ህዝቡን የሚያድን አምላክ[2..]

የእውነት እውቀት

ህዝቡን የሚያድን አምላክ ለሰው ልጆች የሆነ የማዳኑን ብስራት ሲገልጥ በሰማይ የተገለጠው ትእይንት ልብ የሚሞላ ነው፡-
”እነሆም፥ የጌታ መልአክ ወደ እነርሱ ቀረበ የጌታ ክብርም በዙሪያቸው አበራ፥ ታላቅ ፍርሃትም ፈሩ። መልአኩም እንዲህ አላቸው። እነሆ፥ ለሕዝቡ ሁሉ የሚሆን ታላቅ ደስታ የምሥራች እነግራችኋለሁና አትፍሩ፤ ዛሬ በዳዊት ከተማ መድኃኒት እርሱም ክርስቶስ ጌታ የሆነ ተወልዶላችኋልና። ይህም ምልክት ይሆንላችኋል፤ ሕፃን ተጠቅልሎ በግርግምም ተኝቶ ታገኛላችሁ።ድንገትም ብዙ የሰማይ ሠራዊት ከመልአኩ ጋር ነበሩ። እግዚአብሔርንም እያመሰገኑ። ክብር ለእግዚአብሔር በአርያም ይሁን ሰላምም በምድር ለሰውም በጎ ፈቃድ አሉ።”(ሉቃ2:9-14)
የምስራች ነብያት አስቀድመው የተናገሩት፣ መላእክትም በታለቅ ክብር አጅበው ያበሰሩት ይህ የመድሀኒት አዋጅ እንደምን ታላቅ እንደሆነ ከጥቅሱ ማየት ይቻላል፡፡ ደግሞ በነቢዩ ኢሳያስ ትንቢት ውስጥ እንደተነገረው ጽዮን የአምላኩዋ ማዳን ሲቀርብ አስተውላ እንድትነሳና የምስራች እንድትናገር አሳስቦ ነበር፡፡ የጽዮን ምስክር መንፈስ ከፍ ብሎና ወደ አምላኩዋ ተነስቶ ወደ አዋጅ ተራራ መውጣት፣ የምስራች የምትነግር ኢየሩሳሌምም የምስራች እንድትነግር መዘጋጀት እንዳለባት ይህን ሲያሳስብ ድምፅዋን በኃይል አንስታ ለይሁዳም ከተሞች፡- እነሆ፥ አምላካችሁ! ብላ እንድትናገር ይጠበቅ ነበር። አዋጁ ብርቱ ነው፣ ስታውጅ ማን ሊያድን መጣ ብላ ግራ እንዳትጋባ በግልጽ እንዲህ በይ ሲል ይናገራል፡-
”እነሆ፥ ጌታ እግዚአብሔር እንደ ኃያል ይመጣል ክንዱም ስለ እርሱ ይገዛል፤ እነሆ፥ ዋጋው ከእርሱ ጋር ደመወዙም በፊቱ ነው። መንጋውን እንደ እረኛ ያሰማራል፥ ጠቦቶቹን በክንዱ ሰብስቦ በብብቱ ይሸከማል፥ የሚያጠቡትንም በቀስታ ይመራል።”
ይህ ህዝቡን ያድናቸዋልና ስሙን ኢየሱስ ትይዋለሽ ከሚል የመላእክት ቃል ፊት የሄደ ታላቅ የምስራች ነው፡፡ ማዳኑን የሚጠባበቅ ደግሞ እግዚአብሄር ከምን እንዲያድነው በማስተዋል ሊያመልከው፣ ሊገዛለትና ሊወደው ይገባል፤ መድሀኒታችን የተገለጠው በመስዋእት ደህንነትን ሊያቆም ነውና፡-
– እግዚአብሄር ከእርግማን ያድነናል
የእርግማን ቃል ሆነ ንግግር በሰውና በነገሮች ላይ ክፉ ነገርን የሚጠራ፣ መቅሰፍትን የሚስብ፣ ሁከትን የሚፈጥር በአጠቃላይ በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ በሰው ህይወት ውስጥ ጥፋትን የሚያመጣ ከመንፈስ የሆነ የጥፋት ድምጽ ነው፡፡ እርግማን ከመንፈስ የወጣ ንግግር ስለሆነ ከትውልድ ትውልድ (በህዝብ ደረጃ) እንዲሁም ከዘር ወደ ዘር (በግለሰብ ደረጃ፣ ከልጅ ወደ ልጅ እየተላለፈ) የሚሄድና የበቀለን ባለ ተስፋ ትውልድ የሚቀጭ የተረፈውንም ባለመጥፋት ተመላልሶ እየጎበኘ በተመሳሳይ መንገድ የሚያጎሰቁል አደገኛ ቃል ነው፡፡ ሰዎች ይራገማሉ፣ እግዚአብሄርም በሰው አመጽ ምክኒያት ቁጣ የሆነ እርግማን ተናግሮአል፡፡ ሰዎች በተለያየ ምክኒያት ሌሎችን ይራገማሉ፤ በተለይ በመናፍስት የሆነ እርግማን በክፉ መናፍስት እገዛ የሚያከናውን ነው፡፡
እግዚአብሄር ለአዳም ጥብቅ ትእዛዝ ነገረው፣ በትእዛዙ ውስጥ የመተላለፍ ፍርድ ቁጣም ነበረበት፤ ቢሆንም በዚያ በኩል ከእግዚአብሄር ጋር የሚሄድበትን መንገድ ነበር ያመለከተው፡፡ የአዳም መተላለፍ ያን ቁጣ ሳበና የመጀመሪያው መርገም በመጀመሪያው የሰው መተላለፍ ላይ ተገለጠ፡-
ዘፍ.3:17 ”አዳምንም አለው፡- የሚስትህን ቃል ሰምተሃልና፥ ከእርሱ እንዳትበላ ካዘዝሁህ ዛፍም በልተሃልና ምድር ከአንተ የተነሣ የተረገመች ትሁን፤ በሕይወት ዘመንህም ሁሉ በድካም ከእርስዋ ትበላለህ”
ይህ እርግማን አለምንና የሰው ልጅን ቀጣይ የህይወት አቅጣጫ ፈጽሞ ቀይሮአል፡፡ የተፈጠረልን በጎ፣ መልካምና ፍጹም የሆነ ነገር ሁሉ ተበላሽቶአል፤ መልካሙ አምላክ ከእኛ ርቆአል፤ ክብሩንም አጥተናል፡፡ የሰው ልጅ በአእምሮው ክፋት እየጨመረ ሲሄድ፣ አለምም በውስጥዋ የምታበቅለው የአመጽ ብዛት እየጨመረ ሄዶ ነበር፡፡
ከኖህ መዳን በሁዋላ
እግዚአብሄር የአመጻ ብዛትን ከምድር ሊጠርግ በወሰነ ወቅት ቅሬታ ወገን ኖህና ቤተሰቡ ተገኝቶ ነበርና ምድር ለእነርሱ ብቻ ተገብታቸው ነበር፡፡ እግዚአብሄርም ለዚያ ጽናታቸው በረከቱን በእነርሱ ላይ አኖረና በምድር ፊት በሰላም እንዲኖሩ ሰጣቸው፡፡ ቆይቶ ግን ኖህ በምድር ኑሮው ውስጥ የፈጠረው ታላቅ ስህተት እፍረት ወደ ቤተሰቡ አምጥቶበት ነበር፡፡ ኖህ በመጠጥ ብዛት ሰክሮ ራሱን ባዋረደ ወቅት ልጆቹ በሀጢያት እንዲወድቁ በርን ከፈተ፡-
ዘፍ.9:21-24 ”ከወይን ጠጁም ጠጣና ሰከረ፤ በድንኳኑም ውስጥ ዕራቁቱን ሆነ። የከነዓን አባት ካምም የአባቱን ዕራቁትነት አየ፥ ወደ ውጭም ወጥቶ ለሁለቱ ወንድሞቹ ነገራቸው። ሴምና ያፌትም ሸማ ወስደው በጫንቃቸው ላይ አደረጉ፥ የኋሊትም ሄደው የአባታቸውን ዕራቁትነት አለበሱ፤ ፊታቸውም ወደ ኋላ ነበረ፥ የአባታቸውንም ዕራቁትነት አላዩም። ኖኅም ከወይን ጠጁ ስካር ነቃ፥ ታናሹ ልጁ ያደረገበትንም አወቀ።”
የክፉ ሰዎች እርግማን
የእግዚአብሄር እርግማን ተግሳጽ ነው፣ ለጥፋታችን የተወሰነ ቅጣት ነው፡፡ አጋንንት የሚራገሙት ግን ጻድቅን ለማጎሳቆልና ለመቅጠፍ ነው፣ ምስኪኑን አለማዊ እስራት ውስጥ ለመተብተብ ነው፡፡ ሰዎችም በጎ ባልሆነ መንገድ ያን ያደርጋሉ፣ ለባልንጀራቸው ጥፋትን በዚያ መንገድ ያውጠነጥናሉ፡፡ ቀጥሎ የምናያቸው ታሪኮች ያን የሚያሳዩ ናቸው፡-
1ነገ.2:8 ”እኔም ወደ መሃናይም በሄድሁ ጊዜ ብርቱ እርግማን የረገመኝ የብራቂም አገር ሰው የብንያማዊው የጌራ ልጅ ሳሚ፥ እነሆ፥ በአንተ ዘንድ ነው፤ እርሱ ግን ዮርዳኖስን በተሻገርሁ ጊዜ ሊቀበለኝ ወረደ፥ እኔም፡- በሰይፍ አልገድልህም ብዬ በእግዚአብሔር ምዬለታለሁ።”
ዘኊ.23:7-12 ”ምሳሌውንም ይመስል ጀመር፥ እንዲህም አለ፡- ባላቅ ከአራም አመጣኝ፥ የሞዓብ ንጉሥ ከምሥራቅ ተራሮች፤ ና፥ ያዕቆብን ርገምልኝ፤ ና፥ እስራኤልን ተጣላልኝ ብሎ። እግዚአብሔር ያልረገመውን እንዴት እረግማለሁ? በአምቦች ራስ ላይ ሆኜ አየዋለሁ፥ በኮረብቶችም ላይ ሆኜ እመለከተዋለሁ፤ እነሆ፥ ብቻውን የሚቀመጥ ሕዝብ ነው፥ በአሕዛብም መካከል አይቈጠርም።የያዕቆብን ትቢያ ማን ይቈጥራል? የእስራኤልስ እርቦ ማን ይቈጥራል? የጻድቃንን ሞት እኔ ልሙት፥ ፍጻሜዬም እንደ እርሱ ፍጻሜ ትሁን። ባላቅም በለዓምን፡- ያደረግህብኝ ምንድር ነው? ጠላቶቼን ትረግምልኝ ዘንድ ጠራሁህ፤ እነሆም፥ ፈጽመህ ባረክሃቸው አለው። እርሱም መልሶ፡- በውኑ እግዚአብሔር በአፌ ያደረገውን እናገር ዘንድ አልጠነቀቅምን? አለው።”
የተስፋ ቃል አለ
ዘኊ.23:21-26 ”በያዕቆብ ላይ ክፋትን አልተመለከተም፥ በእስራኤልም ጠማምነትን አላየም፤ አምላኩ እግዚአብሔር ከእርሱ ጋር ነው፥ የንጉሥም እልልታ በመካከላቸው አለ። እግዚአብሔር ከግብፅ አውጥቶአቸዋል፤ ጕልበቱ አንድ ቀንድ እንዳለው ነው። በያዕቆብ ላይ አስማት የለም፥ በእስራኤልም ላይ ምዋርት የለም፤ በጊዜው ስለ ያዕቆብና ስለ እስራኤል፡- እግዚአብሔር ምን አደረገ! ይባላል። እነሆ፥ ሕዝቡ እንደ እንስት አንበሳ ይቆማል፥ እንደ አንበሳም ይነሣል፤ ያደነውን አስኪበላ፥ የገደለውንም ደሙን እስኪጠጣ አይተኛም። ባላቅም በለዓምን፡- ከቶ አትርገማቸው፥ ከቶም አትባርካቸው አለው።በለዓምም መልሶ ባላቅን፡- እግዚአብሔር የተናገረውን ሁሉ አደርጋለሁ ብዬ አልተናገርሁህምን? አለው።”
እግዚአብሄር ከነዚህ የክፋት መናፍስት ከሚወጣ ክፉ አሳብ ይታደገናል፣ የእግዚአብሄርን ቃል በመተላለፍ ከሚመጣ እርግማንም እንዲሁ ያድነናል፡-
የዚህን ሕግ ቃሎች ያደርግ ዘንድ የማያጸና ርጉም ይሁን፤ ሕዝቡም ሁሉ አሜን ይላሉ። (ዘዳ.27:26)
ዘዳ.29:19-20 ”የዚህንም እርግማን ቃሎች የሰማ ሰው፡- ምንም እንኳ በልቤ ደንዳንነት ብሄድ፥ ለጥማቴም ስካር ብጨምር፥ ሰላም ይሆንልኛል ብሎ ሰውነቱን በልቡ የሚባርክ ቢኖር፥የእግዚአብሔር ቍጣ ቅንዓቱም በዚያ ሰው ላይ ይጤሳል እንጂ እግዚአብሔር ይቅርታ አያደርግለትም፤ በዚህም መጽሐፍ የተጻፈው እርግማን ሁሉ በላዩ ይኖራል፥ እግዚአብሔርም ስሙን ከሰማይ በታች ይደመስሰዋል።”
የተስፋ ቃል ተገለጠ
እርግማን በሙሉ የጌታ ኢየሱስን መስዋእት የጠየቀ ከፍተኛው የፍጥረት እፍረት፣ ስብራትና ቅጣት ነው፡፡ በተለይ የሰውን ልጅ ለዘለአለም ከእግዚአብሄር የሚለየው እርግማን ምንም አይነት መፍትሄ ሊረው ስላልቻለ የእግዚአብሄር ልጅ የመስዋእት በግ ሆኖ እንዲቀርብ አስገድዶታል፡፡
ጌታ ኢየሱስ ስለ ሰው ልጆች እርግማን ሲል ራሱን ለመስቀል ሞት አሳልፎ ሰጠ፤ በርሱ ዘንድ ያለው ሰውን የመውደዱ ጉልበት በራሱ ሰውነት ላይ መከራ እንዲሸከም አደረገው፡፡
ገላ.3:10-13 ”ከሕግ ሥራ የሆኑት ሁሉ በእርግማን በታች ናቸውና፤ በሕግ መጽሐፍ በተጻፉት ሁሉ ጸንቶ የማይኖር የማያደርግም ሁሉ የተረገመ ነው ተብሎ ተጽፎአልና። ጻድቅ በእምነት ይኖራል ተብሎአልና ማንም በእግዚአብሔር ፊት በሕግ እንዳይጸድቅ ግልጥ ነው።ሕግም ከእምነት አይደለም ነገር ግን፡- የሚያደርገው ይኖርበታል ተብሎአል። በእንጨት የሚሰቀል ሁሉ የተረገመ ነው ተብሎ ተጽፎአልና ክርስቶስ ስለ እኛ እርግማን ሆኖ ከሕግ እርግማን ዋጀን”
በአዲስ ኪዳን የተገለጡ ዋና መርገሞች
ጌታ ኢየሱስ ሰውን ከዚያ የሚያህል ዘላለማዊ ጥፋት አድኖት ሳለ አዳኙን በተለያየ መንገድ የሚክድ ከሆነ ወደ ወጣበት እርግማን ተመልሶ እንደሚወድቅ ቃሉ እንደሚከተለው ያሳስባል፡-
”ጌታን ኢየሱስ ክርስቶስን የማይወድ ቢኖር የተረገመ ይሁን።” (1ቆሮ.16:22)
ጌታ ኢየሱስን ለምን ወደድነው? ስለ እኛ እርግማን ሆኖ ከሕግ እርግማን ስለዋጀን አልነበረምን? ፍቅር ባልነበረን ገና በሀጢያት ህይወት ውስጥ ሳለን ራሱን በመሰዋት ፍቅሩን ሰጥቶን አልነበረምን?
”ነገር ግን እኛ ብንሆን ወይም ከሰማይ መልአክ፥ ከሰበክንላችሁ ወንጌል የሚለይ ወንጌልን ቢሰብክላችሁ፥ የተረገመ ይሁን።”(ገላ.1:8)
– እግዚአብሄር ከወጥመድ ያድነናል
እግዚአብሄር ሰይጣን ከሚዘረጋው ወጥመድ ያስመልጣል (ከመሆኑም በፊት ሆነ ከሆነ በሁዋላ)፡፡
ዕዝ.8:31 ”በመጀመሪያውም ወር በአሥራ ሁለተኛው ቀን ወደ ኢየሩሳሌም እንሄድ ዘንድ ከአኅዋ ወንዝ ተነሣን የአምላካችንም እጅ በላያችን ነበረ፥ በመንገድም ከጠላትና ከሚሸምቅ ሰው እጅ አዳነን።”
ሰይጣን በብዙ የማጥመጃ መንገድ በመያዝ ሰውን ከአምላኩ ጋር ያለያያል፡፡ ሲያጠምድ ከእግዚአብሄር አሳብ ያጎድላል፣ ከመስመርም ያወጣል፡፡
2ቆሮ.1:8-11 ”በእስያ ስለ ደረሰብን መከራችን፥ ወንድሞች ሆይ፥ ታውቁ ዘንድ እንወዳለንና፤ ስለ ሕይወታችን እንኳ ተስፋ እስክንቆርጥ ድረስ ከዓቅማችን በላይ ያለ ልክ ከብዶብን ነበር፤ አዎን፥ ሙታንን በሚያነሣ በእግዚአብሔር እንጂ በራሳችን እንዳንታመን፥ እኛ ራሳችን የሞትን ፍርድ በውስጣችን ሰምተን ነበር። እርሱም ይህን ከሚያህል ሞት አዳነን፥ ያድነንማል፤ እናንተም ደግሞ ስለ እኛ እየጸለያችሁ አብራችሁ ስትረዱን፥ በብዙ ሰዎች በኩል ስለ ተሰጠን ስለ ጸጋ ስጦታ ብዙዎች ስለ እኛ ያመሰግኑ ዘንድ፥ ወደ ፊት ደግሞ እንዲያድን በእርሱ ተስፋ አድርገናል።”
– እግዚአብሄር ከህማምና ከደዌ ያድነናል
ጥፋት፣ መቅሰፍት፣ ሞት፣ በሽታ፣ የመሳሰሉ በሰው ልጅ ህይወት ላይ የሚመጡ መከራዎች በክፉ መናፍስት ይታቀዳሉ፣ ከነርሱ ይወጣሉ፣ በነርሱ ይቀነባበራሉ፣ ይፈጸማሉም፡፡
ደዌ ይመጣል፣ እግዚአብሄር ግን በህመማችን ወቅት አልጋ ያነጥፍልናል፡፡ እንደማንታመም ሳይሆን ስንታመም እርሱ ከአጠገባችን እንደሚሆን ነው ቃል የገባልን፡፡
ዘጸ.15:26 ”እርሱም፡- አንተ የአምላክህን የእግዚአብሔርን ቃል አጥብቀህ ብትሰማ፥ በፊቱም የሚበጀውን ብታደርግ፥ ትእዛዙንም ብታደምጥ፥ ሥርዓቱንም ሁሉ ብትጠብቅ፥ በግብፃውያን ላይ ያመጣሁትን በሽታ አላደርስብህም፤ እኔ ፈዋሽህ እግዚአብሔር ነኝና አለ።”
ዘጸ.23:25-28 ”አምላካችሁንም እግዚአብሔርን ታመልኩታላችሁ፥ እርሱም እህልህንና ውኃህን ይባርካል፤ በሽታንም ከመካከልህ አርቃለሁ። በምድርህም መካን ወይም የምትጨነግፍ አትሆንም፤ የዘመንህን ቍጥር እሞላለሁ። መፈራቴንም በፊትህ እሰድዳለሁ፥ የምትሄድበትንም ሕዝብ ሁሉ አስደነግጣቸዋለሁ፥ ጠላቶችህንም ሁሉ በፊትህ ጀርባቸውን እንዲያዞሩ አደርጋለሁ።በፊትህም ተርብ እሰድዳለሁ፥ ኤዊያዊውንም ከነዓናዊውንም ኬጢያዊውንም ከፊትህ አባርራለሁ።”
መዝ.41:3 ”እግዚአብሔር በደዌው አልጋ ሳለ ይረዳዋል፤ መኝታውን ሁሉ በበሽታው ጊዜ ያነጥፍለታል።”

– እግዚአብሄር ከዘላለም ሞት ያድነናል
ጌታ ኢየሱስ ከእርግማን ሊዋጀን እራሱን እርግማን አድርጎ እንዳቀረበ ከላይ አይተናል፡፡ በርሱ ማንም ያመነ ቢኖር የእርግማን ውጤት ከሆነው ከዘላለም ፍርድ ይታደገዋል፡፡
1ጴጥ.3:20-21 ”ጥቂቶች ማለት ስምንት ነፍስ በውኃ የዳኑበት መርከብ ሲዘጋጅ፥ የእግዚአብሔር ትዕግሥት በኖኅ ዘመን በቈየ ጊዜ ቀድሞ አልታዘዙም። ይህም ውኃ ደግሞ ማለት ጥምቅት ምሳሌው ሆኖ አሁን ያድነናል፥ የሰውነትን እድፍ ማስወገድ አይደለም፥ ለእግዚአብሔር የበጎ ሕሊና ልመና ነው እንጂ፥ ይህም በኢየሱስ ክርስቶስ ትንሣኤ ነው”
ጌታ ኢየሱስ ሲመጣ የሚያገኘን ከነሀጢያታችን ባለንበት ወቅትና ስፍራ ነው፡፡ ወደ እኛ የሚመጣበት አላማም እኛን ከዚያ ካለንበት የህይወት ሁኔታ ማውጣት፣ ማዳንና ለመንግስቱ ማብቃት ነው፡፡ ወደ ህይወታችን በመጣ ጊዜ አስቀድሞ ከሀጢያት ቅጣት ያድነናል፣ ቀጥሎ ከሀጢያት ሀይል ነጻ ያወጣናል፣ በመጨረሻ ከሀጢያት ከበባ ይታደገናል፡፡