ህይወት የሚገኝበት ትምህርት

የእውነት እውቀት

ዕብ.10:19-20 “እንግዲህ፥ ወንድሞች ሆይ፥ በመረቀልን በአዲስና በሕያው መንገድ ወደ ቅድስት በኢየሱስ ደም በመጋረጃው ማለት በሥጋው በኩል እንድንገባ ድፍረት ስላለን፥…“
እግዚአብሄር በአዲስ ኪዳን የከፈተው አንድ ብቸኛ መንገድ ህይወት ያለበት መንገድ ነው።ህያው መንገድ ህያው አምላክ የሚገለጥበት አዲስ የህይወት ስርአት ነው።ህያዋን የሆኑ በመንፈስ የተወለዱ ነፍሳትም ይመላለሱበታል።ህያዋን የሆኑ እነዚህ መንፈሳውያን ከመንገዱ ሳይለቁ ጸንተው እንዲኖሩ እግዚአብሄር የህይወት ትምህርትን ይገልጥላቸዋል።ህይወት የሚገኝበትን ትምህርት መቀበልና ለርሱ መኖር ትግል ያለው ቢሆንም ልብን ማቅናት የሚችል እውቀት የሚገኘው በእርሱ ብቻ ነው።
ህይወት የሚገኝበት መንገድ እግዚአብሄር ለሰው ልጆች የመረቀው፣የፈቀደውና ጸጋ የሚገለጥበት መንገድ ነው። የህይወት መንገድ ህይወት የሆነው ጌታ ክብሩን የሚገልጥበት መንገድ ነው።መንገድ መነሻና መድረሻ ያለው እንደመሆኑ የህይወት መንገድ መነሻው ኢየሱስ መድረሻውም ኢየሱስና መንግስቱ ነው።ጌታ ኢየሱስ እውነት መንገድና ህይወት እንደሆነ ተናግሮአል(ዮሃ14፣ 2)።
መንገዱ ጽድቅ የሚገኝበት መንገድ ስለሆነ በጽድቅ የማይሄዱትን አንገዋልሎ ከመንገድ ያወጣል።በአለምም ፊት ያጋልጣቸዋል። ህይወት የሚገኝበት መንገድ እውነት የሚገኝበት መንገድ ስለሆነ በሃሰትና ሃሰትን በመለማመድ የሚሄዱትን አማኞች ይወቅሳል።
2ጢሞ.4:2-3 “ቃሉን ስበክ፥ በጊዜውም አለጊዜውም ጽና፥ ፈጽመህ እየታገሥህና እያስተማርህ፥ ዝለፍና ገሥጽ ምከርም። ሕይወት የሚገኝበትን ትምህርት የማይታገሡበት ዘመን ይመጣልና…“
ህይወት የሚገኝበት ትምህርት ጌታ ኢየሱስን የሚተርክ ትምህርት ነው።ትምህርቱ ኢየሱስ ክርስቶስን  በማመን ስለሚገኝ ህይወት ይናገራል።ትምህርቱ በአለም ካሉ ተቃራኒ ትምህርቶች ጋር ፊት ለፊት የመጋጠምና የመታገል ባህሪይ ስላለው በትምህርቱ ላይ የቆመን አማኝ ትግስት መፈታተኑ አይቀርም።በአለም የሚኖሩ ሰዎች ትምህርቱ ስለሚወቅሳቸው ሊቀርቡት አይወዱም።የህይወታቸውን ይዘት በመመርመርና ስውር ማንነታቸውን በመግለጥ ስለሚያስደነግጣቸው በብዙዎች ልብ ውስጥ ቁጣ ይፈጥራል።
ህይወት የሚገኝበት ትምህርት የሞት ትምህርትን የመቁዋቁዋምና የማሸነፍ ጉልበት አለው።የሞት ትምህርት የሃጢያት መንፈስ ያለበትና የእውነት ተቃርኖ ከሆነ እምነት የሚመነጭ ነው።የህይወት ትምህርትን ዘወትር የሚቃወሙ ሰዎች ወደ መዳን እንዳይመጡ ሃጢያት መሰናክል ይሆንባቸዋል።የተለያዩ ሃይማኖቶች የተለያዩ ትምህርቶችን ያሰራጫሉ።ትምህርቶቻቸው ከእግዚአብሄር ይሁን ከሰይጣን ያልያም አለማዊ ወይም ሰዋዊ መሆኑን ቃሉ ይመረምረዋል፣ይገልጠዋልም።
ህይወት የሚገኝበት ትምህርት ደህንነት ያለበት ትምህርት እንደመሆኑ ደህና ትምህርት ተብሎአል (1ጢሞ9፣11)፣ እንዲሁም መልካም ትምህርት (1ጢሞ4፣6) እና እግዚአብሄርን ለመምሰል የሚስማማ ትምህርት(1ጢሞ6፣3) እንደሆነ ተጠቅሶአል።
ህይወት የሚገኝበት ትምህርት  በመንፈሳዊ ህይወት ህጻናት የሆኑ አዲስ አማኞች እንዲጸኑ የሚመክር ነው(እብ5፣12)። ትምህርቱ  በእምነት የበረቱትንም አማኞች ፍጹማን የሚሆኑበትን እውቀት ይሰጣል (እብ6፣1-2)።ህይወት የሚገኝበት ትምህርት ለሌሎች ምስክር የሚሆን ትምህርት ነው(1ጴጥ.3:1-2)። ትምህርቱ የክርስቶስ ትምህርት ነው(2ዮሃ.9)። ጌታ በምድር አገልግሎቱ ቀድሞ ያስተማረውን ባሪያዎቹ ደግመው አስተምረውታል።ዛሬም እንደተናገረው ሰለረሱ ይሰበካል።​​​​
ህይወት የሚገኝበት ትምህርት በአጠቃላይ፦
-በመታዘዝ በቤቱ የሚኖሩትን ለመምከር ይረዳል
-ባለመታዘዝ መንገዳቸውን የሚያበላሹትን ይወቅሳል
-ትምህርቱ ደህንነትን ያስተምራል
-ጭምት ህይወት እንድንኖር፣ ጤናማና የማይነቀፍ ንግግርን የሚገልጥ አስተማሪ ያደርጋል(ቲቶ2፣7-8)
ህይወት የሚገኝበት ትምህርት ምንጭ፦
ህይወት የሚገኝበት ትምህርት የእግዚአብሄር መጽሃፍ ነው።ትምህርቱ የቃሉ ብርሃን በሚያበራበት ስፍራ ሁሉ ይገኛል።የቃሉን ትምህርት ጉልበት ቸል ብለው በልባቸው ፍቃድ የሚሄዱና የሚያስተምሩ ወደ ስህተት ይወድቃሉ፣ ሌሎችንም ያሳስታሉ።ከእግዚአብሄር የወጣ ቃል መንፈስና ህይወት እንደሆነ ቃሉ ይመሰክራል።ሰለዚህ ዘላለማዊ ህይወትን ከጌታ ኢየሱስ ሊሰማ የወደደ ከአፉ የወጣውን ቃል መቀበል ይገባዋል።
እንግዳ ትምህርት
እንግዳ ትምህርት ህይወት የሚገኝበት ትምህርት ጠላት ነው።እንግዳ ትምህርት ጽድቅን ይዋጋል።እንግዳ ትምህርት ህይወት የሚገኝበት ትምህርት ውስጥ ጣልቃ የሚገባ አሣሳች ትምህርት ነው።እንግዳ ትምህርቶች ልዩ ትምህርቶች (1ጢሞ1፣3-4) ናቸው። ትምህርቶቹ መጨረሻ ወደሌለው ተረት ተረት ውስጥ ይከታሉ። ተጨባጭ ያልሆኑ ነገሮችንም ያስተምራሉ።ሰውን ተረትና ታሪክ ተራኪ ያደርጋሉ።በመጽህፍ ቅዱስ ውስጥ የተጠቀሱ እንግዳ ትምህርቶች የእግዚአብሄርን እቅድና አላማ የሚቃረኑ ነበሩ። የበለአም ትምህርት (ራእ2፣14) የእግዚአብሄርን ህዝብ ያሳተ ነበር። የኒቆላውያንም ትምህርት (ራእ2፣15) እንደዚሁ።እንግዳ ትምህርቶች ምንጫቸው አንድ እርሱም ሰይጣን ነው(ራእ2፣24)። እንግዳ ትምህርትን ወደ ቤተክርስቲያን አሾልከው የሚያስገቡ አስተማሪዎች በሚያስቱ መናፍስት የተጠቁ፣ ውሸተኞችና ግብዞች ናቸው።
የመጨረሻው ዘመን ዋና መለያ ህይወት የሚገኝበት ትምህርት ላይ በክህደት መነሳትና ማመጽ ነው።እግዚአብሄርን እናውቃለን የሚሉ በተግባር ግን የሚክዱ ሰዎች የማይጸኑት ትምህርቱን መታገስ ስለማይችሉ ነው። ህይወት የሚገኝበትን ትምህርት ስለማይታገሱም በአጋንንት ትምህርት ይማረካሉ።የህይወት ትምህርት የጽድቅ ትምህርት ስለሆነ በጥፋት መንገድ የሚሄዱትን ጆሮአቸውን የሚያሳክክ ይሆናል፣ምቾታቸውንም ይነሳል።
ማቴ.16:12 “እነርሱም ከፈሪሳውያንና ከሰዱቃውያን ትምህርት እንጂ ከእንጀራ እርሾ እንዲጠበቁ እንዳላላቸው ያን ጊዜ አስተዋሉ።“
እስራኤላውያን ጌታ ኢየሱስን አምነው እንዳይከተሉ ታላቅ እንቅፋት በህዝቡ ፊት አኑረው ያጠፉት እነዚህ አስተማሪዎች ነበሩ። ትውልዳቸው ከእግዚአብሄር መንግስት እንዲወገድ ያደረጉ ክፉ አስተማሪዎች ወደ ወገኖቹ የመጣውን ጌታም እስከቀራኒዮ መስቀል ድረስ የተቃወሙት አደገኛ ሰዎች ነበሩ።
​​​​​​​​1ጢሞ.1:3-4 “ወደ መቄዶንያ በሄድሁ ጊዜ፥ አንዳንዶች ልዩ ትምህርትን እንዳያስተምሩና ወደ ተረት መጨረሻም ወደሌለው ወደ ትውልዶች ታሪክ እንዳያደምጡ ልታዛቸው በኤፌሶን ትቀመጥ ዘንድ ለመንሁህ፤ እንደ እነዚህ ያሉ ነገሮች ክርክርን ያመጣሉና በእምነት ግን ላለ ለእግዚአብሔር መጋቢነት አይጠቅሙም።“
በየትኛውም ዘመን ለሚነሳ የእግዚአብሄር ህዝብ እንቅፋት የሚያኖሩ ወንድሞች ቸል ከተባሉ በወንድሞቻቸው መሃል ተቀምጠውና በእግዚአብሄር ቤት ሆነው የአጋንንትን ድምጽ ይሰማሉ።በእርሱም ልዩ ትምህርት ያሰራጫሉ።
​​​​​​​​1ጢሞ.4:1-2 “መንፈስ ግን በግልጥ፦ በኋለኞች ዘመናት አንዳንዶች የሚያስቱ መናፍስትንና በውሸተኞች ግብዝነት የተሰጠውን የአጋንንትን ትምህርት እያደመጡ፥ ሃይማኖትን ይክዳሉ ይላል“
የመጨረሻው ዘመን አደገኛ መንፈስ ሰባኪዎችን በትምህርቱ የሚሞላ የሚያደምጡትንም ከእውነት ስተው የስህተት ትምህርቱ ላይ እንዲወድቁና ጌታ የሰጠውን አንድ ሃይምኖት እንዲክዱ የሚያደርግ ነው። ስለዚህ በዘመን መጨረሻ የምንገኝ በጌታ ኢየሱስ ያመንን የምንጠብቀውን የህይወት አክሊል እንድናገኝ በህይወት መንገድ ላይ ተገልጦ የሚገኘውን የህይወት ትምህርት አጥብቀን እንያዝ።ቃሉ  ሲናገር፦
​ዮሐ.8:43-47 “ንግግሬን የማታስተውሉ ስለ ምንድር ነው? ቃሌን ልትሰሙ ስለማትችሉ ነው። እናንተ ከአባታችሁ ከዲያብሎስ ናችሁ የአባታችሁንም ምኞት ልታደርጉ ትወዳላችሁ። እርሱ ከመጀመሪያ ነፍሰ ገዳይ ነበረ፤ እውነትም በእርሱ ስለ ሌለ በእውነት አልቆመም። ሐሰትን ሲናገር ከራሱ ይናገራል፥ ሐሰተኛ የሐሰትም አባት ነውና። እኔ ግን እውነትን የምናገር ስለ ሆንሁ አታምኑኝም። ከእናንተ ስለ ኃጢአት የሚወቅሰኝ ማን ነው? እውነት የምናገር ከሆንሁ እናንተ ስለ ምን አታምኑኝም? ከእግዚአብሔር የሆነ የእግዚአብሔርን ቃል ይሰማል፤ እናንተ ከእግዚአብሔር አይደላችሁምና ስለዚህ አትሰሙም።“
በአካል ከጌታ ጋር በመንፈስ ግን ከጌታ ክብር ክልል ውጪ እንደሆኑት አይሁድ ሳንሆን ቃሉን በየዋሃት ተቀብለው እንደዳኑት እንደሃዋርያቱ እንድንሆን በህያው ቃሉ ላይ ብቻ እንጣበቅ።