በጎውን፣ መልካሙንና የተሸለውን የጌታ ምህረት ለማግኘት የአለምን ፍቅር፣ የስጋን ምኞትና ሰይጣናዊ ልምምድን መተው፣ መሸሽና መጸየፍ ግድ ይላል፡፡ አመጽን ማቆም፣ ከክፉዎች መለየት፣ ወደተውነው ክፉ ልማድ ዳግም ያለመመለስ ውሳኔን በራስ ላይ ማሳለፍ አስፈላጊ ነው፡፡ እግዚአብሄር ከተከለን ስፍራ ያለመልቀቅ፣ ከክፋት መራቅ፣ የራስን ለርሱ አሳልፎ መስጠትና የጌታን ፈቃድ መከተል የፈለግነውን የጌታ ምህረት እንድንቀበል ያግዘናል፡፡ ጌታን መከተል፣ ቃሉን በፈቃደኝነት መቀበል፣ የእግዚአብሄር አሳብን ማገልገልና ድምጹን መቅረብ ከርሱ ጋር ያስጉዛል፡፡ በተለማመድነው በጎ ነገር ምክኒያት አላስፈላጊ የተባለውን ሰዋዊ አካሄድ መተውና አስፈላጊውን አምላካዊ መንገድ መከተል፣ በእጅ የያዝነውና ለራሴ ብለን ጥብቅ ያልንበትን ያን በእግዚአብሄር ፊት ሞገስ የማያሰጠውን ነገር ትውት በማድረግ ሌላ ቀድሞ ያልነበረንን ግን ከእግዚአብሄር ጋር የሚያስታርቅ ሞገስንም የሚያሰጠውን እንደቃሉ የሆነውን ነገር መከተል ወደ ጠራን ጌታ ያቀርበናል፡፡
ማቴ.4፡18-22 ”በገሊላ ባሕር አጠገብ ሲመላለስም ሁለት ወንድማማች ጴጥሮስ የሚሉትን ስምዖንን ወንድሙንም እንድርያስን መረባቸውን ወደ ባሕር ሲጥሉ አየ፥ ዓሣ አጥማጆች ነበሩና። እርሱም፡- በኋላዬ ኑና ሰዎችን አጥማጆች እንድትሆኑ አደርጋችኋለሁ አላቸው። ወዲያውም መረባቸውን ትተው ተከተሉት። ከዚያም እልፍ ብሎ ሌሎችን ሁለት ወንድማማች የዘብዴዎስን ልጅ ያዕቆብን ወንድሙንም ዮሐንስን ከአባታቸው ከዘብዴዎስ ጋር በታንኳ መረባቸውን ሲያበጁ አየ፤ ጠራቸውም። እነርሱም ወዲያው ታንኳይቱንና አባታቸውን ትተው ተከተሉት።”
የጌታ ኢየሱስ ጥሪ ጊዜና ስፍራን ያማከለ ትክክለኛ ጥሪ መሆኑን የምንረዳው አጠራሩን በማስተዋል ነው፡፡ ከትውልድ መሀል የእግዚአብሄርን ጥሪ የሰሙ ሰዎች ሁሉ ያሉበትን ሁኔታ ትተው ወደ ጠራቸው አምላክ መምጣትን መርጠዋል፡፡ ሁሉን ትቶ መከተል በአምላክ ድምጽ ጥሪ ብቻ የሚሆንበት ምክኒያት የጠሪው ድምጽ ሁሉን ነገር ማስተው የሚችል የፍቅር ሀይል ስለለው ነው፡፡ በመጽሀፍ ቅዱስ ውስጥ ሁሉን ትተው የተከተሉት የእግዚአብሄር ሰዎች እግዚአብሄርን አምነው ወጥተው የሰጣቸውን ተስፋ አግኝተዋል፡፡ ቀርበው ያዩት ወደዱት፡- ከሩቅ ዝናውን የሰሙ ወደእርሱ መምጣት ሆነላቸው፣ ቃሉን በሰሙ ጊዜም ተጠጉት፣ ወደውም ላይለዩት ተከተሉት፡- እነዚህ የትውልድ ተምሳሌቶች ያንን ህያው ጌታ እንዲያ አገኙትና ከርሱ ጋር ኖሩ፡፡ ጌታ ኢየሱስን በልብ ርቀት መከተል ፈጽሞ አይቻልም፡፡ ለአይሁድ በአካል ቅርባቸው ነበር፣ እንዲያውም በመሃከላቸው እለት በእለት ይመላለስ ነበር፤ ሲርባቸው አብልቶአቸዋል፣ ተጠምተው አጠጥቶአቸዋል፤ ታውረው አይናቸውን ሲከፍት፣ ሽባቸውን ሲያዘልል፣ እስራታቸውን ሲፈታ፣ ጎባጣቸውን ሲያቀና ነበር፡፡ ሆኖም በልባቸው ስለራቁት በፍቅራቸው ስላልቀረቡት ሊያገኙት አልቻሉም፡፡
”ፊልጶስ ናትናኤልን አግኝቶ፡- ሙሴ በሕግ ነቢያትም ስለ እርሱ የጻፉትን የዮሴፍን ልጅ የናዝሬቱን ኢየሱስን አግኝተነዋል አለው።ናትናኤልም፡- ከናዝሬት መልካም ነገር ሊወጣ ይችላልን? አለው። ፊልጶስ፡- መጥተህ እይ አለው።ኢየሱስ ናትናኤልን ወደ እርሱ ሲመጣ አይቶ ስለ እርሱ፡- ተንኰል የሌለበት በእውነት የእስራኤል ሰው እነሆ አለ።ናትናኤልም፡- ከወዴት ታውቀኛለህ? አለው። ኢየሱስም መልሶ፡- ፊልጶስ ሳይጠራህ፥ ከበለስ በታች ሳለህ፥ አየሁህ አለው።ናትናኤልም መልሶ፡- መምህር ሆይ፥ አንተ የእግዚአብሔር ልጅ ነህ፤ አንተ የእስራኤል ንጉሥ ነህ አለው።ኢየሱስም መልሶ፡- ከበለስ በታች አየሁህ ስላልሁህ አመንህን? ከዚህ የሚበልጥ ነገር ታያለህ አለው።እውነት እውነት እላችኋለሁ፥ ሰማይ ሲከፈት የእግዚአብሔርም መላእክት በሰው ልጅ ላይ ሲወጡና ሲወርዱ ታያላችሁ አለው።”(ዮሐ.1:46-52)
ናትናኤልን መመልከት ጠቃሚ ነው፡- ከሩቅ ስለ ኢየሱስ ሲሰማ እርሱ ማን ነው በሚል አስተያየት ተናገረ፣ ቀረብ እንዳለው መምህር ሲል ከፍ አደረገው፤ ይበልጥ ተጠግቶ ባስተዋለው ጊዜ ይበልጥ በራለት፣ አንተ የእግዚአብሔር ልጅ ነህ፤ አንተ የእስራኤል ንጉሥ ነህ አለውም። ከዚያን ጊዜ አንስቶ እርሱን መከተል አልተወም፣ አውቆትና ወዶት ነበርና፡፡
ምክኒያቶች
ሁሉን ትቶ ለመከተል የሚያስችል ምክኒያት በሰዎች ዘንድ የሚሆነው በውስጥ ልዩ የፈቃድ ውሳኔ ሲመጣና እሺታ በልብ ተተክሎ ሲገኝ ነው፡፡ ከተያዝንበት የአንዋንዋር ይዘት ጨክነን እንድንወጣና ወዳልተለማመድነው የህይወት ይዘት ፈጥነን እንድንገባ የሚያስገድድ አንድ የፈቃድ ጉልበት ሲያገኘን ብቻ ልባችን ይሸነፋል፤ በዚያ ሁኔታ ውስጥ ሳለን ከእግዚአብሄር የ’ውጡ’ ድምጽ ለውስጣችን ይሰማል፣ ያኔ ያለማቅማማትና ያለመጠራጠር ወደ ጥሪው/ ትእዛዙ አቅጣጫ በማተኮር ፈቅደን እንወጣለን፡፡ እንዲያ ገፍቶ የሚመጣ ታላቅ ሀይል የእግዚአብሄር መንፈስ ሲሆን እርሱ ካላገዘንና የሚያስወስነን ነገር በልባችን ካልኖረ ስፍራ መቀየር የሚባል ነገር በቀላሉ የሚሆን አይደለም፡፡ የሰውን ልብ የሚያሸንፍ ጉልበት እንዲህ ያለ ስራ በማከናወን እስከወዲያኛው ይለውጠናል፡፡
የእኛ የሰው ልጆች ልብ በቀላሉ የሚማረክ አይደለም፡፡ ይህን የሚያውቅ አምላክ እኛን ወደ እርሱ አካባቢ ሊያወጣ ሲያቅድ ወደ ጥሪው አቅጣጫ ማምራት የሚያስችልን መንገድ በእኛ ያኖራል፤ በጥሪው ውስጥ የሚያስቀምጠውን ታዛዥነት የሚፈጥረውና ልባችንን የሚረታው የእግዚአብሄር የራሱ ፍቅር ነው፡፡ ሲጠራን ልባችንን በቅጽበት ይዞ እሺ የሚያሰኝ ይህ የእግዚአብሄር ፍቅር ሃያል ነው፡፡ የርሱ ፍቅር በርቀት ያለነውን ሲጠራ የሚያቀርብ፣ ምቾት ማስጣልና ማስወሰን የሚችል ጉልበተኛ፣ የሚማርክና የሚለውጥ ሀይል ነው፡፡ በርሱ ፍቅር የተያዙትን ሃዋርያት ጌታ ጠየቃቸው፣ እነርሱም በመገረምና ተስፋቸውን በርሱ ላይ በጣለ መንፈስ መለሱለት፡-
ዮሐ.6:65-70 ”ደግሞ፡- ስለዚህ አልኋችሁ፥ ከአብ የተሰጠው ካልሆነ ወደ እኔ ሊመጣ የሚችል የለም አለ። ከዚህም የተነሣ ከደቀ መዛሙርቱ ብዙዎች ወደ ኋላ ተመለሱ፤ ወደ ፊትም ከእርሱ ጋር አልሄዱም። ኢየሱስም ለአሥራ ሁለቱ፡- እናንተ ደግሞ ልትሄዱ ትወዳላችሁን? አለ። ስምዖን ጴጥሮስ፡- ጌታ ሆይ፥ ወደ ማን እንሄዳለን? አንተ የዘላለም ሕይወት ቃል አለህ፤ እኛስ አንተ ክርስቶስ የሕያው የእግዚአብሔር ልጅ እንደ ሆንህ አምነናል አውቀናልም ብሎ መለሰለት። ኢየሱስም፡- እኔ እናንተን አሥራ ሁለታችሁን የመረጥኋችሁ አይደለምን? ከእናንተም አንዱ ዲያብሎስ ነው ብሎ መለሰላቸው።”
ስንጠራ እሺ እንድንል የሚያደርግ ወደ እርሱ ከመጣን በሁዋላም ከርሱ በመጣበቅ ካንተ ወደማን እንሄዳለን የሚያሰኝ እውነተኛ የእግዚአብሄር ፍቅር ለዚህም ትውልድ ያስፈልጋል፡፡ በግልጽ የሚታየው የአለም ሁኔታ ይህን የሚያሳስብ ነው፤ የዚህ ትውልድ ችግር ምልክት የእርሱ እጥረት በመሆኑ ያንን እንድንለምን ያስገድዳል፡፡
በ2ጢሞ.3:1-5 ውስጥ የተቀመጠው ማስጠንቀቂያ ሁላችን እንድንነቃ የሚያሳስብ ነው፡-
”ነገር ግን በመጨረሻው ቀን የሚያስጨንቅ ዘመን እንዲመጣ ይህን እወቅ። ሰዎች ራሳቸውን የሚወዱ ይሆናሉና፥ ገንዘብን የሚወዱ፥ ትምክህተኞች፥ ትዕቢተኞች፥ ተሳዳቢዎች፥ ለወላጆቻቸው የማይታዘዙ፥ የማያመሰግኑ፥ ቅድስና የሌላቸው፥ ፍቅር የሌላቸው፥ ዕርቅን የማይሰሙ፥ ሐሜተኞች፥ ራሳቸውን የማይገዙ፥ ጨካኞች፥ መልካም የሆነውን የማይወዱ፥ከዳተኞች፥ ችኩሎች፥ በትዕቢት የተነፉ፥ ከእግዚአብሔር ይልቅ ተድላን የሚወዱ ይሆናሉ፤ የአምልኮት መልክ አላቸው ኃይሉን ግን ክደዋል፤ ከእነዚህ ደግሞ ራቅ።”
ወደ እግዚአብሄር ጥሪ የሚስብና ከርሱ ጋር ተጣብቅን እንድንኖር የሚያደርገው የእግዚአብሄር የፍቅር ሀይል መሆኑን ካስተዋልን አይቀር አብረን ማስተዋል ያለብን ከፍተኛ ጥንቃቄ የሚፈልገውን ዋና ነገር አብሮ መያዝ እንደሚገባ ማወቅ ይጠቅማል፤ ይህ የምንለው ነገርም ፍቅሩን መቀበል/ማግኘት ብቻ ሳይሆን በፍቅሩ መኖር፣ ፍቅሩን የሚያሸሽ ነገር ውስጥ ያለመጠመድ ይህ ካልሆነ የእግዚአብሄርን ፍቅር እንደምንጥል በዚያ ምክኒያትም ከጠራን አምላክ ፈቃድ አካባቢ እንደምንወጣ ማወቅ ያስፈልጋል፡፡ የመጨረሻውን ዘመን አስጨናቂ ካደረጉት ምክኒያቶች ዋነኛው የእግዚአብሄር ፍቅር በሌላ ፍቅር በመተካቱ ምክኒያት ነውና፡፡ እግዚአብሄርን ወደው የወጡ ፊታቸውን ወደራሳቸውና ወደ አለም ሲመልሱ፣ ተስፋቸውን ከእግዚአብሄር ይልቅ በሌሎች አማራጮች ላይ ያደርጉና የእርሱን ፍቅር ይጥላሉ፡፡ ስለዚህ እግዚአብሄርን ከመውደድ ተመልሰው ራሳቸውን የሚወዱ ይሆናሉ፣ የእርሱን ፍቅር በገንዘብ ፍቅር ይተካሉ፣ በውስጣቸው በመንፈስ የፈሰሰውን የእግዚአብሄር ፍቅር ቸል ብለው ተድላን/ቅምጥልነትን የሚወዱ ይሆናሉ፣ በዚህ ውሳኔያቸው ከእርሱ ይርቃሉ፡፡
ቀረብ አድርገን እንመልከት፡- ”ነገር ግን በመጨረሻው ቀን የሚያስጨንቅ ዘመን እንዲመጣ ይህን እወቅ። ሰዎች ራሳቸውን የሚወዱ ይሆናሉና፥ ገንዘብን የሚወዱ… ፍቅር የሌላቸው፥… መልካም የሆነውን የማይወዱ፥… ከእግዚአብሔር ይልቅ ተድላን የሚወዱ ይሆናሉ… ከእነዚህ ደግሞ ራቅ።”
አማኞች የጠራቸውን ረስተው በሆነላቸው (ያውም እርሱ ራሱ ባደረገላቸው) ነገር ላይ ተጣብቀው ሲሸነፉ አድራጊ ፈጣሪውን ገሸሽ እንደሚያደርጉ ቃሉ ያመለክታል፤ እንዳንሳሳት ያን የሚያደርጉት አለማውያን ሳይሆኑ በስሙ ታምነው የልጅነት ስልጣን ያገኙ በቤቱ ውስጥ ሆነውም እርሱን ብለው የሚኖሩ ሰዎች ናቸው፡፡ እንጀራውን እየበሉና ውሃውን እየጠጡ ተረከዝ ማንሳት ያስነቅፋል፡፡ ከዚህ የሚሻለው በእግዚአብሄር መጽሀፍ ውስጥ ያሉ ራሳቸውን አሸንፈው ከእግዚአብሄር ጋር የኖሩ፣ የተጉዋዙና ድል ያደረጉትን ምሳሌዎች መመልከት ነው፣ ያ ቢሳካና ቢሆንልን እምነት ይጨመርልናል፣ ወደ ፍቅሩ መለስ የማድረግ ዝንባሌም ይፈጥራል፡፡
• ኖህ ከዘመኑ ሰዎች መሀል ተለይቶ ወጣ
ኖኅና የተናገረው ድምጽ በህይወቱ የፈጠረውን ውጤት እንመልከት፡- እግዚአብሄር ኖኅን ተናገረው፤ የእግዚአብሄርም ንግግር ይዞት የመጣው እጅግ ታላቅ ነገር ስለነበር ኖኅ በማስተወል ተቀበለው፡፡ የእግዚአብሄርን ድምጽ እንደዚያ የሰማው ኖህ ትእዛዙን ይፈጽም ዘንድ ያለበትን ሁኔታ ትቶ ወጣ፣ ያን በማድረጉም የእግዚአብሄርን እቅድ አሳካ፡፡ የኖኅ መታዘዝ ከአመጽ መሀል ነጥቆ ወደ እግዚአብሄር አሳብ ውስጥ ሊያስገባው ከመቻሉም ሌላ እርሱም ወገኖቹም እንዲተርፉ ምክኒያት ሆነው፡፡ በአጠገቡ ሆነ በርቀት ከርሱ ጋር የነበረውን ሁሉ ትቶ እርሱን በመከተሉ ኖህ ዳነ!
ዘፍ.6:5-9 ”እግዚአብሔርም የሰው ክፉት በምድር ላይ እንደ በዛ፥ የልቡ አሳብ ምኞትም ሁልጊዜ ፈጽሞ ክፉ እንደ ሆነ አየ።
እግዚአብሔርም ሰውን በምድር ላይ በመፍጠሩ ተጸጸተ፥ በልቡም አዘነ። እግዚአብሔርም፡- የፈጠርሁትን ሰው ከምድር ላይ አጠፋለሁ፥ ከሰው እስከ እንስሳ እስከ ተንቀሳቃሽም እስከ ሰማይ ወፍም ድረስ፤ ስለ ፈጠርኋቸው ተጸጽቼአለሁና አለ። ኖኅ ግን በእግዚአብሔር ፊት ሞገስን አገኘ። የኖኅ ትውልድ እንዲህ ነው። ኖኅም በትውልዱ ጻድቅ ፍጹምም ሰው ነበረ፤ ኖኅ አካሄዱን ከእግዚአብሔር ጋር አደረገ።”
በኖህ ዘመን ወደ ሰው ልጆች የተመለከተው እግዚአብሄር መልካም ነገር በምድር ላይ ሊያገኝ አልቻለም፡፡ ምድርን በልማት እንዲንከባከብ የተሸመው የሰው ልጅ በአመጽ አርክሶአት ተገኘ፡፡ በሚሰራው ክፉ ስራ ፍጹም አጥፍቶአት ነበር፡፡ ምድርን የፈጠረና በሰው ልጅ ስልጣን ስር ያደረጋት እርሱ ምድር በሰው የክፋት ምኞትና አሳብ ምክኒያት ጎድፋና ጎስቁላ ስላየ ተቆጣ፡፡ በውሃም ሊጠራርጋት በውስጡዋ ያለውን አጥፊ የሰው ዘርም ሊደመስስ እግዚአብሄር ወስኖ ተነሳ፡፡ ያን ከባድ ፍርድ እግዚአብሄር ሲያወጣ የሰው ልጅ በምድር ላይ እንደልማዱ ነበር የሚመላለሰው፡፡ ያለማስተዋሉን ያየ እግዚአብሔርም፡- የፈጠርሁትን ሰው ከምድር ላይ አጠፋለሁ፥ ከሰው እስከ እንስሳ እስከ ተንቀሳቃሽም እስከ ሰማይ ወፍም ድረስ፤ ስለ ፈጠርኋቸው ተጸጽቼአለሁና አለ። ኖኅ ግን በፊቱ ሞገስን አገኘ።
እንደ ኖህ ያለ ወደ እግዚአብሄር ለመመልከት የቀና ልብ ያለው በትውልዳችን ከሌለ እንዴት ነው ምድር የምትታየው? የመጨረሻው ዘመን የተያዘው በኖህ ዘመን ሲሰራ በነበረው የድሮው ክፉ መንፈስ እስከሆነ ድረስ፣ የእግዚአብሄር ምህረት ሳይሆን ቁጣው እንዲንቀሳቀስና እንዲፈጥን አልሞ መንፈሱ እኛን በድንግዝግዝ እያርመሰመሰን እስከሆነ ድረስ፣ ዛሬ የሚገባው ከቃሉ ብርሀን በማስተዋል የኖህን ምሳሌ አትኩሮ ማየት፣ ከዚያም የማይሻር ትምህርትን ተቀብሎ ወደ እግዚአብሄር አሳብ መዞር ተገቢም ግድም ነው፡፡
ዘፍ.6:17-19 ”…እኔም እነሆ ከሰማይ በታች የሕይወት ነፍስ ያለውን ሥጋ ሁሉ ለማጥፋት በምድር ላይ የጥፋት ውኃን አመጣለሁ፤ በምድር ያለው ሁሉ ይጠፋል። ቃል ኪዳኔንም ከአንተ ጋር አቆማለሁ፤ ወደ መርከብም አንተ ልጆችህንና ሚስትህን የልጆችህንም ሚስቶች ይዘህ ትገባለህ። ከአንተ ጋር በሕይወት ይኖሩ ዘንድ ሥጋ ካለው ከሕያው ሁሉ ሁለት ሁለት እያደረግህ ወደ መርከብ ታገባለህ፤ ተባትና እንስት ይሁን።”
በኖህ ዘመን በነበሩ ሰዎችና በኖህ በራሱ መሀል የነበረው ልዩነት ግልጽ ነበረ፣ ቃሉም ስለእርሱ ሲመሰክር፡-ኖኅም በትውልዱ ጻድቅ ፍጹምም ሰው ነበረ፤ ኖኅ አካሄዱን ከእግዚአብሔር ጋር አደረገ ብሎአል፡፡ ይህ ብቻ አልነበረም፣ ከኖህ መታዘዝ ጋር ሊወጡ ያሉ ከተገኙ አንድ ሆነው ወደ ጥሪው ሊገሰግሱና እግዚአብሄር በህይወት እንዲቆዩ በፈቀደው ስፍራ ሊገኙ አስፈላጊ ነበረ፡፡
እግዚአብሔር ምድር በሰው ክፉት ተሞልታ እያየና የሰው የልቡ አሳብ ምኞትም ክፋት ብቻ እንደሚያመነጭ እየተመለከተ በዝምታ ሊያልፍ እንደማይችል ቃሉ ያመለክታል፡፡ በሩቁ የኖህ ዘመን ጊዜ የነበረው ያለመታዘዝ ልማድ ከዚያ ትውልድ ጋር አልፎ የቀረ ሳይሆን በመጨረሻው ዘመን ውስጥ እየከፋ እንደሚቀጥል የእግዚአብሄር ቃል ይህንም የሚመሰክረው እውነታ ነው፡፡
2ጴጥ.2:4-10 ”እግዚአብሔር ኃጢአትን ላደረጉ መላእክት ሳይራራላቸው ወደ ገሃነም ጥሎ በጨለማ ጉድጓድ ለፍርድ ሊጠበቁ አሳልፎ ከሰጣቸው፥ለቀደመውም ዓለም ሳይራራ ከሌሎች ሰባት ጋር ጽድቅን የሚሰብከውን ኖኅን አድኖ በኃጢአተኞች ዓለም ላይ የጥፋትን ውኃ ካወረደ፥ኃጢአትንም ያደርጉ ዘንድ ላሉት ምሳሌ አድርጎ ከተማዎችን ሰዶምንና ገሞራን አመድ እስኪሆኑ ድረስ አቃጥሎና ገልብጦ ከፈረደባቸው፥ጻድቅ ሎጥም በመካከላቸው ሲኖር እያየና እየሰማ ዕለት ዕለት በዓመፀኛ ሥራቸው ጻድቅ ነፍሱን አስጨንቆ ነበርና በዓመፀኞች ሴሰኛ ኑሮ የተገፋውን ያን ጻድቅ ካዳነ፥ጌታ እግዚአብሔርን የሚያመልኩትን ከፈተና እንዴት እንዲያድን፥ በደለኞችንም ይልቁንም በርኵስ ምኞት የሥጋን ፍትወት እየተከተሉ የሚመላለሱትን ጌትነትንም የሚንቁትን እየቀጣቸው ለፍርድ ቀን እንዴት እንዲጠብቅ ያውቃል።”
ብዙ ጊዜ የሞራል ዝቅጠትን ስናነሳና የጥፋትን መፋጠን ስንመለከት ሰበባችን በአለም ላይ ወዳሉ አመጸኞች አመልካች ነው፡፡ እነርሱማ ህይወታቸው እንዲያ በመሆኑ ከውጪ ቆመዋል፣ እኛስ?
ስሙን እየጠሩ በምግባራቸው ግን በውጪ ከተንሰራፋው ልማድ ያልወጡ እንዲያውም ከአለማውያን በሚብስ ሁኔታ ውስጥ የሚገኙ ከፍተኛ ጥፋትና መርገምን እየሳቡ ስለመሆኑ ልብ ብለው ሊመለከቱ አይገባም? በኖህ ዘመንም ሆነ በመጨረሻው ዘመን ትውልዱን አስጨናቂ ያደረጉ ስራዎች ወደ እግዚአብሄር የተጠጉ ሰዎች የክፋት ልምምዶች ናቸውና (ዘፍ.6:4-8፣ 2ጢሞ.3:1-5)፡፡
1ቆሮ.5:1-6 ”በአጭር ቃል በእናንተ መካከል ዝሙት እንዳለ ይወራል የዚያም ዓይነት ዝሙት በአሕዛብስ እንኳ የማይገኝ ነው፥ የአባቱን ሚስት ያገባ ሰው ይኖራልና። እናንተም ታብያችኋል፤ ይልቅስ እንድታዝኑ አይገባችሁምን? ይህን ሥራ የሠራው ከመካከላችሁ ይወገድ። እኔ ምንም እንኳ በሥጋ ከእናንተ ጋር ባልሆን፥ በመንፈስ ከእናንተ ጋር ነኝ፥ ከእናንተም ጋር እንዳለሁ ሆኜ ይህን እንደዚህ በሠራው ላይ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ስም አሁን ፈርጄበታለሁ፤ እናንተና መንፈሴም ከጌታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ ኃይል ጋር ተሰብስበን፥መንፈሱ በጌታ በኢየሱስ ቀን ትድን ዘንድ እንደዚህ ያለው ለሥጋው ጥፋት ለሰይጣን እንዲሰጥ ፍርዴ ነው። መመካታችሁ መልካም አይደለም። ጥቂት እርሾ ሊጡን ሁሉ እንዲያቦካ አታውቁምን?”