥር ይችላል፤ መሳት ከኮምፓስ ምሪት መውጣትና ተገፍቶ ወደ ባህር መካከል መግባት፣ ወጀብና አውሎ ነፋስ ወደሚያይልበት አቅጣጫም መገስገስ ያስከትላል፡፡ ያንን ሁሉ ስጋት ያስወግድ ዘንድ የመርከቡ ካፒቴን እጅግ ይደክማል፣ የጫነውን ህዝብ በሰላም ወደ ምድር ያደርስ ዘንድ ከፍተኛ ሃላፊነት ተሸክሞአልና መፍትሄ እስኪያገኝ እረፍት አያገኝም፡፡
መርከብ አደገኛ አውሎነፋስ አግኝቶአት ብትመታ ልትሰበር ትችላለች፣ ሳትሰበር ብትተርፍ እንኩዋን ወደማይገባ አቅጠጫ እስከተጉዋዘች ድረስ ስጋቱ ከፍተኛ ነው፡፡ በመትረፍዋ እፎይታ ቢሆንም ከማእበል በስቲያ የአቅጣጫዋ ነገር አሳሳቢ ነው፡- የመጨረሻ ማረፊያዋ ምድር/ወደብ እንዲሆን የጉዞ አቅጣጫዋ ወደየት እንደሆነ ማወቅ ስለሚገባ ያን ማረጋገጥ አሰገዳጅ ነው፤ ያ ካልሆነ አቅጣጫዋም ካልተለየ ከባህሩ አደጋ መትረፍና ምድርን መገናኘት የሚቻል አይሆንም፡፡ ስለዚህ ከወጀብና ከአውሎነፋስ እንግልት በሁዋላ አእምሮ በተረጋጋ ወቅትና የመጣው አስፈሪ ሁከት ባለፈ ጊዜ ካፒቴኑ እንደገና ወደ ትክክለኛው የጉዞ አቅጣጫ መርከቢቱን ያስገባ ዘንድ መስራት ሊጀምር ግድ ነው፡፡ ዋና ትኩረቱን የሚያደርገውም ወደ መነሻው የጉዞ መስመር መመለስ እንጂ አዲስ አቅጣጫን መፍጠር ሊሆን አይችልም፡፡
በዚህ አለም ያለው የአማኝ ኑሮ ምቾት የሚጠብቀው እንደሆነ ወይም የተመቻቸ ነገር እንደሚቀርብለት እግዚአብሄር ቃል አልገባም፤ ይልቅ በአለም ሳላችሁ መከራ አለባችሁ ሲል ልባችን እረፍትና ጸጥታን ብቻ የሚናፍቅ እንዳይሆን፣ እንዲያውም የተመቻቸ በሚመስል ነገር ውስጥ ሰጥመን እንዳንዘናጋና እንዳናንቀላፋ ቃሉ ይመክረናል፡፡ ስለዚህ ቀን በሚያመጣው ክፋትና ውጣ ውረድ ተይዘን እንደመርከብዋ ስንንገላታ ብንቆይም ፈተናችን ጋብ በሚል ሁኔታ ውስጥ ስንገኝ የሚቀጥለው እርምጃ ራሳችንን ወደ ተሰመረልን የህይወት መስመር ውስጥ ማስገባት እንጂ አቁዋራጭ አካሄድ ልንመርጥ እንደማይገባ እርግጠኛ መሆን ያስፈልጋል፡፡
​​​​​​​​ኤር.6:16 ”እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፡- በመንገድ ላይ ቁሙ ተመልከቱም፥ የቀደመችውንም መንገድ ጠይቁ፤ መልካሚቱ መንገድ ወዴት እንደ ሆነች እወቁ፥ በእርስዋም ላይ ሂዱ፥ ለነፍሳችሁም ዕረፍት ታገኛላችሁ።” ስለሚል ፡፡
የሃዋርያው ጳውሎስ የመርከብ ጉዞን እንደ ምሳሌ ለማየት የሚከተለውን ጥቅስ ማንበብ ይጠቅማል፡-
​​​​​​​​ሐዋ.27:12-22 ” ..ያም ወደብ ይከርሙበት ዘንድ የማይመች ስለ ሆነ፥ የሚበዙቱ ቢቻላቸው በሰሜንና በደቡብ ምዕራብ ትይዩ ወዳለው ፍንቄ ወደሚሉት ወደ ቀርጤስ ወደብ ደርሰው ይከርሙ ዘንድ ከዚያ እንዲነሡ መከሩ። ልከኛም የደቡብ ነፋስ በነፈሰ ጊዜ፥ እንዳሰቡት የሆነላቸው መስሎአቸው ተነሡ በቀርጤስም አጠገብ ጥግ ጥጉን አለፉ። ነገር ግን እጅግ ሳይዘገይ አውራቂስ የሚሉት ዓውሎ ነፋስ ከዚያ ወረደባቸው፤ መርከቡም ተነጥቆ ነፋሱን ሲቃወም መሄድ ስላልቻለ ለቀነው ተነዳን። ቄዳ በሚሉአትም ደሴት በተተገንን ጊዜ ታንኳይቱን ለመግዛት በጭንቅ ቻልን፤ወደ ላይም ካወጡአት በኋላ መርከቡን በገመድ አስታጥቀው አጸኑ፤ ስርቲስም ወደሚሉት ወደ አሸዋ እንዳይወድቁ ፈርተው ሸራውን አውርደው እንዲሁ ተነዱ። ነፋሱም በርትቶ ሲያስጨንቀን በማንግሥቱ ከጭነቱ ወደ ባሕር ይጥሉ ነበር፥ በሦስተኛውም ቀን የመርከቡን ዕቃ በእጃችን ወረወርን። ብዙ ቀንም ፀሐይን ከዋክብትንም ሳናይ ትልቅ ነፋስም ሲበረታብን ጊዜ፥ ወደ ፊት እንድናለን የማለት ተስፋ ሁሉ ተቈረጠ።
ሳይበሉም ብዙ ቀን ከቆዩ በኋላ፥ ያን ጊዜ ጳውሎስ በመካከላቸው ቆሞ እንዲህ አለ። እናንተ ሰዎች ሆይ፥ ሰምታችሁኝ በሆነ ኖሮ ከቀርጤስ እንዳትነሡ ይህንም ጥፋትና ጕዳት እንዳታገኙ ይገባችሁ ነበር። አሁንም። አይዞአችሁ ብዬ እመክራችኋለሁ፤ ይህ መርከብ እንጂ ከእናንተ አንድ ነፍስ እንኳ አይጠፋምና።”
የማይመች ከባቢ
ተጉዋዦቹ ያረፉበት ወደብ ይከርሙበት ወይም በዚያ ያሳልፉበት ዘንድ የማይመች ስፍራ ሆኖ ነበር፤ በዚህ ምክኒያት የሚበዙቱ ቢቻላቸው በሰሜንና በደቡብ ምዕራብ ትይዩ ወዳለው ፍንቄ ወደሚሉት ወደ ቀርጤስ ወደብ ደርሰው ይከርሙ ዘንድ ከዚያ እንዲነሡ መከሩ። ያ ስፍራ ድንገት የባህር ሞገድ ተነስቶ የሚከድነው አካባቢ ስለሆነ በዚያ ስፍራ በዚያን ወቅትም መክረም እጅግ አደገኛ ነበርና ወደ ተሻለ ስፍራ መጉዋዝ የሚበጅ አማራጭ ሆኖ አገኙት፡፡
የዚህ ገጠመኝ ምሳሌ የእኛን መንፈሳዊ ህይወት ከበባ ሊወክል ይችላል፤ የማያንጽ ከባቢ ውስጥ ብንሆን ወደፊት ምን ሊገጥመን ይችላል ብለን ካላሰብን አደጋው በመርከቢቱ ላይ እንደሆነው ድንገት በእኛም ላይ ይወርድብናል፡፡ መንፈሳዊ ህይወትን የሚያናጉ ብዙ ነገሮች አሉ፤ ምክኒያቶቹ ከውጪ የሚመጡብን ፈተናዎች ብቻ አይደሉም፤ እኛው ራሳችን ራሳችንን ያስገባንበት የማይመች ሁኔታ (ለስጋ ህይወታችን ሙሉ ሆኖ ቢሰማን እንኩዋን) መንፈሳዊ ህይወታችን ላይ አደጋ የሚደቅን ሊሆን ይችላልና ውስጣችንን ስናዳምጥ  ያለመመቸት/እረፍት የማጣት ምልክት ካለ ምክኒያቱን በማስተዋል ወደፊት በዚያ መቆየት አደጋ እንደሚሆን ወስኖ ከሁኔታው ውስጥ በአስቸኩዋይ መልቀቅ ተገቢ ነው፡፡
ልከኛ ሂደት መሳይ ሁኔታ  
ተጉዋዦቹ ከሚያስፈራው ወደብ መልቀቅን መርጠው በዚያ ውሳኔ ጉዞ ጀምረዋል፤ መልቀቃቸውን ብቻ የተመለከቱት መንገደኞች የጉዞአቸውን መስመር ሁኔታ ፈትነው ሳያረጋግጡ ነበር የተነሱት፤ ስለዚህ ልከኛ የደቡብ ነፋስ በነፈሰ ጊዜ፥ እንዳሰቡት የሆነላቸው መስሎአቸው ተነሡ፣ በቀርጤስም አጠገብ ጥግ ጥጉን አለፉ። እነዚህ ሰዎች እየሸሹ የነበሩት ከአውሎነፋስ ነበር፤ ሆኖም ከአንድ የአውሎነፋስ ክስተት አምልጠው ሌላ አውሎነፋስ ውስጥ እንዳይገቡና ህይወታቸውን መልሰው አደጋ ውስጥ እንዳይከትቱ ጉዞቸውን ማጤን/መሰለል አልቻሉም ነበር፡፡
እንደመንፈሳዊ ሰው ህይወትን የሚጎዳና የሚሸረሽር ሁኔታ ተቀባይነት ስለማይኖረው/ትእግስት ስለማያስፈልገው አፋጣኝ ውሳኔ ማድረጉ ተገቢ ነው፡፡ ግን ቀጣዩ አካሄድስ? በየትኛው አቅጣጫ ይሁን ጉዞው? በጉዞውስ ላይ ምን ሊመጣ ይችላል? በዚህ ጥያቄ ጉዞ ይፈተሻል፤ ነገ የሚሆነውን አናውቅም፣ ይሄ እርግጥ ነው፤ የዛሬው ቀን መልክ ግን የነገን ስሜት ሊያመላክተን ይችላልና ዛሬ ምሸቱ ከዳመነ የነገን ዝናብ መገመቱ አይከፋም፡፡ በተመሳሳይ ወቅቱ  በመንፈሳዊ ህይወት ላይ ሁከትን የሚጋብዝ መሆኑን ካመንን የሚቀጥለውን ወቅት በጥንቃቄ መጠባበቅ ተገቢነት የለውምን? ይሄ ስለመሰለኝ፣ ስለመሰለው ወይም መስሎአቸው የሚባል አጉል ሰበብ የጥፋት ምክኒያት ነው፡፡ በክረምቱ ወራት ደመናው ከብዶ ሳለ ዝናብ አይመጣም ብሎ መደምደም አይቻልም፣ በባህር/ውቅያኖስ አካባቢ የሚኖሩ ሰዎች እንደሚያደርጉት ወጀቡና ውሽንፍሩ እጅግ ተንጠራርቶ/አኮብኩቦ ባለበት ወቅት ጸሀይ እንኩዋን ብትወጣ የጊዜውን ጸጥታ መጠርጠር እጅግ ተገቢ ነው፡፡
ትኩረትን የሚያቃውስ ክስተት
እነዚያ የባህር ተጉዋዦች ለአጭር ጊዜ በሚቆይ ሰላም ተዘናግተው ባህር መሀከል ገብተዋል፤ የወቅቱን መንፈስ አልተገነዘቡምና፡፡ እጅግ ሳይዘገይ አውራቂስ የሚሉት ዓውሎ ነፋስ ከዚያ ወረደባቸው፤ መርከቡም ተነጥቆ ነፋሱን ሲቃወም መሄድ ስላልቻለ ለቀውት ተነዱ። ያ ፈርተው የተሸሸጉት ፈተና ብዙም ሳይቆዩ እንደገና ደረሰባቸው፡፡ የነፋሱ ሀይል መንገዳቸውን አሳተው፣ መርከባቸው የሚቁዋቁዋምበት የቀረ ጉልበት አልነበረውምና ተወሰደ እነሱም ተስፋ ቆርጠው የመርከቡን ቁጥጥር ለነፋሱ ተዉ፡፡
እኛንም ጠላት ወጀብ አስነስቶ በዚያ መሀል ካስገባን በሁዋላ ቀድሞ በመንፈሳዊ ነገሮች ላይ እናደርግ የነበረውን ጥንቃቄ እንድንጥል ያደርጋል፡፡ አያስፈልግም የምንለውን እንድናደርግ፣ የተውነውን እንድናነሳ፣ ፊታችንን የመለስንባቸው ነገሮች ዋና ተፈላጊ ሆነው ህይወታችንን እንዲገዳደሩ ያደርጋል፡፡ በዚያ ሳቢያ ተስፋ ቆርጠን ሁሉን እርግፍ አድርገን እንጥላለን፡፡
የተሸከምነውን የምንጥልበት የጭንቅ ወቅት
ፈተና የተጠራቀመ ሀይል፣ ንብረት፣ እውቀት ብቻ የትኛውም የኛ ነው ብለን የምንቆጥረውን ነገር ሁሉ ስለሚያረግፍ ያስደነግጣል፣ ተስፋም ያስቆርጣል፡፡ ልክ በመርከቢቱ ላይ ተሳፍረው የነበሩ ነፋሱ በርትቶ ሲያስጨንቃቸው ከጭነቱ ወደ ባሕር ይጥሉ እንደነበር፥ ተሳፋሪዎች በሙሉ የያዙትን እያንዳንዱን ንብረት ከእጃቸው እስኪጥሉ ድረስ ባዶአቸውን አስቀርቶአቸው እንደነበር ማለት ነው፡፡ ፈተና አእምሮን ስለሚሰርቅ መጣል ያለብን የትኛው መሆኑን እስከምንዘነጋ ያደርሳል፤ የመርከቢቱ ተሳፋሪዎች በማእበሉ ጭንቀት ምክኒያት ለህልውናቸው የሚገባውን ሳይቀር ጥለው እንደነበር ተመዝግቦአል፡፡
​​​​​​​​1ጴጥ.1:6-7 ”በዚህም እጅግ ደስ ይላችኋል፥ ነገር ግን በእሳት ምንም ቢፈተን ከሚጠፋው ወርቅ ይልቅ አብልጦ የሚከብር የተፈተነ እምነታችሁ፥ ኢየሱስ ክርስቶስ ሲገለጥ፥ ለምስጋናና ለክብር ለውዳሴም ይገኝ ዘንድ አሁን ለጥቂት ጊዜ ቢያስፈልግ በልዩ ልዩ ፈተና አዝናችኋል።”
አንድንም የሚል ተስፋ መቁረጥ
ፈተናው በርትቶ ብዙ ነገራችን መውደቁ ሳያንስ የፈተነን ወጀብ የጭንቁንና የፍርሀቱን ጥልቀት ስለሚያጋባብን በእግዚአብሄር ላይ የሚኖረንን መታመን ይቆረጣል፤ እንደዚሁ ከመርከቢቱ ተጉዋዦች የሰማነው የሀዘን ድምጽ የወረደባቸው  ማእበል  ፍርሀታቸውን ከፍ አድርጎት እንደነበር አመልካች ነው፡-
”ብዙ ቀንም ፀሐይን ከዋክብትንም ሳናይ ትልቅ ነፋስም ሲበረታብን ጊዜ፥ ወደ ፊት እንድናለን የማለት ተስፋ ሁሉ ተቈረጠ።” ብለዋል፡፡ ጨለማ፣ ጭጋግ፣ አውሎነፋስ፣ ጥማት፣ ረሀብ ሲረባረቡባቸው እንድናለን ወይ? የሚለው ጥያቄ መልስ የሚያገኝ አልመሰላቸውም፡፡
​​​​​​​​መዝ.107:23-32 ”በመርከቦች ወደ ባሕር የሚወርዱ፥ በታላቅ ውኃ ሥራቸውን የሚሠሩ፥እነርሱ የእግዚአብሔርን ሥራ፥ በጥልቅም ያለችውን ድንቁን አዩ።ተናገረ፥ ዐውሎ ነፋስም ተነሣ፥ ሞገድም ከፍ ከፍ አለ።ወደ ሰማይ ይወጣሉ ወደ ጥልቅም ይወርዳሉ፤ ነፍሳቸውም በመከራ ቀለጠች።ደነገጡ እንደ ስካርም ተንገደገዱ፥ ጥበባቸውም ሁሉ ተዋጠች።በተጨነቁ ጊዜ ወደ እግዚአብሔር ጮኹ፥ ከመከራቸውም አዳናቸው።ዐውሎንም ጸጥ አደረገ፥ ሞገዱም ዝም አለ።ዝም ብሎአልና ደስ አላቸው፤ ወደ ፈለጉትም ወደብ መራቸው።ለሰው ልጆች ስላደረገው ተአምራት ስለ ምሕረቱም እግዚአብሔርን ያመስግኑ።በአሕዛብ ጉባኤ ከፍ ከፍ ያድርጉት፥ በሽማግሌዎችም ሸንጎ ያመስግኑት።”
ወደ ቀደመው መንገድ መመለስ
የቀደመው  መንገድ/በመነሻቸው ላይ ያቀዱት የጉዞ መስመር በእቅድ ውስጥ የነበረ የመርከቢቱ መንገድና ወደ መዳረሻ የሚያደርስ ትክክለኛ አቅጣጫ ያለበት ነበር፡፡ ለዚያ አማራጭና አቁዋራጭ መጠቀም የተሸለ መፍትሄ ስለማያስገኝ መስመርዋን የሳተች መርከብ መጀመሪያውኑ ወዳለመችው አቅጣጫ ልትመለስ የግድ እንደሆነ የምንገነዘበው ጉዳይ ነው፡፡ እንዲሁም መንገዳቸውን ለሳቱ የጭንቁንም መንገድ ለሚሄዱ ወገኖች ሳይታደኑ በፊት የሚታደግ የእግዚአብሄር ምሪት ሊቀድም እጅግ አስፈላጊ ነው፡፡
​​​​​​​​በመዝ.32:8 ላይ ሲናገር ”አስተምርሃለሁ በምትሄድበትም መንገድ እመራሃለሁ፤ ዓይኖቼን በአንተ ላይ አጠናለሁ።” ብሎአልና፡፡
የተገለጠ የእግዚአብሄር ማዳን እንደቃሉ ጣልቃ ካልገባ የሰው አማራጭ ብዙ ፈቀቅ አያደርግም፤ ስለዚህ የጭንቅ መንገድ በእግዚአብሄር ምሪት አቅጣጫ ገብቶ መፍትሄ ካልተገኘ የመንገዳችን ጫፍ ጥፋት እንደሆነ ጥርጥር የለውም፡፡
​​​​​​​​መዝ.107:4-9 ”ውኃ በሌለበት ምድረ በዳ ተቅበዘበዙ፤ የሚኖሩበትንም ከተማ መንገድ አላገኙም። ተራቡ ተጠሙም፥ ነፍሳቸውም በውስጣቸው አለቀች። በተጨነቁ ጊዜ ወደ እግዚአብሔር ጮኹ፥ ከመከራቸውም አዳናቸው፤ ወደሚኖሩበት ከተማ ይሄዱ ዘንድ የቀና መንገድን መራቸው። ለሰው ልጆች ስላደረገው ተኣምራት ስለ ምሕረቱም እግዚአብሔርን ያመስግኑ፤ የተራበችን ነፍስ አጥግቦአልና፥ የተራቈተችንም ነፍስ በበረከት ሞልቶአልና።”