እግዚአብሄር በፍቅሩ የጠራቸው ሰዎች የጠራቸውን አምላክ ታዝዘው በመውጣት ፈቃዱን ሲከተሉና ሲፈጽሙ ኖረዋል፡፡ ጥሪውን ሰምተው ለመውጣት የፈቀዱ እነዚህ ታማኝ ሰዎች ታሪካቸው ለትምህርታችን እንዲነገር በቃሉ ውስጥ ተጠቅሰዋል፡፡ የጥቂቶችን ታሪክ አስቀድመን ያየን ሲሆን ከዚህ በመቀጠል ተጨማሪ ሰዎችን እናያለን፡-
• አብረሃም ወገንና ቤተሰቦቹን ትቶ ወጥቶ ነበር
አብረሃም እግዚአብሄር ወደ ነገረው ስፍራ ሲወጣ ሁሉን ነገር ትቶ በመከተል ነበር፡፡ ያኔ አብረሃምን ከእግዚአብሄር ጥሪ ሊያደናቅፍ የሚችል ጠንካራ ማህበራዊ ትስስር ነበረ፤ በዙሪያው የተኮለኮለውም ዘመድ አዝማድ ብዙ ስለነበር እግዚአብሄር ሲጠራው አስሮ የሚያስቀረው ሰበብ ብዙ እንደነበር ያሳያል፡፡ ነገር ግን እርሱ በጥሪው ጉልበት ያን ሁሉ ማሰሪያ በጣጥሶ ሊወጣ በቅቶአል፡-
ዘፍ.12:1-4” እግዚአብሔርም አብራምን አለው፡- ከአገርህ ከዘመዶችህም ከአባትህም ቤት ተለይተህ እኔ ወደማሳይህ ምድር ውጣ።ታላቅ ሕዝብም አደርግሃለሁ፥ እባርክሃለሁ፥ ስምህንም አከብረዋለሁ፤ ለበረከትም ሁን፤የሚባርኩህንም እባርካለሁ፥ የሚረግሙህንም እረግማለሁ፤ የምድር ነገዶችም ሁሉ በአንተ ይባረካሉ።አብራምም እግዚአብሔር እንደ ነገረው ሄደ፤ ሎጥም ከእርሱ ጋር ሄደ፤ አብራምም ከካራን በወጣ ጊዜ የሰባ አምስት ዓመት ሰው ነበረ።”
እግዚአብሄር አብረሃምን ሲጠራው ከዋስትና ጋር ስለነበረ የሚበልጥ ነገር እንዲያይ አይኑ ተከፍቶ ነበር፡፡ በእግዚአብሄር ጥሪ ውስጥ የነበረው ፍቅር አብረሃምን ያመለከተው ምን ነበር? ከአገርህ ከዘመዶችህም ከአባትህም ቤት ተለይተህ እኔ ወደማሳይህ ምድር ውጣ ሲለው የሚበልጥ አገር እንደሚሰጠው አመነ፣ ከዘመዶቹና ከአባቱ ቤት የሚበልጥ ቤት እንደሚሰራለት የሚያመለክት ቃል እንደነገረው አስተውሎ ነበርና አብረሃም ያንንም አመነ። አብረሃም ወገኖች መሀል ታጅቦ እየኖረ ሳለ እንዲወጣ ሲጠራና እርሱም ሳያመነታ ሲወጣ ሲታይ ሂደቱ የሚያስፈራ ይመስላል፡፡ እንዲያ ይምሰል እንጂ እግዚአብሄር ታላቅ ሕዝብ አደርግሃለሁ፥ ካለህ በረከት ይበልጥ እባርክሃለሁ፥ በአባትህ ቤት ካለህ ክብር ይልቅ ስምህንም አከብረዋለሁ ያለው ለርሱ በግልጽ ታይቶት ነበር፡፡ ስለዚህ በዚያ ታላቅ የተስፋ ቃል የተማረከው አብረሃም በእምነት ወጣና እግዚአብሔር እንደ ነገረው ሄደ፡፡
ዕብ.11:8-12 ”አብርሃም የተባለው ርስት አድርጎ ሊቀበለው ወዳለው ስፍራ ለመውጣት በእምነት ታዘዘ፥ ወዴትም እንደሚሄድ ሳያውቅ ወጣ። ለእንግዶች እንደሚሆን በተስፋ ቃል በተሰጠው አገር በድንኳን ኖሮ፥ ያን የተስፋ ቃል አብረውት ከሚወርሱ ከይስሐቅና ከያዕቆብ ጋር፥ እንደ መጻተኛ በእምነት ተቀመጠ፤መሠረት ያላትን፥ እግዚአብሔር የሠራትንና የፈጠራትን ከተማ ይጠብቅ ነበርና። ተስፋ የሰጠው የታመነ እንደ ሆነ ስለ ቈጠረች፥ ሣራ ራስዋ ደግሞ ዕድሜዋ እንኳ ካለፈ በኋላ ዘርን ለመፅነስ ኃይልን በእምነት አገኘች። ስለዚህ ደግሞ በብዛታቸው እንደ ሰማይ ኮከብ እንደማይቈጠርም በባሕር ዳር እንዳለ አሸዋ የነበሩት የሞተን ሰው እንኳ ከመሰለው ከአንዱ ተወለዱ።”
በመጨረሻው ዘመን ያለው ጣይ ሰበብ እንዳይዘን እኛስ ምን እናድርግ? በዋናነት የተሰጠንን ዘላለማዊ ተስፋ በመንፈስ ቅዱስ በፈሰሰልን ፍቅር በኩል አጥብቀን እንያዝ፣ በማስከተል መከተልን ያለብንን ማጥበቅና መተው ያለብንን መልቀቅ፣ እርሱን መፍራት የተናገረውንም መጠንቀቅ አለብን፡፡
• ሙሴ ስለጽድቅ ሲል የግብጻውያን ወራሽነቱን ትቶአል
የሙሴ ህይወት በባእድ ምድር በአስገራሚ ሁኔታ በድል፣ በተድላና በተስፋ የተከበበ ቢሆንም ለወገኖቹ ከነበረው ፍቅር የተነሳ ከነዚህ ጥቅሞች ራሱን ገሸሽ ሊያደርግ የወሰነ ሰው ነበር፡፡ ሙሴ በታላቅ እንክብካቤ በፈርኦን ቤት ሲያድግ ስጋው በንጉሱ ምግብ፣ ማንነቱ ግን በእስራኤላውያን ትምህርት ተገንብቶ ነበር፡፡ ስለዚህ አሳዳጊ ሆና በገባች ወገኑ በኩል የእስራኤልን ተስፋ እየተመገበ አደገ፤ የእግዚአብሄር ፍቅርም አብሮት በውስጡ አደገ፣ በስተመጨረሻም ከምቾቱ ፈንቅሎ ስለህዝቡ ሲል ወደ መከራና እንግልት እንዲገባ አስገደደው፡፡
ዕብ.11:23-27 ”ሙሴ ከተወለደ በኋላ ወላጆቹ ያማረ ሕፃን መሆኑን አይተው በእምነት ሦስት ወር ሸሸጉት የንጉሥንም አዋጅ አልፈሩም። ሙሴ ካደገ በኋላ የፈርዖን የልጅ ልጅ እንዳይባል በእምነት እምቢ አለ፤ ከግብፅም ብዙ ገንዘብ ይልቅ ስለ ክርስቶስ መነቀፍ እጅግ የሚበልጥ ባለ ጠግነት እንዲሆን አስቦአልና ለጊዜው በኃጢአት ከሚገኝ ደስታ ይልቅ ከእግዚአብሔር ሕዝብ ጋር መከራ መቀበልን መረጠ፤ ብድራቱን ትኵር ብሎ ተመልክቶአልና። የንጉሡን ቍጣ ሳይፈራ የግብፅን አገር የተወ በእምነት ነበር፤ የማይታየውን እንደሚያየው አድርጎ ጸንቶአልና።”
ሙሴ የእግዚአብሄርን ብድራት የሚመለከትበት መንፈሳዊ አይን ነበረው፤ ስጋዊውማ ሊያይ የሚችለው የፈርኦንን ቤት ተድላ፣ ማእረግና ክብር ነው፡፡ ሆኖም በፈርኦን ቤት ከሞላው ክብር ሊሸሽ ሲወስን እምቢተኝነቱ የሚያደርስበትን ቁጣ እንዳይፈራ ልቡን በእምነት የሞላው ያ የእግዚአብሄር ብድራት ረዳው፡፡ ይህ ሰው እንዲህ አይነት መንፈሳዊ ጉልበት እንዳለው ብንረዳም በእግዚአብሄር ፊት እጅግ ትሁትና ቅን ነበር፡፡ ያም ከእግዚአብሄር ጋር በድል እንዲጉዋዝና ተለይቶ የወጣበትን አላማ እንዲያሳካ ረድቶታል፡፡ ዛሬም እግዚአብሄርን ብለው ወደ ፈቃዱ የወጡ ፍቅሩን እንደሙሴ በትህትና ይዘው በቤቱ መኖር እንዲገባቸው ቃሉ ያስተምረናል፡፡
• እስራኤላውያን ግብጽን ትተው ወጡ
እስራኤላውያን በእግዚአብሄር ምሪት ከግብጽ አገር በብዙ ክብርና ሞገስ ወጡ፡፡ ሳይወጡ አስቀድሞ ህይወታቸው በብዙ ግብጻዊ ኮተት የተተበተበ ነበር፤ ነገር ግን ምክኒያታቸውን አስቆርጦ ወደ ምድረ በዳ እንዲወጡ ያደረገ ለአባቶቻቸው የተነገረ ጠንካራ የተስፋ ቃል ነበር፡፡ ቃሉ ከባርነት ሊያወጣና በአምላካቸው ፈቃድ ወደ ተዘጋጀ ስፍራ ሊወስዳቸው እንደሚችል በሙሴ በኩል ተገልጦ በሰራ ወቅት አመኑ፡፡
ዘጸ.13:17-22 ”እንዲህም ሆነ፤ ፈርዖን ሕዝቡን በለቀቀ ጊዜ፥ ምንም ቅርብ ቢሆን እግዚአብሔር በፍልስጥኤማውያን ምድር መንገድ አልመራቸውም፤ እግዚአብሔር፡- ሕዝቡ ሰልፉን ባየ ጊዜ እንዳይጸጽተው ወደ ግብፅም እንዳይመለስ ብሎአልና። ነገር ግን እግዚአብሔር ሕዝቡን በዙሪያ መንገድ በኤርትራ ባሕር ባለችው ምድረ በዳ መራቸው። የእስራኤልም ልጆች ከግብፅ ምድር ተሰልፈው ወጡ።ዮሴፍም፡- እግዚአብሔር ሳይጎበኛችሁ አይቀርም፥ አጥንቶቼንም ከዚህ ከእናንተ ጋር ታወጣላችሁ ብሎ የእስራኤልን ልጆች አምሎአቸው ነበርና ሙሴ የእርሱን አጥንቶች ከእርሱ ጋር ወሰደ። ከሱኮትም ተጓዙ፥ በምድረ በዳውም ዳር በኤታም ሰፈሩ። በቀንና በሌሊትም ይሄዱ ዘንድ፥ መንገድ ሊያሳያቸው ቀን በደመና ዓምድ፥ ሊያበራላቸውም ሌሊት በእሳት ዓምድ እግዚአብሔር በፊታቸው ሄደ።የደመና ዓምድ በቀን፥ የእሳት ዓምድ በሌሊት ከሕዝቡ ፊት ከቶ ፈቀቅ አላለም።”
የእስራኤል ህዝብ በተጠራ ጊዜ አንድ ሰው ሳይቀር ከግብጽ ሙልጭ ብሎ ወጣ፡፡ ህዝቡ ለጥሪው ታዝዞ ወደ ተጠራበት አቅጣጫ መውጣቱ ትልቅ ነገር ሆኖ ሳለ መንገድ ላይ በጉዞ መሀል የተፈጠረበት የልብ መንጠባጠብ ግን የተጠራበትን የተስፋ ቃል እንዲጥል በቁጣ ውስጥም እንዲገባ አድርጎታል፡፡ የእስራኤል አወጣጥና ጉዞ ለመጨረሻው ዘመን አማኞች የሚያስተምረን በእምነት የመጽናትን ዋጋ ነው፡፡
ዘዳ.1:29-36 ”… እኔም አልኋችሁ፡- አትደንግጡ፥ ከእነርሱም አትፍሩ፤ በፊታችሁ የሚሄደው አምላካችሁ እግዚአብሔር፥ እናንተ ስታዩ በግብፅና በምድረ በዳ እንዳደረገላችሁ ሁሉ፥ ስለ እናንተ ይዋጋል፤ ወደዚህም ስፋራ እስክትመጡ ድረስ በሄዳችሁበት መንገድ ሁሉ፥ ሰው ልጁን እንዲሸከም አምላክህ እግዚአብሔር እንደተሸከመህ አንተ አይተሃል። ዳሩ ግን ለሰፈራችሁ የሚገባውን ስፍራ እንዲፈልግላችሁ፥ ትሄዱበት ዘንድ የሚገባውንም መንገድ እንዲያሳያችሁ ሌሊት በእሳት፥ ቀን በደመና በፊታችሁ በመንገድ ሲሄድ የነበረውን አምላካችሁን እግዚአብሔርን በዚህ ነገር አላመናችሁም። እግዚአብሔርም የቃላችሁን ድምፅ ሰምቶ ተቆጣ። ለአባቶቻችሁ እሰጣት ዘንድ የማልሁላቸውን መልካሚቱን ምድር ከእነዚህ ሰዎች ከዚህ ክፉ ትውልድ ማንም አያይም፥ከዮፎኒ ልጅ ከካሌብ በቀር እርሱ ግን ያያታል፤ እግዚአብሔርን ፈጽሞ ተከትሎአልና የረገጣትን ምድር ለእርሱ ለልጆቹም እሰጣለሁ ብሎ ማለ።”
• ኤልሳዕ ሁሉን ትቶ ከኤልያስ ሁዋላ ተከተለ፣ የእግዚአብሄርም አገልጋይ ሆነ
ኤልሳዕ ወደ ኤሊያስ የመጣው የነበረውን ሁሉ በአንድ ቅጽበት ከላዩ አራግፎ በመጣል ነበር፡፡ ይህ ነቢይ በፍጹም ልቡ አምኖ በመውጣቱ የእግዚአብሄርን አገልግሎት እስከመጨረሻው የእድሜ ዘመኑ በስኬት ሊያስቀጥል ችሎአል፡፡ ኤልሳ ከነበረበት የምቾት ህይወት ወጥቶ ይህ ነው ተብሎ ሊጠራ ወደማይችል ዝቅተኛ ኑሮ ውስጥ እንደገባ ብንመለከትም እርሱ ግን ምኞቱ በእጥፍ ቅባት እጥፍ አገልግሎትን ማሳካት ነበርና የኑሮውን ሁኔታ ሳያይ እግዚአብሄርን እያየ እስከመጨረሻው በድል አገለገለ፡፡ የታመነው ጌታም ሳያሳፍረው ከአፉ ጋር ሆኖ ሰርቶለታል፡፡ ዛሬ በእግዚአብሄር መንፈስ መውረድ ምክኒያት ለአማኞች የሚሰጥ የተለያየ ጸጋ እንዴት ተጠብቆ ሳይወድቅ ይቀጥል? ለዚህ መልሱ የኤልሳዕ የህይወት ጉዞ ነው፡፡
1ነገ.19:19-21 ”ከዚያም ሄደ፥ የሣፋጥንም ልጅ ኤልሳዕን በአሥራ ሁለት ጥማድ በሬዎች ሲያርስ፥ እርሱም ከአሥራ ሁለተኛው ጋር ሆኖ አገኘው። ኤልያስም ወደ እርሱ አልፎ መጐናጸፊያውን ጣለበት። በሬዎቹንም ተወ፥ ከኤልያስም በኋላ ሮጦ። አባቴንና እናቴን እስማቸው ዘንድ፥ እባክህ፥ ተወኝ፥ ከዚያም በኋላ እከተልሃለሁ አለው። እርሱም፡- ሂድና ተመለስ፤ ምን አድርጌልሃለሁ? አለው። ከእርሱም ዘንድ ተመልሶ ሁለቱን በሬዎች ወስዶ አረዳቸው፥ ሥጋቸውንም በበሬዎቹ ዕቃ ቀቀለው፥ ለሕዝቡም ሰጣቸው፥ በሉም፤ እርሱም ተነሥቶ ኤልያስን ተከትሎ ሄደ፥ ያገለግለውም ነበር።”
• ሃዋሪያቶች ሁሉን ትተን ተከተልን አሉት
ሃዋሪያትን ጌታ ኢየሱስ ለልዩ ተልእኮ ሊያዘጋጃቸው ጠራቸው፡፡ የተጠሩት በሙሉ ያለምንም ማንገራገር ሁሉን ትተው ተከትለውታል፡፡ ከርቀት ለታዘበ ከጌታ ጋር የነበረው ውሎ ድካምና እንግልት የሞላበት ይመስላል፡- ብዙ ጊዜ በየገጠራማውና በየበረሃው ጉዞ ውስጥ ነበሩ፤ በባህር በማእበል ፍርሀት ውስጥ ነበሩ፤ ከአመጸኞች ጋር ተጋፍጠዋል፤ ተርበዋል፣ ተጠምተዋል… ከዚያም በላይ ሁኔታ ውስጥ ገብተውም ወጥተዋል፤ ግን ያን ሁሉ አሳልፎ ሰማያዊ ክብርን ሊያሳይ የሚችል የጌታ ፍቅር ስለታተመባቸው ከርሱ መገኘት ውጪ ንቅንቅ ሊሉ አልቻሉም፡፡
ማቴ.4:18-25 ”በገሊላ ባሕር አጠገብ ሲመላለስም ሁለት ወንድማማች ጴጥሮስ የሚሉትን ስምዖንን ወንድሙንም እንድርያስን መረባቸውን ወደ ባሕር ሲጥሉ አየ፥ ዓሣ አጥማጆች ነበሩና። እርሱም፡- በኋላዬ ኑና ሰዎችን አጥማጆች እንድትሆኑ አደርጋችኋለሁ አላቸው። ወዲያውም መረባቸውን ትተው ተከተሉት።ከዚያም እልፍ ብሎ ሌሎችን ሁለት ወንድማማች የዘብዴዎስን ልጅ ያዕቆብን ወንድሙንም ዮሐንስን ከአባታቸው ከዘብዴዎስ ጋር በታንኳ መረባቸውን ሲያበጁ አየ፤ ጠራቸውም። እነርሱም ወዲያው ታንኳይቱንና አባታቸውን ትተው ተከተሉት። ኢየሱስም በምኩራቦቻቸው እያስተማረ የመንግሥትንም ወንጌል እየሰበከ በሕዝብም ያለውን ደዌና ሕማም ሁሉ እየፈወሰ በገሊላ ሁሉ ይዞር ነበር። ዝናውም ወደ ሶርያ ሁሉ ወጣ፤ በልዩ ልዩ ደዌና ሥቃይም ተይዘው የታመሙትን ሁሉ አጋንንትም ያደሩባቸውን በጨረቃም የሚነሣባቸውን ሽባዎችንም ወደ እርሱ አመጡ፥ ፈወሳቸውም። ከገሊላም ከአሥሩ ከተማም ከኢየሩሳሌምም ከይሁዳም ከዮርዳኖስም ማዶ ብዙ ሕዝብ ተከተሉት።”
ጌታ ኢየሱስ ሲጣራ የተከተሉት ሁለት አይነት ሰዎች ነበሩ፡- በፍቅሩ ተስበው በፍጹም ልባቸው የተከተሉት ሀዋርያቶችና ሌሎች ደቀመዛሙርት ነበሩ፣ እንዲሁም በምክኒያትና በጊዜያዊ ጥቅም የተያዙ አይሁድ እንዲሁ ነበሩ፡፡ ሁለቱም መነሻቸው አንድ ቢመስልም (ጌታን ማግኘትና ከርሱ ጋር መሆን ቢሆንም) ግባቸው ግን ፍጹም የተለያየ ነበር፡፡
• ስለ እግዚአብሄር መንግስት መሆን ያለባቸው ነገሮች አሉ
ዘኊ.15:39-40” የእግዚአብሔርንም ትእዛዝ ሁሉ ታስቡና ታደርጉ ዘንድ፥ እርስዋን በመከተል ያመነዘራችሁባትን የልባችሁንና የዓይኖቻችሁን ፈቃድ እንዳትከተሉ፥ትእዛዜን ሁሉ ታስቡና ታደርጉ ዘንድ፥ ለአምላካችሁም ቅዱሳን ትሆኑ ዘንድ ዘርፉ በልብሳችሁ ላይ እንዲታይ ይሁን።”
ማቴ.16:24-27” በዚያን ጊዜ ኢየሱስ ለደቀ መዛሙርቱ እንዲህ አለ፡- እኔን መከተል የሚወድ ቢኖር፥ ራሱን ይካድ መስቀሉንም ተሸክሞ ይከተለኝ። ነፍሱን ሊያድን የሚወድ ሁሉ ያጠፋታል፤ ስለ እኔ ግን ነፍሱን የሚያጠፋ ሁሉ ያገኛታል። ሰው ዓለሙን ሁሉ ቢያተርፍ ነፍሱንም ቢያጐድል ምን ይጠቅመዋል? ወይስ ሰው ስለ ነፍሱ ቤዛ ምን ይሰጣል? የሰው ልጅ ከመላእክቱ ጋር በአባቱ ክብር ይመጣ ዘንድ አለውና፤ ያን ጊዜም ለሁሉ እንደ ሥራው ያስረክበዋል።”
ዮሐ.6:26-29” ኢየሱስም መልሶ፡- እውነት እውነት እላችኋለሁ፥ የምትፈልጉኝ እንጀራን ስለ በላችሁና ስለ ጠገባችሁ ነው እንጂ ምልክቶችን ስላያችሁ አይደለም። ለሚጠፋ መብል አትሥሩ፤ ነገር ግን ለዘላለም ሕይወት ለሚኖር መብል የሰው ልጅ ለሚሰጣችሁ ሥሩ፤ እርሱን እግዚአብሔር አብ አትሞታልና። እንግዲህ፡- የእግዚአብሔርን ሥራ እንድንሠራ ምን እናድርግ? አሉት። ኢየሱስ መልሶ፡- ይህ የእግዚአብሔር ሥራ እርሱ በላከው እንድታምኑ ነው አላቸው።”
”ሕዝቤ ግን ቃሌን አልሰሙኝም፥ እስራኤልም አላዳመጠኝም። እንደ ልባቸው ሥራ ተውኋቸው፥ በልባቸውም አሳብ ሄዱ። ሕዝቤስ ሰምቶኝ ቢሆን፥ እስራኤልም በመንገዴ ሄደው ቢሆን፤ ጠላቶቻቸውን ፈጥኜ ባዋረድኋቸው ነበር፥ በሚያስጨንቋቸውም ላይ እጄን በጣልሁ ነበር፤ የእግዚአብሔር ጠላቶችም በተገዙለት ነበር፥ ዘመናቸውም ለዘላለም በሆነ ነበር፤ ከስንዴም ስብ ባበላቸው ነበር፥ ከዓለቱም ማር ባጠገባቸው ነበር።” (መዝ.81:11-16)
መዝ.104:33-35 ”በሕይወቴ ሳለሁ ለእግዚአብሔር እቀኛለሁ፥ ለአምላኬም በምኖርበት ዘመን ሁሉ እዘምራለሁ። ቃሌ ለእርሱ ይጣፍጠው፥ እኔም በእግዚአብሔር ደስ ይለኛል። ኅጥኣን ከምድር ይጥፉ፤ ዓመፀኞች እንግዲህ አይገኙ። ነፍሴ ሆይ፥ እግዚአብሔርን ባርኪ። ሃሌ ሉያ።”