ሰውን ለማዳን በጎ ፈቃዱ የሆነና ሁሌም ሊገለጥ የሚፈቅድ አምላክ ሲናገር ተመልከቱና አስተውሉ እንጂ ለማዳን፣ ለመፈወስ፣ ለመምታትም ሆነ ለመግደል የምችለው እኔ እግዚአብሄር ብቸኛው አምላክ ነኝ፣ ይህን እወቁም ሲል አዋጅ ይናገራል፡፡ በተለይ በዘዳ.32:39 ላይ ብርቱ ቃል ሲናገር፡-
”አሁንም እኔ ብቻዬን እኔ እንደ ሆንሁ፥ ከእኔም በቀር አምላክ እንደሌለ እዩ፤ እኔ እገድላለሁ፥ አድንማለሁ፤ እኔ እመታለሁ፥ እፈውስማለሁ፤ የሚያድን የለም።”
እግዚአብሄር እንዲታወቅ፣ እንዲታመንና ሰዎች የእርሱን ማንነት እንድናውቅ መሻቱ ለራሳችን ጥቅም ስለመሆኑ የምናስተውል ወገኖች እጅግም ነን፡፡ ብዙዎች መድሀኒት ነኝ፣ አዳኝ ነኝ፣ ታዳጊ ነኝ፣ ሰጪ ነኝ… ወዘተ እያሉ የእግዚአብሄርን ክብር በሚናጠቁበት አለም እግዚአብሄር ከርሱ በቀር አምላክ ያለመኖሩን የሚያሳስበው አጠንክሮ ነው፡፡
ኢሳ.43:10-13”… ከእኔ በፊት አምላክ አልተሠራም ከእኔም በኋላ አይሆንም። እኔ፥ እኔ እግዚአብሔር ነኝ፥ ከእኔ ሌላም የሚያድን የለም። ተናግሬአለሁ አድኜማለሁ አሳይቼማለሁ፥ በእናንተም ዘንድ ባዕድ አምላክ አልነበረም፤ ስለዚህ እናንተ ምስክሮቼ ናችሁ፥ ይላል እግዚአብሔር፥ እኔም አምላክ ነኝ። ከጥንት ጀምሮ እኔ ነኝ ከእጄም የሚያመልጥ የለም፤ እሠራለሁ፥ የሚከለክልስ ማን ነው?” ይላል፡፡
በኢሳ.33:22 ”እንደተናገረው እግዚአብሔር ፈራጃችን ከሆነ፥ እግዚአብሔር ሕግን ሰጪያችን ከሆነና እግዚአብሔር ንጉሣችን ከሆነ ያለምንም ጥርጣሬ እርሱ አዳኛችን ነው። በግልጽ እንደምናየው እግዚአብሄር ለተዛባብን ፍርድ ቅን ፈራጃችን ነው፤ በጠላት ክፉ ተንኮል ምክኒያት ለሚገጥመን እንቅፋትና የተጣመመ ፍርድ እርሱ የነጻነት ፍርድ ሰጪ ነው፡፡”
እግዚአብሄር አዳኝ የመሆኑን ባህሪ ከላይ በቃሉ ውስጥ በግልጥ የምናየው ነው፡፡ አዳኙ ጌታ ኢየሱስ አዳኝነቱ ከታላቁ ዘላለማዊ ጥፋት ጀምሮ አስከ ቀላል የሚሰኝ እንቅፋት ድረስ ያለውን ጉዳት፣ ጥፋትና መቅሰፍት ሁሉ ሊጋርድ፣ ሊያስወግድና ሊያጠፋ የሚሰራ አምላክ ነው፡፡ ሁሌም ቢሆን እግዚአብሄር ደርሶ የሚታደገው አጋንንት ከሚሰሩት የጥፋት ወጥመድ ሁሉ ነው፡፡
ኤፌ5:23 ”ክርስቶስ ደግሞ የቤተ ክርስቲያን ራስ እንደ ሆነ እርሱም አካሉን የሚያድን እንደ ሆነ ባል የሚስት ራስ ነውና።”
ህዝቡን ያድናቸዋልና ስሙን ኢየሱስ ትይዋለሽ የሚል የመላእክት ቃል ጌታችን ከመወለዱ በፊት ተነግሮለታል፡፡
– እግዚአብሄር ከሀጢያት ያድናል
የጥፋት ሁሉ መሰረት ከሆነው የዲያቢሎስ ስራ እግዚአብሄር ያድናል፡፡ በዮሐ.11:50-52 ውስጥ እንደተገለጠው ጌታ በምድር ላይ ሳለ በወቅቱ የነበረው ሊቀ ካህናት ቀያፋ አንድ ታላቅ ትንቢት ተነገረ፡-
”ሕዝቡም ሁሉ ከሚጠፋ አንድ ሰው ስለ ሕዝቡ ይሞት ዘንድ እንዲሻለን አታስቡም አላቸው። ይህንም የተናገረ ከራሱ አይደለም፥ ነገር ግን በዚያች ዓመት ሊቀ ካህናት ነበረና ኢየሱስ ስለ ሕዝቡ ሊሞት እንዳለው ትንቢት ተናገረ፤ ስለ ሕዝቡም ሁሉ አይደለም፥ ነገር ግን የተበተኑትን የእግዚአብሔርን ልጆች ደግሞ በአንድነት እንዲሰበስባቸው ነው እንጂ።”
የሀጢያት ሀይል ገዝቶን ሳለ የእግዚአብሄር ጠላቶች ሆነን ተቆጥረን ነበር፤ እግዚአብሔር ግን በልጁ ሞት ምክኒያት ሊታረቅን በቃ፡፡ ይህ ብቻ አይደለም ከታረቅን በኋላ በሕይወቱ እንድንድን ምህረትን አደረገልን፡፡
ቆላ.1:13-14 ”እርሱ ከጨለማ ሥልጣን አዳነን፥ ቤዛነቱንም እርሱንም የኃጢአትን ስርየት ወዳገኘንበት ወደ ፍቅሩ ልጅ መንግሥት አፈለሰን።”
የእስራኤል ጌታ አምላክ ጐብኝቶ ለሕዝቡ ቤዛ ያደረገበት ዘመን በብሉይ ኪዳን ተስፋ ሰጥቶ በአዲስ ኪዳን የፈጸመውን ስራ እውን ያደረገ ነው፡፡ ከጥንት ጀምሮ በነበሩት በቅዱሳን ነቢያት አፍ ተናግሮ እንደነበረ በብላቴናው በዳዊት ቤት የመዳን ቀንድን አስነስቶአል፤ ጌታ ኢየሱስን ከይሁዳ ነገድ እንዲወጣ በማድረግ እግዚአብሄር ተስፋውን ፈጽሞአል፤ ማዳኑም ወደረኛ ከሆኑ አጋንንት ነው፤ ይህም ሲሆን ለእምነት አባቶች ለነአብረሀም የተናገረው ተስፋ እውን እንዲሆን አድርጎአል፤ ለነርሱ የማለውን መሐላውንም ቅዱሱን ኪዳን አስቦአል፡፡
ስለዚህ ለአማኝ ትልቅ ደስታ ሆኖ የሚታየው እግዚአብሔር ለቍጣ እንዳልመረጠን የተነገረው ማስተማመኛ ነው፣ በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሞት ምክኒያት በተቆረሰልን ስጋና በፈሰሰልን ደም መዳንን አግኝተናልና።
ቲቶ3:5 ”እንደ ምሕረቱ መጠን ለአዲስ ልደት በሚሆነው መታጠብና በመንፈስ ቅዱስ በመታደስ አዳነን እንጂ፥ እኛ ስላደረግነው በጽድቅ ስለ ነበረው ሥራ አይደለም”
– እግዚአብሄር ከክፉ አሳብ ያድናል
ምሳ.12:20 ”ክፉን በሚያስቡ ልብ ውስጥ ተንኰል አለ፤ በሰላም ለሚመክሩ ግን ደስታ አላቸው።”
እግዚአብሔር የሰው ክፉት በምድር ላይ እንደበዛ፣ የልቡ አሳብ ምኞትም ሁልጊዜ ፈጽሞ ክፉ መሆኑን አየ፡፡ ስለዚህ ሰውን በምድር ላይ በመፍጠሩ ተጸጸተ፥ በልቡም አዘነ፣ ሰውን ሊያጠፋም ወሰነ። ከሰው ክፋት የተነሳ ምድር በእግዚአብሔር ፊት ተበላሸች፤ ምድርም ግፍን ተሞላች። እግዚአብሔር ምድርን ባየ ጊዜ የተበላሸች እንደሆነች አየ፤ ሥጋን የለበሰ ሁሉ በምድር ላይ መንገዱን አበላሽቶ ነበርና። ስለዚህ እግዚአብሄር ሰውን ከምድር ጠርጎ ሊያጠፋ ሲወስን ጻድቁ ኖህን አገኘውና ውሳኔውን አሳወቀው፡፡
የሰው የልብ ክፉ አሳብ የእግዚአብሄርን ቁጣ የሚያነሳሳ ቢሆንም፣ ሰውን ለዘላለም መጣል የማይሻ አምላክ ግን ሰው ይድን ዘንድ፣ ቅድሚያ ከልቡ ክፋት ሊያላቅቀውና ነጻ ሊያወጣው ወስኖአል (ለስጋ ምኞት ተላልፎ እንዳይሰጥ ሊረዳው ወስኖአል)፡፡
በኤር.4:14 ላይ ሲናገር፡-
”ኢየሩሳሌም ሆይ፥ ትድኚ ዘንድ ልብሽን ከክፉ ነገር እጠቢ። ክፉ አሳብ የሚኖርብሽ እስከ መቼ ድረስ ነው?” ይላል የዳኑትን ነገር ግን ከአመጽ ህይወት ሊላቀቁ ያልቻሉትን ለማስጠንቀቅ፡፡
ከልብ የሚወጣ ክፉ አሳብ አደጋ ይጠራል፣ ይህ ከክፉ ልብ የተወለደ ክፉ ነገር ወጥቶ አንደበት ላይ ይቀመጣል፤ አርፎ መቀመጥም አያውቅ፣ እየተሰራጨ ክፋትን በአለም ላይ ያዳርሳል፤ ጽድቅን ያበላሻል፤ በጎውንም ያጠፋል፡፡ ለዚህ ነው በእግዚአብሄር የተጠራ ህዝብ ያለብሽ ከተማ ሆይ በውስጥሽ ያሉ በልባቸው ያከማቹትን የክፋት አሳብ ጠርገው በማውጣት ይታደሱ ሲል የተጣራው፡፡
ማቴ.15:18-20 ”ከአፍ የሚወጣ ግን ከልብ ይወጣል፥ ሰውንም የሚያረክሰው ያ ነው። ከልብ ክፉ አሳብ፥ መግደል፥ ምንዝርነት፥ ዝሙት፥ መስረቅ፥ በውሸት መመስከር፥ ስድብ ይወጣልና። ሰውን የሚያረክሰው ይህ ነው እንጂ፥ ባልታጠበ እጅ መብላትስ ሰውን አያረክሰውም። ”
ሰዎች የራሳችን ክፉ አሳብ የሚበላን ፍጥረቶች ነን፡፡ ከዚህ አስፈሪ ሁኔታ ሊያድን የሚችለው ታዳጊ ግን የልብ ፈጣሪ እግዚአብሄር ብቻ ነው፡፡ንጉስ ዳዊት ይሄን አጥብቆ ለልጁ ስለፈራ በጥሞና ሲያስጠነቅቀው በ1ዜና.28:9 ውስጥ ይታያል፡፡
”ልጄ ሰሎሞን ሆይ፥ እግዚአብሔር ልብን ሁሉ ይመረምራልና፥ የነፍስንም አሳብ ሁሉ ያውቃልና፥ የአባትህን አምላክ እወቅ፤ በፍጹም ልብና በነፍስህ ፈቃድም አምልከው፤ ብትፈልገው ታገኘዋለህ፤ ብትተወው ግን ለዘላለም ይጥልሃል።” ሲልም በብርቱ ያስገነዝበዋል፡፡
ሐዋ.8:22 ”እንግዲህ ስለዚህ ክፋትህ ንሰሐ ግባ፥ ምናልባትም የልብህን አሳብ ይቅር ይልህ እንደ ሆነ ወደ እግዚአብሔር ለምን፤”
ከመናፍስት አሳብ ያድናል
በዮሐ.13:2 ላይ ”እራትም ሲበሉ ዲያብሎስ በስምዖን ልጅ በአስቆሮቱ በይሁዳ ልብ አሳልፎ እንዲሰጠው አሳብ ካገባ በኋላ…” የሚል ቃል አለ፡፡ ይህ ቃል ልባችንን ከክፉ አሳብና ምኞት መከለል ሲያቅተን ለክፉ መናፍስት ጥቃት ተላልፈን እንደምንሰጥ ያሳያል፡፡ ይሁዳ በአካል ከጌታ ጋር ያለ ቢመስልም ውስጡ በሰይጣን ቁጥጥር ስር ነበር፤ አሳቡ ተማርኮ በክፉ አሳብ ሲወረስ አላስተዋለም፣ ስለዚህ ወደ ስህተት እየገባ ሳለ ሊመለስ አልቻለም፣ ይልቅ ወደ ጥፋት ተንደረደረ እንጂ፡፡
2ቆሮ.10:5 ”የሰውንም አሳብ በእግዚአብሔርም እውቀት ላይ የሚነሣውን ከፍ ያለውን ነገር ሁሉ እናፈርሳለን ለክርስቶስም ለመታዘዝ አእምሮን ሁሉ እንማርካለን፥”
ሰውን የሚያድን የወንጌል እውቀት በፍጥረት ጆሮ ደርሶ መዳን ሊያገኝ፣ ለክርስቶስም ሊታዘዝ የተገባ ሆኖ ሳለ፣ በአጋንንት የተጠመዘዘ የሰው አሳብ ሲሰለጥን ግን በህያው ወንጌል ላይ ታላቅ እንቅፋት እንደሚፈጥር ቃሉ ያረጋግጣል፡፡
ጌታ ኢየሱስ የተቀበለን መፍረስ ያለበትን አጥፊ መናፍስታዊ አሳብ ከስሩ ነቅሎልን ነጻ በማውጣት ነው፡፡ የዳንነው ከተያዝንበት መናፍስታዊ ስርአት በቀላሉ ተላቀን ሳይሆን ከፍ ያለው የመሸገው አጥፊ እሳብ በጸጋው አሰራር ተወግዶልን እንደሆነ ማስተዋል ተገቢ ነው፡፡
ሮሜ.8:27 ” ልብንም የሚመረምረው የመንፈስ አሳብ ምን እንደ ሆነ ያውቃል፥ እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ ስለ ቅዱሳን ይማልዳልና።”
የመንፈስ አሳብ የእግዚአብሄር አሳብ በልባችን እንዲያድርና የሰይጣን አሳብ እንዳይስበን ይጋርደናል፣ ጸጋው እንዲያገኘን ወደ እርሱ መጠጋት መፍትሄ ነው፡፡
2ቆሮ.2:611 ”… በሰይጣን እንዳንታለል፤ የእርሱን አሳብ አንስተውምና።”
2ቆሮ.4:4 ”ለእነርሱም የእግዚአብሔር ምሳሌ የሆነ የክርስቶስ የክብሩ ወንጌል ብርሃን እንዳያበራላቸው፥ የዚህ ዓለም አምላክ የማያምኑትን አሳብ አሳወረ።”
ከአለም አሳብ ያድናል
ሰይጣን በአለም ውስጥ በሰው ልጆች ላይ የዘረጋው የጥፋት አሰራር ስርአት አለ፤ እግዚአብሄር ደቀመዛሙርትን ከዚህ ጥፋት ያስመልጥ ዘንድ አለማዊ አሳብ ላይ ጸጋውን ይገልጣል፡፡
ቲቶ2:11-13 ”ሰዎችን ሁሉ የሚያድን የእግዚአብሔር ጸጋ ተገልጦአልና፤ ይህም ጸጋ፥ ኃጢአተኝነትንና ዓለማዊን ምኞት ክደን፥ የተባረከውን ተስፋችንን እርሱም የታላቁን የአምላካችንንና የመድኃኒታችንን የኢየሱስ ክርስቶስን ክብር መገለጥ እየጠበቅን፥ ራሳችንን በመግዛትና በጽድቅ እግዚአብሔርንም በመምሰል በአሁኑ ዘመን እንድንኖር ያስተምረናል”
አሳባችን በአለማዊው ስርአት ሲሳብና ሲታለል በውስጡ በሚሰራው መንፈስ ይዋጣል፡፡ በሌላ በኩል መንፈሳዊ የሚመስል አለማዊ ትምህርት ሾልኮ በመግባት እምነትን የሚያናጋ አሳብ እንዳይፈጥር በግልም በህብረትም መከላከል ይገባል፡፡
ልዩ ልዩ ዓይነት የሆነ እንግዳ ትምህርት ደቀመዛሙርትን ለማናወጥና ከእምነት ነቅሎ ለመውሰድ ከአለም ይወጣል፤ ልባችን ግን በጸጋ ቢጸና በእግዚአብሄር እውቀት ላይ ታንጸንና ጸንተን አንንኖራለን፡፡
ቆላ.2:8-9 ”እንደ ክርስቶስ ትምህርት ሳይሆን፥ እንደ ሰው ወግና እንደ ዓለማዊ እንደ መጀመሪያ ትምህርት ባለ በፍልስፍና በከንቱም መታለል ማንም እንዳይማርካችሁ ተጠበቁ። በእርሱ የመለኮት ሙላት ሁሉ በሰውነት ተገልጦ ይኖራልና።”
– እግዚአብሄር ከመቅሰፍት ያደነናል
በየእለቱ ከሚጋረጡብን አደጋዎች እግዚአብሄር ይታደገናል፡-
የሰው ልጆች ጠላት የሆነ እርኩስ መንፈስ ከሚያጠምድብን ወጥመድ ከሚያስደነግጥም አስፈሪ ነገር እርሱ ያድነናል። ከሚወረውረው ፍላጻ በላባዎቹ ይጋርደናል፥ ታማኝ ስለሆነ ስፍራችንን በክንፎቹ በታች አድርገን በርሱ እንተማመናለን፤ የቃሉ እውነት እንደ ጋሻ ከጠላት ሽንገላ ሊጋርድ ነፍሳችንን፣ መንፈሳችንን፣ ልባችንንም ይከብባል። በእንዲህ ያለ ከፍተኛ ጥንቃቄ አምላካችን ከሌሊት ግርማ፥ በቀን ከሚበርር ፍላጻ፥ በጨለማ ከሚሄድ ክፉ ነገር፥ ከአደጋና ከቀትር ጋኔን ይጋርደናልና ጭሩሱን አንፈራም (መዝ.91:3-6)፡፡
እግዚአብሄር የሁሉ ፈጣሪና ባለቤት የመሆኑ ምስጢር ሲገለጥ የሚታመኑትን በእምነት ያሳርፋል፤ የእግዚአብሄር ሰዎች የሚድኑበትን የርሱን ማንነት ለመግለጥ ሲሞክሩ እንዲህ ይሉታል፡-
”እግዚአብሔር ፈራጃችን ነው፥ እግዚአብሔር ሕግን ሰጪያችን ነው፥ እግዚአብሔር ንጉሣችን ነው፤ እርሱ ያድነናል” (ኢሳ.33:22)፡፡
– መፍታት ከማንችላቸው እንቆቅልሽ አሳቦች ያድነናል
እግዚአብሄር ህዝቡ ከመንገድ በሳተና ጥፋት ውስጥ በገባ ጊዜ የሚታደግበትን መንገድ ማመላከቻና ምሪትን መስጫ ትእዛዝ ይልካል፡፡ ጥፋት ውስጥ በምንሆንበት አጋጣሚ ነፍሳችን ለመፍታት በሚያዳግት የአሳብ ግፊት ላይ ትወድቃለች፤ ሆኖም ያን የሚያስጨንቅና መፍቻ ያጣ አሳብ መሻር የምትችለው የእግዚአብሄር የማጽናኛ ድምጽ ሲመጣላት ብቻ ይሆናል፡፡ የእግዚአብሄር ማጽናናት ሲመጣ የነፍስ ሀሴት ይመጣል፡፡ ዮሴፍ ማርያም ጽንስ ይዛ በነበረ ጊዜ ሳይጋቡ በፊት በሆነው ነገር እጅግ ደንግጦና ተጨንቆ ነበር፡፡ ያስጨነቀውን አሳብ በልቡ ይዞ ለጥያቄው መልስ ሳያገኝ ቆየ፡፡ በዚያን ወቅት መውጣትና መግባት እስኪያቅተው ድረስ ጭንቀቱ በርትቶ የት ድረስ ሊያደርሰው እንደሚችል መገመት አያዳግትም፤ የሙሴን ህግ ስናስብ ማርያም ላይ ሊማጣ የሚችለው በድንጋይ የመወገርና የመሞት ፍርድ ስለምናገኝ ዮሴፍ ላይ የወረደውን የመንፈስ ሁከት በልቦናችን መሳል እንችላለን፡፡ በጽድቅ በእግዚአብሄር ፊት የምትኖርን ሴት በእንዲያ ያለ ታላቅ ሀጢያት (አርግዛ ማየት) ውስጥ ማግኘት (ለዚያውም የራሱ እጮኛ የሆነች) ሳያንሰው የሚወርድባት እፍረቱም ፍርዱም (በድንጋይ ተወግራ መሞቱም) እጅግ ያውከዋል፡፡ ሁዋላ ግን እግዚአብሄር ለእንቆቅልሹ መልስ የሚሆን ድምጽ ስለላከለት ከጭንቀቱ አርፎአል፣ በተፈታው እንቆቅልሽ እጅግ አጽናንቶታል፡፡ እጮኛህን ለመውሰድ አትፍራ የሚል ድምጽ ነጻ አወጣው፡፡ ዲቃላ ነው ብሎ የደመደመው ጽንስ መድሀኒት መሆኑ ታወጀና ህዝቡን ከሀጢያታቸው ያድናቸዋልና ስሙን ኢየሱስ ትለዋለህ ሲባል በደስታ ተጥለቀለቀ፡፡ ዮሴፍ መላኩ እንዳዘዘው ማርያምን በደስታ ለመውሰድ ተስማማ፣ እግዚአብሄር በውስጡ ከተፈጠረው አስጨናቂ አሳብ ነጻ አውጥቶታልና፡፡
የጌታ መልእክት ሲመጣ ለልብ ደስታ የሚሆን ተከታታይ በረከት ይመጣል፡፡ ዮሴፍ ሲታዘዝ የተከተለው ደስታና እረፍት ነበር፣ ምክኒያቱም መታዘዙ የእግዚአብሄርን ፈቃድ ያስከተለ ስለነበር፡፡
ዳን.3:17 ”የምናመልከው አምላካችን ከሚነድደው ከእሳቱ እቶን ያድነን ዘንድ ይችላል፤ ከእጅህም ያድነናል፥ ንጉሥ ሆይ!”